የኬንያ መንግሥት “ሐሰተኛ” ያላቸውን በርካታ ተከታይ ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ፍቃድ ሰረዘ

መስቀል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያ መንግሥት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “ከእየሱስ ጋር ለመገናኘት” ሲሉ እራሳቸውን አስረበው መሞታቸውን ተከትሎ “ሐሰተኛ” ያላቸውን ቤተ-ክርስቲያናት ፍቃድ መሰረዝ ጀመረ።

የአገሪቱ መንግሥት የአምስት አብያተ ክርስቲያናት ፍቃድን የሰረዘ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከ400 ሰዎች ሞት ጋር ስሙ የሚያያዘው “ዘ ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቸርች” ይገኝበታል።

የዚህ ቤተ-ክርስቲያና መሪ ነኝ የሚል ግለሰብ ለተከታዮቹ “የዓለም ፍጻሜ ተቃርቧል እየጾማችሁ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትን ጠብቁ” ካላቸው በኋላ ከ400 የማያንሱ ተከታዮቹ እራሳቸውን ነጥለው ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ ጾመው ሲጸልዩ ነበረ ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኘው ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ የተባለ የኃይማኖት ሰባኪ ለተከታዮቹ ‘ኢየሱስን ማግኘት’ ከፈለጉ እራሳቸውን እንዲያስርቡ ነግሯቸዋል ተብሏል። ተከታዮቹም በተነገራቸው መሠረት የተባሉትን ካደረጉ በኋላ በረሃብ ሕይወታቸው አልፏል።

በአሁኑ ወቅት ከ40ሺህ ያላነሱ ሐይማኖታቸዊ ተቋማት በኬንያ የሚገኙ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት “ከእየሱስ ጋር እንድትገኛኙ ጾማችሁ ጸልዩ” የተባሉ ክርስቲያኞች በረሃም ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የኬንያ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቷል።

ለመንፈሳዊ ተቋማት ፍቃድ የሚሰጠው መንግሥታዊ ተቋም ለዚህ ቤተክርስቲያን እና “ኒው ላይፍ ፕረየር ሴንተር” ለተባለ ሌላ ታዋቂ ቤተ-ክርስቲያን የሰጠውን ፍቃድ መሰረዙን ይፋ አድርጓል።

“ኪንግስ አውትሪች ቸርች” እንዲሁም “ሄሊኮፕተር ኦፍ ክራይስት ቸርች” ቀሪ ሁለት ብዙ ተከታዮች የነበሯቸው ፍቃዳቸው የተሰረዘ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

ይሁን እንጂ የአብየተ ክርስቲያናቱ ጠበቆች መንግሥት በክርስትና እምነት ላይ ጦርነት ከፍቷል ሲሉ እርምጃውን ተቃውመዋል።

ጠበቃ ዳንስታን ኦማሪ ውሳኔውን በመቃውም ጉዳዩን ወደ አገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ገልጸው መንግሥት በኃይማኖታዊ ጉዳዮች ጣልቃ መግባት አንደማይችልም ብለዋል።

ጠበቃው የመንግሥት ውሳኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ተከታዮችን መብት የሚጋፋ ነው ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

በኬንያም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገራት ከእንዲህ አይነት የእምነት ሰባኪያን ምክር ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ የጾም እና ሌሎች ትዕዛዞች ምክንያት ምዕመናን በተለያዩ ጉዳት ሲደርስባቸው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከጥቂት ወራት በፊት ሞዛምቢክ ውስጥ አንድ ፓስተር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀን እና ሌሊት እጾማለሁ ብሎ በመሞከሩ ክፉኛ ተጎድቶ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ለሕልፈት መብቃቱ ይታወሳል።