ለረጅም ጊዜ ከዕይታ ተሰውሮ የቆየው የአሊባባ መሥራች ጃክ ማ በይፋ ታየ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ለረጅም ጊዜ ከሕዝብ ዕይታ ተሰውሮ የቆየው የአሊባባ መሥራች ጃክ ማ ቻይና ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት መታየቱ ተዘገበ።
ላለፉት ሦስት ዓመታት የት እንዳለ ሳይታወቅ የተለያዩ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሲነገሩበት የቆየው ቻይናዊው ቱጃር ሃንግዡ በተባለችው ከተማ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ነው የታየው።
የ58 ዓመቱ ጃክ ማ ከሦስት ዓመት በፊት የቻይና መንግሥትን የፋይናንስ ደንቦችን ከተቸ በኋላ ከዕይታ እና ከመገናኛ ብዙኃን ርቆ ቆይቶ ነበር።
በዚህም ሳቢያ ከቻይና መንግሥት ጋር በመቃቃሩ አንዳች ነገር ገጥሞት ይሆናል የሚሉ ወሬዎች ሲናፈሱ የነበሩ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያም ስለ ጃክ ማ ከዕይታ መጥፋት በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቆይቷል።
የቻይና መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት ባለፉት ዓመታት ከተሰወሩ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ጃክ ማ ከፍተኛ ተሰሚነት ያለው ቻይናዊ ቢሊየነር ነው።
ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው፣ ማ ከአንድ ዓመት በላይ በውጭ አገር ቆይቶ በቅርቡ ወደ አገሩ ሲመለስ ሆንግ ኮንግ ውስጥ አጭር ቆይታ አድርጓል።
ቀድሞው የእንግሊዝኛ መምህር ጃክ ማ፣ የአሊባባ ተቋም ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝባት ሃንግዡ ውስጥ የሚገኘውን ዩንጉ የተባለውን ትምህርት ቤት እና መምህራንን ሲጎበኝ ነበር ከረጅም ጊዜ መጥፋት በኋላ በይፋ የታየው።
በቻይና ቀዳሚው ቱጃር የነበረው ጃክ ማ፣ አንት ግሩፕ በተባለው የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ግዙፍ ተቋም ላይ የነበረውን ሥልጣን ባለፈው ጥር ወር ለቋል።
ይህንንም በቻይና መንግሥት ሕጎች ላይ በሰነዘረው ትችት የተነሳ ከገዢው ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደሚገኝ ማሳያ ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደማስረጃ ይጠቅሱታል።
ከሦስት ዓመት በፊት በአንድ የፋይናንስ ኮንፈረንስ ላይ መደበኛ ባንኮችን መያዣ በመቀበል ብር ከሚያበድሩ ባሕላዊ አበዳሪዎች ጋር የሚመሳስል አስተሳሰብ አላቸው ብሎ ተችቷቸው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የራሱ የፋይናንስ ኩባንያ ለሽያጭ ሊያቀርበው የነበረው ከ25 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ የአክስዮን ሽያጭ ከጫፍ በደረሰበት ጊዜ በቻይና ባለሥልጣናት ዕቅዱን ሰርዘውበታል።
ከዚያ በኋላ ለረጅም ጊዜ ተሰውሮ የቆየው ማ አውሮፓ ውስጥ እና በሌሎችም አገራት ውስጥ ታይቷል። ከእነዚህም መካከል በስፔን፣ በኔዘርላንድስ፣ በታይላንድ እና በአውስትራሊያ ውስጥ መታየቱ ተነግሯል።
ባለፈው ኅዳር ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ፣ ጃክ ማ ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ ለስድስት ወራት መቆየቱን ዘግቦ ነበር።
ማ መጀመሪያ ላይ ከሕዝብ ዕይታ ርቆ በቆየበት ጊዜ፣ በቁም እስር ላይ ነው ወይም ታስሯል የሚሉ ወሬዎች ሲናፈሱ ቆይተዋል።












