ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብፅ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ ሦስት መንትዮችን ጨምሮ 15 ህጻናት ሞቱ
ባሳለፈው እሁድ በግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሕይወታቸው ካለፈ 41 ሰዎችመካከል ቢያንስ 15ቱ ህጻናት መሆናቸው ተገለጸ።
በአደጋው ቤተክርስቲያኒቱ የተሰበሰቡ ህጻናት እና ወላጆቻቸውን ጨምሮ ከ 41 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግቧል።
የካይሮ ከተማ አካል በሆነችው እና ጊዛ ተብላ በምትጠራው አካባቢ በተለይም ሰርቶ አዳሪ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል በሚገኝበት እምባባ በተሰኘው ክፍል የሚገኘው የአቡ ሰፌይን ቤተ ክርስቲያን ላይ ነበር አደጋው የተከሰተው።
ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቅዳሴን ከሚከታተሉት ህጻናት በሻገር፣ ሌሎች በርካታ ህጻናት በቤተክርስቲያኑ አንደኛ ፎቅ ላይ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነበር።
መርማሪዎች በኤሌክትሪክ መስመሮች ችግር ምክንያት የተነሳው የእሳት ቃጠሎ የጀመረውም በዚሁ የመጀመሪያው ወለል ላይ እንደሆነ ያምናሉ።
የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ አብዛኛው ህልፈት የተከሰተው በጭስ በመታፈን ብሎም መውጫ በሮች ተዘግተው ባሉበት ሰዎች ለመውጣት ባደረጉት ጥረት ወቅት በተፈጠረ መረጋገጥ ነው።
በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡ ህጻናት መካከል የአምስት ዓመት እድሜ ያላቸው ሦስት መንትዮች የነበሩት ሞሃሬል፣ የሱፍ እና ፊሎፓተር ባሴም አሚር ይገኙበታል።
የህጻናቱ ዘመዶች፣ የቤተክርስቲያኑ ባለሥልጣናት፣ በአካባቢው የሚገኝ ሆስፒታልን በማጣቀስ የግብፅ የዜና ማሰራጫዎች የህጻናቱን ሕልፈት ዘግበዋል።
ህጻናቶቹ ከእነሱ ባሻገር የ34 ዓመቷ እናታቸው ኢሪና አተፍ ራምዚ፣ 61 ዓመቷ አያታቸው ማክዳ ሀቢብ ነቢህ እና የ25 ዓመቷ አክስታቸው ሚርና አተፍ ራምዚ በአደጋው ሕይታቸውን አጥተዋል።
የሟቾች የቅርብ የሥጋ ዘመድ የሆነችው እና ሙዚቀኛዋ ሚሬቲያ ኢማድ በፌስቡክ ገጿ ላይ በፃፈችው ፅሁፎች ሐዘኗን ገልጻለች።
"ከክርስቶስ ጋር ይህ እጅግ የሚሻል ነውና በጸጋው ዙፋን ፊት አስበን" ስትል ጽፋለች። "አሁን በሰማይ ስድስት ቅዱሳን አሉኝ" ስትል ሐዘኗን ገልጻለች።