ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብፅ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በደረሰ ቃጠሎ 41 ሰዎች ሞቱ
በግብፅ ጊዛ ከተማ በሚገኝ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።
በእሳት አደጋው ሕይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ደግሞ ከእሳት አደጋው ለማምለጥ በተደረገ ጥረት ተረጋግጠው መጎዳታቸው ተገልጿል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሟቾች ቁጥር 41 የደረሰ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል ህጻናት እንደሚገኙበት ይታመናል።
በጊዛ በሚገኘው አቡ ሲፊን በተሰኘው የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን 5 ሺህ ምዕመናን ለአምልኮ በተሰበሰቡበት ወቅት ነው አደጋው የተከሰተው።
በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ባሉ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ በተነሳ የእሳት ሳቢያ አደጋው መከሰቱን የደኅንነት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
አክለውም የእሳት አደጋው መውጫ በሮችን በመዝጋቱ ለመረጋገጡ እና ለሟቾች ቁጥር ከፍ ማለት ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።
የሆስፒታል ምንጮችን ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው እድሜያቸው ከ3 እስከ 16 ዓመት መካከል የሆኑ 18 ሕጻናት በአደጋው ሕይወታቸውን አጥተዋል።
የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንደገለፁት የእሳቱ ትክክለኛ መንስኤ እስካሁን አልታወቀም። ነገር ግን አደጋው ባጋጠማት ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኝ ሌላ ቤተ ክርስቲያን አባት የሆኑት አባ ፋሪድ ፋህሚ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት እሳቱ በኤሌክትሪክ መስመር ችግር ምክንያት የተከሰተ ነው።
"መብራት ጠፍቶ ስለነበር ጄኔሬተር እየተጠቀሙ ነበር። ነገር ግን መብራት ተመልሶ ሲመጣ ከመጠን በላይ ጫና ተፈጠረ" ሲሉ ተናግረዋል።
"ሰዎች በሦስተኛው እና በአራተኛው ወለል ላይ እየተሰበሰቡ ነበር። ከሁለተኛው ፎቅ አካባቢ ጭስ ሲወጣ ተመለከትን። ሰዎች ወደ ታች ለመውረድ ሲጣደፉ እርስ በእርሳቸው መረጋገጥ ጀመሩ" ሲል ያሲር ሙኒር የተሰኘ የዐይን እማኝ ለሮይተርስ ተናግሯል።
"ከዚያም ጩኸት ሰማን፣ እሳት በመስኮት ሲወጣ አየን" ያለው የዐይን እማኙ፣ እሱና ሴት ልጁ ምድር ቤት ላይ ስለነበሩ ማምለጥ እንደቻሉ ተናግሯል።
አደጋውን ተከትሎ የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ "በአምልኮ ላይ ሳሉ ሕይወታቸውን ላጡ እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው ልባዊ ሐዘኔን እገልጻለሁ" ብለዋል።
የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ቤተክርስቲያኑን መልሰው እንዲገነቡም ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም የቃጠሎውን መንስኤ የሚያጣራ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን አስታውቋል።
ጊዛ ከካይሮ ከአባይ ወንዝ ማዶ የምትገኝ እና የካይሮ ከተማ አካል ነች። ግብፅ ካላት 103 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ቢያንስ 10 ሚሊዮኑ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ናቸው።
የኮፕቲክ ኦርቶዶክሶች በግብፅ መድልዎ እንደሚደርስባቸው እና በግብፅ ውስጥ ከቁጥራቸው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቦታ እንዳላቸው ይናገራሉ።