እስራኤል ሄዝቦላህን ይደግፋሉ ያለቻቸውን የሊባኖስን ባንኮች በአየር ደበደበች

በሊባኖስ የደረሰው የአየር ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, REX/Shutterstock

እስራኤል ሄዝቦላህን ይደግፋሉ ያለቻቸውን በመዲናዋ ቤይሩት እንዲሁም በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ባንኮች ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች።

በአየር ጥቃቱ በቤይሩት ዳሂየህ ወረዳ እንዲሁም በደቡባዊ ሊባኖስ ቤካ ሸለቆ ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰምቷል።

እነዚህ ስፍራዎች ሄዝቦላህ የሚቆጣጠራቸው ናቸው ተብሏል። የአየር ጥቃቶቹን ተከትሎ በደረሱ ፍንዳታዎች በሰዎች ሕይወት ላይ ጉዳት ስለማድረሱ እስካሁን አልተገለጸም።

የእስራኤል ጦር በቤይሩት 14 ሰፈሮችን ጨምሮ በመላዋ ሊባኖስ በ25 ስፍራዎች ላይ ሌሊቱን ሙሉ የአየር ጥቃት እንደሚፈጽም ቀደም ሲል አስጠንቅቆ ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ሄዝቦላህን የሚደግፉ ባንኮችን እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፎችን ዒላማ አደርጋለሁ ብሏል።

“የሄዝቦላህ የሽብር ተግባራትን ለመደገፍ ጥቅም ላይ ከሚውሉ አካባቢዎች አጠገብ ያሉ ማንኛውም ነዋሪዎች ከእነዚህ ስፍራዎች መራቅ አለባቸው” ሲሉ የእስራኤል መከላከያ ቃለ አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ እሁድ ምሽት አስጠንቅቀው ነበር።

“በሚቀጥሉት ሰዓታት በርካታ ዒላማዎችን እንዲሁም ሙሉ ሌሊቱን ተጨማሪ ስፍራዎች ላይ ጥቃት እንፈጽማለን” ብለው ነበር።

ቃለ አቀባዩ አክለውም “በሚቀጥሉት ቀናት ኢራን የሲቪል ተቋማትን፣ ማኅበራትን እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሽፋን በማድረግ የሄዝቦላህ የሽብር ተግባራትን እንዴት ድጋፍ እንደምታደርግ እናሳውቃለን” ሲሉ ገልጸዋል።

በቤካ የሚገኙ አልቃርድ አል ሐሰን አሶሲዬሽን የተሰኘው ባንክ ቅርንጫፎች በአየር ጥቃቱ እንደተመቱ የሊባኖስ መንግሥታዊ የዜና ወኪል ኤንኤንኤ ዘግቧል።

በዋና ከተማዋ ቤይሩት ራፊቅ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የሚገኘው የባንኩ ቅርንጫፍ በአየር መደብደቡንም የዜና ተቋሙ አክሎ ዘግቧል።

በአውሮፕላን ማረፊያው አካባባቢ የደረሰውን ፍንዳታ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

ባንኩ በመላው ሊባኖስ ከ30 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ 15ቱ ሕዝብ በሚበዛባቸው የቤይሩት አካባቢዎች እንደሚገኙ ሮይተርስ ገልጿል።

እስራኤል ባንኩን የኢራንን ገንዘብ ለጦር መሳሪያ ግዢ፣ ማከማቻ እንዲሁም የሄዝቦላህን ታጣቂዎች ደመወዝ ለመክፈል ይጠቀማል ስትል ትከሰዋለች።

አሜሪካ በተጨማሪም ሄዝቦላህ ባንኩን ገንዘቡን ለመቆጣጠር ይጠቀምበታል ትላለች።

በተያያዘ ዜና ሄዝቦላህ እሁድ ዕለት ወደ እስራኤል ባስወነጨፋቸው ሮኬቶች ወታደራዊ የጦር ሰፈሮችን ዒላማ ማድረጉን ገልጿል። በተጨማሪም ደቡባዊ ሊባኖስን ወረው ባሉ የእስራኤል ወታደሮች ላይም ሮኬት ማስወንጨፉን ተነግሯል።