የመረጃ ልውውጥን ለማቀላጠፍ የዳታ ማዕከላትን በምህዋር እና በጨረቃ ላይ የማስቀመጥ ዕቅድ

ሃሳቡ ከሳይንስ ልብ ወለድ ፊልም ላይ የተቀዳ ይመስላል።

ስቴፈን ኢሴሌ ግን አንድ ቀን ኩባንያው በጨረቃ ላይ የመረጃ ማዕከል እንደሚከፍት እርግጠኛ ነው።

የሎኔስታር ዳታ ሆልዲንግስ ፕሬዝደንት "የመረጃ ማዕከሉን በህዋ ላይ በማስቀመጥ ተገዳዳሪ የሌለው ደኅንነት እየሰጠን እንደሆነ ነው የሚታየን" ብለዋል።

ባለፈው ወር በፍሎሪዳ የሚገኘው ድርጅት ከአሜሪካው የጠፈር ምርምር ድርጅት፣ አቴና ሉናር ላንደር ጋር በመሆን መጽሐፍ የምታክል አነስተኛ የመረጃ ማዕከልን ወደ ጨረቃ በማጓጓዝ የተሳካ ሙከራ ማድረጉን ገልጿል።

የመረጃ ቋቶቹ ድረገጾች፣ ኩባንያዎች እና መንግሥታት የሚጠቀሙባቸውን መረጃዎች የሚያከማቹ እና የሚያሳልጡ ኮምፒውተሮችን የሚያይዙ ሰፊ መጋዘኖች ናቸው።

ሎንስታር እነዚህን የመረጃ ቋቶች በጨረቃ ላይ ማስቀመጥ ከፀሐይ ብርሃን የሚያገኙትን ኃይል እየተጠቀሙ ደንበኞች ያልተገደበ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የመረጃ ፍሰት ማግኘት ያስችላቸዋል ብሏል።

በህዋ ላይ የተመሠረቱ የመረጃ ማዕከሎች በጣም ሩቅ ቢመስሉም፣ አሁን ግን በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ቅቡልነት እያገኙ መጥተዋል።

ተቀባይነት እያገኙ ከመጡባቸው ምክንያቶች መካከል ወደ ህዋ ለመብረር ያለው ፍላጎት እየጨመረ መሄድ እና በምድር ላይ ተስማሚ ቦታዎችን ማግኘት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱ ነው።

በዓለማችን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም፣ መረጃዎችን ለመቀመር የሚያስፈልገው ዳታ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቷል።

በዚህም ምክንያት የመረጃ ማዕከላት ፍላጎትም ከፍ ብሏል።

በ2030 የሚኖረው ዓመታዊ ፍላጐት በ19 በመቶ እና 22 በመቶ መካከል እንደሚጨምር ማኪንሴይ የተባለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት አስታውቋል።

በዚህ የዳታ ማዕከል ግንባታ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ አዳዲስ ተቋማት በየጊዜው እየተከፈቱ ነው።

ተቋማቱ የሚከፈቱበትን ቦታ ማግኘት ግን አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።

የመረጃ ማዕከሎቹ ግዙፍ እና የተንጣለሉ ናቸው። ለማንሳቀስ እና ለማቀዝቀዝ ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ ኃይል እና ውሃ ይጠቀማሉ።

እናም ነዋሪዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው አቅራቢያ እንዲገነቡ አይፈልጉም።

የመረጃ ማዕከሎችን በህዋ ላይ፣ በመሬት ዙሪያ ምህዋር ወይም በጨረቃ ላይ ማስቀመጥ፣ የሚለው ሃሳብ ጉዳት ሊያደርሱ አይችሉም የሚለውን ይነግረናል።

በቀዳሚነት ከፀሐይ ያልተገደበ ኃይል የማግኘት ዕድል አለ። በመቀጠል ደግሞ አካባቢ ላይ ስለሚያደርሰው ተጽእኖ የሚያማርር ጎረቤትም አይኖርም።

ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በጠፈር ላይ የሚከፈቱ የመረጃ ማዕከሎች ለጠፈር መንኮራኩር እና ለሌሎች የጠፈር መገልገያዎች መረጃን በማቅረብ ሊያገለግሉ ይችላሉ።

ከመሬት ይልቅ ከህዋ ወደ መሬት መረጃን በፍጥነት መላክ ይቻላል።

ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ኮሚሽን የገንዘብ ድጋፍ በምህዋር ላይ ስለሚቀመጡ የዳታ ማዕከሎች ላይ የተሠራው የአዋጭነት ጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል።

በፈረንሳይ እና በጣልያን ኤሮስፔስ ቡድኖች የተቋቋመው ታሌስ እና ሊዮናርዶ በጋራ ያቋቋሙት ወደ ህዋ ለመብረር የሚያስችለው ጥናት ውጤትም ታትሟል።

ጥናቱ የዳታ ማዕከሎችን በጠፈር ላይ ማስቀመጥ "የአውሮፓን ዲጂታል መልክዓ ምድር ሊለውጥ ይችላል" እንዲሁም "የበለጠ ለአካባቢ ተስማሚ" እንደሚሆን ገልጿል።

ታልስ አሌኒያ ስፔስ 200 ሜትር በ80 ሜትር የሚሆኑ 13 ሳተላይቶች ለመገንባት አቅዷል።

ይህም ወደ 10 ሜጋ ዋት መረጃን ማስተላለፍ ያስችላል።

አሁን መሬት ላይ ካለው የመረጃ ማዕከል ጋር ሲነጻጸር ደግሞ መካከለኛ መጠን እና 5,000 የሚያህሉ ሰርቨሮች ካሉት ማዕከል ጋር እኩል ነው።

ሳተላይቶቹ የሚገጣጠሙት ቀደም ሲል በነበሩ ወይም በመገንባት ላይ ባሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ በመመሥረት ይሆናል።

በታሌስ አሌኒያ ስፔስ የምህንድስና ባለሙያ የሆኑት ዴሚየን ዱሜስቲየር፣ በህዋ ላይ የመረጃ ቋቶችን ለማኖር የሚሠሩ ድርጅቶች አሁን መሬት ላይ ካሉት በበለጠ ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ እንዲሆኑ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን በሕይወት ዘመናቸው በ10 እጥፍ ያነሰ ልቀት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ይህ ደግሞ የሚቻል ይመስላል ይላሉ መሃንዲሱ።

ይኹን እንጂ፣ ቴክኖሎጂውን ለማዳበር ዓላማ ያላቸው ኩባንያዎች ተስፋ ቢያደርጉም፣ በዩናይትድ ኪንግደም የአንግሊያ ራስኪን ዩኒቨርሲቲ የመረጃ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ዶሜኒኮ ቪኪናንዛ በጠፈር ላይ የሚቀመጡ የመረጃ ማዕከላት አዋጭ ሐሳብ ከመሆናቸው በፊት ብዙ ትልልቅ መሰናክሎች እንዳሉባቸው ይናገራሉ።

"እንደ ስፔስ ኤክስ (SpaceX) ባሉ ኩባንያዎች አስተዋፅዖ እንኳን ሃርድዌርን ወደ ኦርቢት ማስወንጨፍ በጣም ውድ ነው" ይላሉ።

"ወደ ህዋ የሚላክ እያንዳንዱ ኪሎ ግራም በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ያስወጣል።"

"በስፔስ ላይ የሚቋቋሙ የመረጃ ማዕከላት ለመጠበቅ፣ ኃይል ለማቅረብ እና ለማቀዝቀዝ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ያስፈልጋል። ሁሉም ክብደት እና ውስብስብነት ይጨምራሉ።"

መሳሪያውን ማቀዝቀዝ ራሱን የቻለ ችግር ይሆናል። ምክንያቱም ቦታው ቀዝቃዛ ቢሆንም፣ የተለመደው የማቀዝቀዣ ዘዴዎች ያለ ስበት አይሠራም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የጠፈር አየር ጠባይ ኤሌክትሮኒክስን ሊጎዳ ይችላል፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው የህዋ ቁሳቁስ ስብርባሪ ሃርድዌሮችን አደጋ ላይ ይጥላል።

ዶክተር ቪሲናንዛ "በምህዋሩ ላይ ችግሮች ሲከሰቱ ጥገና ማድረግ ቀላል አይሆንም። በሮቦቲክስ እና አውቶሜሽን እንኳን ቢሆን ከርቀት ለመጠገን መሰናክል የሚሆኑ ነገሮች አሉ። ትልቅ የሃርድዌር ብልሽት ውድ የሆነ ወጪን አስወጥቶ ሰውን ወደ ህዋ መላክ ሊጠይቅ ይችላል። ይህም ለሳምንታት ወይም ለወራት የሚፈለገውን መረጃ ሊያስተጓጉል ይችላል" ብለዋል።

ሆኖም እንደ ሎንስታር ያሉ ኩባንያዎች በህዋ ላይ ስለሚቀመጡ የመረጃ ማዕከላት እጅግ በጣም እርግጠኛ ከመሆን ባሻገር፣ ላለው ፍላጎት ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ሚስተር ስኮት "ደንበኞቹ ባይጠይቁን ይህን አናደርግም ነበር" ብሏል።

ቀጣዩ ዕቅድ በ2027 በጨረቃ ዙሪያ ትንሽ የመረጃ ማዕከልን ማስቀመጥ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች ኩባንያዎች ይህንን በፍጥነት ይቀላቀላሉ ተብሎ ይታመናል።

ዋሽንግተን መቀመጫውን ያደረገው ስታርክሎድ በሚቀጥለው ወር በሳተላይት ላይ የተመሠረተ የመረጃ ማዕከልን ለመጀመር አቅዷል።

የሎኔስታሩ ኢዴሌ በህዋ ላይ የዳታ ማዕከል የሚከፍቱ ተቋማት ለመንግሥታት እና በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች የበለጠ ደኅንነቱ የተሟላ አግልግሎትን የሚያቀርቡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ይህም የሚሆነው መረጃዎቻቸው ምድር ላይ በተዘረጋ ኔትወርኮች መተላለፍ ስለማያስፈልጋቸው ነው ብለዋል።

ይልቁንስ መረጃው በቀጥታ ከጠፈር መሬት ላይ ወደ ተተከለ ጣቢያ በቀጥታ ሊተላለፍ ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም መረጃ ለመመንተፍም በጣም ከባድ መሆኑን በመግለጽ፣ ". . . በቀላሉ ሰብሮ ለመግባት አይታሰብም" ብለዋል።

ከጨረቃ ወደ መሬት መረጃ ለመድረስ አንድ ሰከንድ ተኩል ያህል ብቻ ጊዜ ይወስድበታል። ይህ ለአንዳንድ መተግበሪያዎች ምንም ለውጥ አያመጣም ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የሎንስታር መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክሪስ ስቶት፣ በህዋ ላይ የተመሠረቱ የመረጃ ማዕከላት ድርጅቶች የዳታ ሉዓላዊነት ሕጎችን ማየት እንደሚኖርባቸው ያሳስባሉ።

"በህዋ ሕግ መሠረት በህዋ ላይ የሚገኘው የኤሌክትሮኒክስ ሳጥን፣ በፈቃድ ሰጪው ወይም በአስወንጫፊው መንግሥት ሕግ ስር ነው - እሱ በህዋ ላይ ያለ ኤምባሲ ነው" ይላሉ።