በሚሸቱ ጫማዎች ላይ ምርምራቸውን ሰርተው ለሽልማት የበቁት ሕንዳዊ መምህር እና ተማሪው

በየቤቱ ቢያንስ አንድ ጠረኑ አፍንጫን የሚረብሽ ጫማ አይጠፋም።

ይህንን በአካባቢያችሁ፣ በምትኖሩበት አፓርትመንት አስቡት፤ ከዚያ እነዚህን አፍንጫ የሚሰነፍጡ ጫማዎች በጋራ ብንደረድራቸው አንድ ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ ችግር ኖረን ማለት ነው።

ሁለት የሕንድ ተመራማሪዎች ግን ስለጫማ ሽታው ሳይሆን ሳይንሱ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ብለው ተነሱ።

መጥፎ ሽታ ያላቸው ጫማዎች እንዴት የጫማ መደርደሪያ የመጠቀም ልምዳችንን እንደሚቀይሩ ለማጥናት ተነሱ።

ይህንን ሲያደርጉም ወደ ተከበረው የአይጂ ኖቤል ሽልማት (Ig Nobel Prize) አዳራሾች ለመግባት በቁ።

አይጂ የኖቤል ሽልማት ቀለል ላለና አስቂኝ ግን ደግሞ ሳይንሳዊ ለሆነ የፈጠራ ጥረት የሚሰጥ ሽልማት ነው።

የ42 ዓመቱ ቪካሽ ኩማር ከደልሂ ወጣ ብሎ በሚገኘው በሺፍ ናዳር ዩኒቨርስቲ የዲዛይን ተባባሪ ፕሮፌሰር ነው።

የ29 ዓመቱ ሳርታክ ሚታል ደግሞ የመጀመርያ ዲግሪውን ሲሰራ ተማሪው ነበር።

በዩኒቨርስቲው ውስጥ መምህር እና ተማሪ ሳሉ ነው የሚሸቱ ጫማዎችን ለማጥናት የወሰኑት።

ሚታል በሚኖርበት አፓርትመንት መተላለፊያ ኮሪደሮቹ በጫማ ተሞልተው ይመለከት እንደነበር ያስታውሳል።

የመጀመርያው ሃሳብ ቀለል ያለ ነበር። ለምን ለተማሪዎች ቅልብጭ ያለች ውብ የጫማ መደርደሪያ ዲዛይን አናደርግም? የሚል።

ነገር ግን ጉዳዩን እያብሰለሰሉት ሲመጡ ጫማዎቹን ወደ ደጅ ያስወረወራቸው የመደርደሪያ እጦት ሳይሆን የሚቆንስ ሽታቸው መሆኑን ተረዱ።

አሁን በሶፍትዌር ኩባንያ ውስጥ የሚሰራው ሚታል "የቦታ ጥበት ወይንም የመደርደሪያ አለመኖር አይደለም። በክፍሉ ውስጥ በቂ ቦታ አለ። ችግሩ በተደጋጋሚ ማላብ እና አንድን ጫማ ሁል ጊዜ መጫማት ናቸው ሽታውን የሚያመጡት" ይላል።

ከዚህ በኋላ ነው መምህሩ እና ተማሪው በተማሪዎች መኖሪያ እየዞሩ ቀለል ያለ ሰብዓዊነት ያለው ጥያቄ መጠየቅ የጀመሩት።

ጫማችን የሚሸት ከሆነ የጫማ ማስቀመጫችንን አያበላሸውም?

ከ149 የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የተሰበሰበው መረጃ፤ 80 በመቶዎቹ ወንዶች ናቸው፣ ብዙዎቻችን የምናውቀውን፤ ነገር ግን አልፎ አልፎ የምንቀበለውን እውነት አረጋግጧል።

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በራሳቸው ወይም በሌላ ሰው ጫማ ጠረን ተሸማቀዋል፤ሁሉም ማለት ይቻላል ጫማቸውን በቤት ውስጥ በጫማ መደርደሪያዎች ላይ ያስቀምጧቸዋል። እንዲሁም ስለ ጠረን ማስወገጃ ምርቶች ማንም ሰምተው አያውቁም።

ጠረንን ያስወግዳል በሚል በልማድ የሚደረጉ፣ የሻይ ከረጢቶችን በጫማ ውስጥ ማስቀመጥ፣ቤኪንግ ሶዳ ወይንም ዲኦድራንት መርጨት የጫማውን መጥፎ ሽታ አላስቆመውም።

ከዚያም ሁለቱ ተመራማሪዎች ወደ ሳይንስ ፊታቸውን አዞሩ።

ሳይንስ ለጫማ ሽታ ተጠያቂ የሚያደረገው በላብ በሚጠቃ እግር ላይ መኖሪያውን የሚያደርገውን ኪቶኮከስ ሴደንታሪየስ (Kytococcus sedentarius) የተባለን ባክቴሪያ ነው።

ሙከራቸው እንደሚያሳየው አጭር የአልትራቫዮሌት ጨረርን በመጠቀም ረቂቅ ተሕዋስያንን መግደል እና ጠረኑንም ማስወገድ ይቻላል።

"በሕንድ ውስጥ እያንዳንዱ ቤተሰብ ማለት ይቻላል አንድ ወይም ሌላ ዓይነት የጫማ መደርደሪያ አለው። እና ጫማውን ከሽታው ውጭ የሚይዝ መደርደሪያ መኖሩ ግልግል ነው ሲሉ ጥናቱን ያደረጉት ተመራማሪዎች ገልጸዋል።

"የሚሸቱ ጫማዎችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ባህላዊውን የጫማ መደርደሪያ እንደገና በጥሩ ንድፍ በመስራት የተጠቃሚዎችን የአጠቃቀም ልምድ ለማሻሻል ጥረዋል።"

ውጤቱስ? የሰውን ልጅ በሚሰራበት አካባቢ እንደሚጠናው ዓይነት ጥናት አይደለም። ልክ ደስ የሚል እንግዳ ሃሳብ ዓይነት ነው። ለማሳያነት ጫማን የሚያከማች ብቻ ሳይሆን ሽታን ማምከን የሚችል ዩቪሲ (UVC) ብርሃን የተገጠመለት የጫማ መደርደሪያ ነው የሰሩት።

ለሙከራው ተመራማሪዎቹ ከፍተኛ ጠረን የነበራቸውን የዩንቨርስቲ አትሌቶች የሚጫሟቸውን ጫማዎችን ተጠቅመዋል።

ባክቴሪያዎች የሚከማቹት የእግር ጣቶች አካባቢ በመሆኑ የዩቪሲ (UVC) ጨረሩ እዚያ አካባቢ እንዲያተኩር አድርገዋል።

ጥናቱ የተጋላጭነት ጊዜን ጠብቆ የሽታውን መጠን ለክቷል።

እናም ባክቴሪያውን ለመግደል እና መጥፎ ሽታውን ለማስወገድ ከ2-3 ደቂቃ የዩቪሲ ጨረሩን መጠቀም በቂ መሆኑን አረጋግጧል።

ቀላል አልነበረም። በጣም ብዙ ጨረር ማለት በጣም ብዙ ሙቀት ማለት ሲሆን ይህም የጫማውን ጎማ ለማቃጠል ይበቃል።

ተመራማሪዎቹ የዩቪሲ ጨረሩን በጫማዎቹ ላይ ብቻ ተጠቅመው ውጤት እናገኛለን አላሉም። እያንዳንዱን ሽታም ይለካሉ።

ሲጀመር ጠረኑ "በጣም ጠንካራ፣ጠንከር ያለ፣ የበሰበሰ ዓይብ የሚመስል" ተብሎ ተገልጿል።

ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ፣ ወደ "በጣም ዝቅተኛ፣ መለስተኛ የሚቃጠል የጎማ ሽታ" ዝቅ ብሏል።

በአራት ደቂቃዎች ውስጥ መጥፎው ሽታ ጠፍቷል። "አማካኝ በሆነ የተቃጠለ የጎማ ሽታ" ተተካ።

ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ጫማዎቹ ከሽታ ነፃ ሆኑ። ነገር ግን ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ድረስ በተጨመረ ቁጥር ጠረኑ ወደ "ጠንካራ የተቃጠለ ጎማ" በመለወጥ ጫማው ይግላል።ይህም በሳይንስ እንኳን ጊዜን መመጠን ሁሉም ነገር መሆኑን አረጋግጧል።

በመጨረሻም ሁለቱ ተመራማሪዎች የዩቪሲ ጨረር የተገጠመላቸው የጫማ መደርደሪያ ሰርተው አቅርበዋል። መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው አይጂ የኖቤል ሽልማት ስለ የምርምር ስራው ተረድቶ እስኪያገኛቸው ድረስ ማንም ዞር ብሎ ያያቸው አልነበረም።

በአናልስ ኦቭ ኢምፕሮቤብል ሪሰርች ጆርናል አዘጋጅነት እና በሐርቫርድ-ራድክሊፍ ግሩፕስ ስፖንሰር የሚደረገው የ34 ዓመቱ አይጂ ኖቤል በየዓመቱ 10 ሽልማቶችን ይሸልማል።

ኩመር "ስለ ሽልማቱ ምንም ሀሳብ አልነበረንም" ብሏል።

"የቆየ የ2022 የጥናት ወረቀት ነበር፤ ወደ የትኛውም ተቋም አልላክንም። የአይጂ ኖቤል ቡድን አገኘን ፤ ደወለልን። እና ይህ በራሱ እንድንስቅ እና እንድናስብ አድርጎናል።"

"ሽልማቱ ለምርምር ምስክር ወረቀት መስጠት ሳይሆን የሳይንስን አስቂኝ ጎን ለማክበር ነው። አብዛኛው ምርምር በፍላጎት የሚሰራ በመሆኑ እና ይህ ሽልማት ወደ ሕዝቡ እንዲደርስ የማስተዋወቂያ መንገድ ነው።"

በዚህ ዓመት ሁለቱ ሕንዳውያን በሽልማቱ መካተታቸው በሚያስደስት ሁኔታ የተዋጣለት የአሸናፊዎች ስብስብ እንዲሆን አድርጓል።

ከዚህ ዓመት አሸናፊዎች መካከል ላሞችን ከዝንብ ለመከላከል ቀለም የቀባው ጃፓናዊው ባዮሎጂስት፣ ቺዝ ያለው ፒዛ የሚወድደው የቶጎው ቀስተደመና እንሽላሊት፣ነጭ ሽንኩርት የእናቶች ጡት ወተት ለሕጻናት ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው እንደሚያደርግ ያገኘውን አሜሪካዊ ተመራማሪ እና አልኮልን መጠጣት ሰዎች በተሻለ ሁኔታ የውጭ ቋንቋን መናገር እንዲችሉ እንደሚያደርግ ነገር ግን ፍርፍሬዎች የለሊት ወፎች በአግባቡ እንዳይበርሩ እንደሚያደርግ ያገኙትን የሆላንድ ተመራማሪዎች ያካተተ ነው።

ለ35 ዓመታት የእግር ጥፍራቸውን እድገት የተከታተሉ የታሪክ ምሁር እና የፓስታ ስጎን እንቆቅልሽ ለመፍታት ምርምር ያደረጉ የፊዚክስ ተመራማሪዎችም የሽልማቱ አካል ናቸው።

ከእነዚህ ተሸላሚዎች ጋር በመሆን በሚሸት ጫማ ማሸነፍ ለሕንድ ተመራማሪዎች አንድ ደረጃ ከፍ ማለት ነው።

"ከእውቅና ባሻገር፣ ኃላፊነት ይጨምራል። አሁን ሰዎች ብዙውን ጊዜ በማያሰቧቸው ነገሮች ላይ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ አለብን" ይላል ኩመር።

በሌላ አነጋገር ዛሬ የሚሸቱ ጫማዎች ነገ ፈር ቀዳጅ ሳይንስ ሊሆኑ ይችላሉ።