ቀን ላይ የምንተኛው አጭር እንቅልፍ ለአእምሮ ጤናችን ጠቃሚ ነው

የተኛ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አጥኚዎች ቀን ቀን የምንትኛት አጭር እንቅልፍ ለአእምሮ ጤናችን ጠቃሚ ናት ይላሉ።

ከቻላችሁ በቀን ለጥቂት ደቂቃ ጋደም ብላችሁ ሸለብ ቢያደርጋችሁ ለአእምሮ ዕድገት ጠቃሚ ነው ይላሉ።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት በቀን እንቅልፍ የሚተኙ ሰዎች አንጎላቸው በ15 ኪዩቢክ ሴንቲሜትር ያድግላቸዋል።

ይህ ማለት እርጅና እነዚህ ሰዎች ላይ መታየት የሚጀምረው ከሶስት እስከ ስድስት ዓመት ዘግይቶ ነው።

ነገር ግን በቀን ጋደም የምንለው ከግማሽ ሰዓት በላይ እንዳይሆን ሳይንቲስቶቹ ይመክራሉ።

ቀን ቀለል ያለች እንቅልፍ ማግኘት ቀላል አይደለም። በተለይ ደግሞ ጥሮ ግሮ ለሚበላ።

“እኛ እያልን ያለነው ሰዎች ከቀን እንቅልፍ ትንሽ ጥቅም ያገኛሉ ነው” ይላሉ ዶክተር ቪክቶሪያ ጋርፊልድ።

እሳቸው ጥናቱ በጣም “አስደሳች” ውጤት ይዞ ብቅ ብሏል ባይ ናቸው።

ልጅ ሳለን ያለአንዳች ሐሳብ የምንለጥጠው እንቅልፍ ለዕድገታችን እጅጉን ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።

ቢሆንም እያደግን ስንመጣ እንቅልፍ እንኳን በጠራራ ፀሐይ በድቅድቅ ጨለማም ብርቅ እየሆነብን ይመጣል።

ከዚያ በኋላ ደግሞ ዕድሜ አካላችንን ሲፈትነው እንቅልፍ ተመልሶ ይመጣል።

ከ65 ዓመት በላይ ከሆናቸው የዕድሜ ባለጠጋዎች 27 በመቶ ያህሉ ቀን ቀን ይተኛሉ።

ዶክተር ጋርፊልድ እንደሚሉት ቀን መተኛት ከሌሎች አካላዊ ልምምዶች ቀለል ያለ ነው። ለምሳሌ “ብዙ ሰዎች” ክብደት መቀነስ እጅግ ሊከብዳቸው ይችላል።

በጠቅላላው የአእምሮ ዕድገት እራሳችንን ዲሜንሺያ ከተሰኘው ከእርጅና ጋር ተያይዞ ከሚመጣ በሽታ [የአእምሮ መዳከም] ሊከላከለን ይችላል።

አንጎላቸውን በተፈጥሮ ዕድሜያችን ሲገፋ እየኮሰመነ ይመጣል። ነገር ግን ቀን ቀን መተኛት ከመርሳት በሽታ ይከላከለን ይሆን ወይ የሚለው ተጨማሪ ጥናት ይፈልጋል።

ዶክተር ጋርፊልድ ሥራ ቦታ እንቅልፍ ከመለጠጥ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መሞከር ያዋጣል ይላሉ።

“እውነት ለመናገር እኔ ቀን ከመተኛት ይልቅ ለ30 ደቂቃ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እመርጣለሁ።”

መልሱን እንዴት ማግኝ ይቻላል?

አጠር ያለ እንቅልፍን ማጥናት ቀላል አይደለም።

እርግጥ ነው ቀን ቁንጥር እንቅልፍ ማግኘት ለጤና ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ሰውነታችን ተዳክሞ ‘እንቅልፍ አምጡ’ እያለ ሊያስቸግረንም ይችላል።

አጥኚዎቹ ቀን ቀን ለደቂቃዎች መተኛት ጠቃሚ መሆኑን ለመጠቆም ምርጥ መላ አበጅተዋል።

ይህ መላ ዘረ-መል ላይ የተመሠረተ ነው።

ከዚህ በፊት የተደረጉት ጥናቶች 97 የዘር-መል ዓይነቶችን ለይተው የትኞቹ የቀን እንቅልፍ ያሻቸዋል? የትኞቹስ ያለ እንቅልፍ ቀናቸውን መግፋት ይችላሉ? የሚለውን ለይተዋል።

የጥናት ቡድኑ ዕድሜያቸው ከ40-69 የሆኑ 35 ሺህ ሰዎች መልምለው ቀን የሚያሸልቡ እና እንቅልፍ የማይበግራቸው ሲሉ ለሁለት ከፈሉ።

ስሊፕ ሄልዝ በተሰኘው መፅሔት ላይ የታተመው የጥናቱ ውጤት እንደሚገልጠው ቀን እንቅልፍ ያገኙ አንጎላቸው በ15 ኪዩቢክ ሴንቲሜትር አድጎ ታየ።

ይህ ማለት ከ2.6 እስካ 6.5 ዓመት ዘግይተው ነው የሚያረጁት ማለት ነው።

“ቅዳሜና እሑድ ቅንጭብ እንቅልፍ ማግኘት እወዳለሁ። ይህ ጥናት ቀን መተኛቴ ስንፍና እንዳልሆነ አሳይቶኛል። አእምሮየን እየጠበቀልኝም ይሆናል” ይላሉ ፕሮፌሰር ታራ ስፓይርስ-ጆንስ።

የኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ መምሕርት እንዲሁም የብሪቲሽ ኒውሮሳይንስ ማሕበር ፕሬዝደንት የሆኑት ፕሮፌሰሯ ጥናቱ እንቅልፍ ለአእምሮ ዕድገት ጠቃሚ መሆኑ ተጨማሪ ማሳያ ነው ይላሉ።

አጥኚዎቹ ምንም እንኳ በቀን የለሊት እንቅልፍን የሚያስንቅ እንቅልፍ ማግኘት ጠቃሚና ጎጂ የሚለውን ባያጠኑም ከግማሽ ሰዓት ባያልፍ የሚል ምክር አላቸው።