ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለኢንተርኔት ጅማሬ ምክንያት የሆነው ከ50 ዓመታት በፊት ያጋጠመው ግንኙነት መቋረጥ
ጥቅምት 29 ቀን 1969 ሁለት ሳይንቲስቶች 563 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ ኮምፒውተሮች መካከል ግንኙነት ፈጠሩ። መልዕክት እየተየቡም መላላክ ጀመሩ። በመሃል ላይ ግን አምቢ አለ። ሁለቱ ሳይንቲስቶች ከ55 ዓመታት በኋላ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ቻርሊ ክላይን እና ቢል ዱቫል በቴክኖሎጂው ዘርፍ እጅግ በጣም ትልቅ ከሚባሉ ምርምሮች ቀዳሚ የሚባለውን የሚመሩ መሐንዲሶች ነበሩ።
ክላይን ከካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ዩኒቨርስቲ (ዩሲኤልኤ) የተመረቀ 21 ዓመት ወጣት ነበር። የ29 ዓመቱ ዱቫል ደግሞ በስታንፎርድ ሪሰርች ኢንስቲትዩት (ኤስአርአይ) የሲስተም ፕሮግራመር ነበር። ሁለቱም አድቫንስድ ሪሰርች ፕሮጀክትስ ኤጀንሲ ኔትዎርክ ወይም በምጻረ ቃል አርፓኔት በሚባል ሥርዓት ላይ ይሠሩ ነበር።
ይህ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ደግሞ በአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ነበር። ፕሮጀክቱ ከስልክ መስመር ውጪ መረጃን በቀጥታ የሚያጋራ ኔትዎርክ ለመፍጠር ያለመ ነው። ይህ አሠራር ለዘመናዊው ኢንተርኔት መሠረት የሆነውን "ፓኬት ስዊቺንግ" የሚባለውን የመረጃ አሰጣጥ ዘዴ አስተዋውቋል።
የሰው ልጅን በአዲስ መልክ የሚቀይር የቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ለመሥራት ከመቻሉ በፊት ግን መመዝገብ ያስፈልጋል።
ክላይን በዩሲኤልኤ መማሪያ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ ዱቫል ደግሞ በካሊፎርኒያ ግዛት አጋማሽ በሚገኝ ስፍራ በኮምፒውተር ላይ እየሠራ ነበር። ክላይን ተመዝገብ የሚለውን ትዕዛዝ ከመፈጸሙ በፊት ዱቫል ደውሎ ሥርዓቱ መበላሸቱን ነገረው። ለዚያ ስህተት ምስጋና ይግባውና እአአ በ1969 ክላይን ለዱቫልን የላከው የመጀመሪያው "መልዕክት" "ኤል-ኦ ( L-O)" የሚሉ ፊደላት ብቻ ናቸው።
ከአንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገው ከአንድ ሰዓት በኋላ ግንኙነታቸውን መልሰው ጀምሩ። ያ የመጀመሪያ ብልሽት ለሌላ ትልቅ ስኬት መንገድ የጠረገ ነበር።
ሁለቱም ባለሙያዎች የሥራቸውን አስፈላጊነት አልተገነዘቡትም ነበር። ክላይን "በእርግጠኝነት በዚያ መልኩ አልተረዳሁም ነበር። ብቻ እንዲሠራ ለማድረግ እየሞከርን ነበር" ብሏል።
የዚህን አጋጣሚ 55ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ቢቢሲ ክላይንን እና ዱቫልን አነጋግሯል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በይነ መረብ መላው ዓለምን በኪስ ውስጥ ወደ ምትገባ ትንሽ ነገርነት ቀይሯታል። ይህም የሰው ልጅን ትኩረት የሚቆጣጠር እና የሕይወት ልምዳችንን የሚነካ ሆኗል።
ቢቢሲ፡ አርፓኔትን ያስጀመሩ ኮምፒውተሮችን መግለጽ ይችላሉ? እነዚህ ግዙፍ እና የሚጮሁ ኮምፒውተሮች ነበሩ?
ክላይን፡ በወቅቱ መመዘኛዎች ማቀዝቀዣ የሚያክሉ ትናንሽ ኮምፒውተሮች ነበሩ። ከማቀዝቀዣው የሚወጣ የተወሰነ ድምጽ ነበራቸው። ከሲግማ 7 ኮምፒውተር ጋር ሲነጻጸሩ የሚያሰሙት ድምጽ የለም ማለት ይቻላል። ከፊት በኩል ብልጭ ድርግም የሚሉ መብራቶች፣ አይኤምፒ (ኢንተርፌስ ሜሴጅ ፕሮሰሰርን) የሚቆጣጠሩ ማብሪያ ማጥፊያዎች እና ሶፍትዌሩን ለመጫን የሚያገለግል የወረቀት ቴፕ አንባቢ ነበራቸው።
ዱቫል: ዛሬ ትልቅ የድምጽ ማጉያዎችን ለመያዝ በሚያስችል ትልቅ መደርደሪያ ላይ ነበሩ። በአፕል ዋች ውስጥ ካለው ፕሮሰሰር በሚሊዮን ወይም በቢሊዮን እኳን ባይሆን በሺዎች በሚቆጠሩ ጊዜ ያነሱ ነበሩ። እነዚህ የድሮ ዘመን ላይ የነበሩት ናቸው!
ቢቢሲ፡ ኡል-ኦ እያላችሁ ለመተየብ ስትጀምሩ ወደ ነበረበት ቅጽበት እስቲ መልሱን
ክላይን፡ ከበይነ መረብ እና ከሌሎች ሥርዓቶች በተለየ መልኩ ከኤስአርአይ ሥርዓት ጋር ሲገናኙ የሆነ ነገር እስኪተይቡ ድረስ ምንም ነገር አይፈጠረም። ፕሮግራም ማስጀመር ከፈለጉ መጀመሪያ መመዝገብ ያስፈልጋል። ለመግባት ደግሞ “login" የሚለውን ቃል መተየብ ያስፈልጋል። ቀጥሎም ሥርዓቱ የተጠቃሚው ስም እና የይለፍ ቃል ይጠይቃል።
ከእኔ የቴሌታይፕ ሞዴል 33 ኮምፒውተር ላይ አንድ ሆሄ ስተይብ ወደ ኤስዲኤስ ሲግማ 7 ኮምፒዩተር ይላካል። ያ ፕሮግራም ፊደሉን ወስዶ ወደ መልዕክት ይቀርጸዋል። በመቀጠልም ወደ በይነገጽ መልዕክት ፕሮሰሰር ይልካል። ኤስአርአይ ሲስተም ላይ ሲደርስ፣ [መልዕክቱን] ከአካባቢው ኮምፒውተር እንደመጣ በማድረግ ያስተናግደዋል። ፊደሉን “በማስተጋባት” ይደግመዋል። የቢል ኮድ ያንን ፊደል ወስዶ ወደ መልዕክት ይቅረዋል። በኋላም ወደ አይኤምፒ ልኮ ወደ ዩሲኤከልኤ ይመለሳል። ስቀበል ኮምፒውተሩ ላይ አትመዋለሁ።
ይህንን ስንሞክር ከቢል ጋር ስልክ እያወራሁ ነበር። ኤል የሚለውን ፊደል እንደጻፍኩ ነገርኩት። እሱም እንደረሰው እና መልሶ እንደላከልኝ ነገረኝ። እኔም እንደታተመ ነገርኩት። ከዚያም ኦ የሚለውን ፊደል ጻፍኩ። ይህም በትክክል ሠርቷል። ጂ የሚለውንም ጻፍኩኝ። የእሱ ሲስተም መበላሸቱን እና መልሶ እንደሚደውል ቢል ነገረኝ።
ዱቫል፡ የዩሲኤልኤ ኮምፒውተር ቻርሊ L- O ን ከተየበ በኋላ G-I-Nን እቀበላለሁ ብሎ አልጠበቀም። በዚህ ምክንያትም ወደ ኤስአርአይ ኮምፒዩተር የስህተት መልዕክት ልኳል። መልዕክቱ ምን እንደነበረ በትክክል ባላስታውስም ግን ከዚያ በኋላ የተከሰተው የአውታረ መረብ ግንኙነት ከዚህ በፊት ከታዩት ሁሉ በጣም ፈጣን በመሆኑ ነው።
የነበረው የግንኙነት ፍጥነት በሰከንድ 10 ፊደላትን የሚያስተላልፍ ነበር። አርፓኔት ግን በሰከንድ እስከ 5 ሺህ ፊደላትን ማስተላለፍ ይችላል። ይህ መልዕክት ከዩሲኤልኤ ወደ ኤስአርአይ ኮምፒዩተር የተላከው አጥለቅልቆታል። አንድን ብርጭቆ በእሳት እንደ መሙላት ነበር። ምን እንደተፈጠረ በፍጥነት በመረዳት የመቀበያውን መጠን ቀይሬ ሥርዓቱን እንደገና ገነባሁ። ይህም አንድ ሰዓት ያህል ፈጅቷል።
ቢቢሲ፡ ይህ ታሪካዊ ወቅት ሊሆን እንደሚችል ተረድታችሁ ነበር?
ክላይን: አይ በእርግጠኝነት ያን ጊዜ አንደዚያ አላሰብኩም።
ዱቫል: አይደለም። በኤስአርአይ ውስጥ በምንሠራው ሥራ ትልቅ እርምጃ ነበር። ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለን ያመንነው።
ቢቢሲ፡ ሳሙኤል ሞርስ በ1844 የመጀመሪያውን የቴሌግራፍ መልዕክት ሲልክ “የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ” የሚል መልዕክት አስተላልፎ ነበር። ወደ ኋላ መመለስ ብትችሉ በተመሳሳይ የማይረሳ ነገር ትተይቡ ነበር?
ክላይን: አስፈላጊነቱን ብገነዘብ በትክክል አደርገው ነበር። እኛ ግን እንዲሠራ ለማድረግ እየሞከርን ነበር።
ዱቫል፡ አይሆንም። ይህ በጣም ብዙ ተንቀሳቃሽ ክፍሎች ያሉት የመጀመሪያው የተወሳሰበ ሥርዓት ፈተና ነበር። ይህንን ውስብስብ ሥራ በመጀመሪያው ሙከራ ማግኘት በራሱ አስደናቂ ነበር።
ቢቢሲ፡ መልዕክቱ ሲላክ የነበረው ድባብ ምን ይመስል ነበር?
ዱቫል፡ ሁለታችንም በምሽት በየራሳችን የኮምፒውተር ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ብቻችንን ነበርን። ሁለታችንም ለአድካሚው ሥራ የመጀመሪያ ሙከራ መፍትሄ በማግኘታችን ደስ ብሎናል። በአካባቢው ወደሚገኝ መዝናኛ አምርቼ በርገር በልቼ ቢራ ጠጣሁ።
ክላይን: በመሥራቱ ደስተኛ ስለነበርኩ ትንሽ ለመተኛት ወደ ቤት ሄድኩኝ።
ቢቢሲ፡ አርፓኔት ምን እንዲሆን ጠብቃችሁ ነበር?
ዱቫል፡- በኤስአርአይ የምንሠራውን ሥራ እንደ አንድ ትልቅ ራዕይ ነበረው። የኢንፎርሜሽን ባለሙያዎች እርስ በርስ ተገናኝተው ችግሮችን፣ ምልከታዎችን፣ ሰነዶችን እና መፍትሄዎችን የሚለዋወጡበት ወሳኝ አካል አድርጌ ነበር ያየሁት። ያላሰብነው ነገር በንግድ ዘርፍ ወይም የማኅበራዊ ሚዲያን ክስተት እና ተዛምደው የመጡትን የሐሰት መረጃ ሥርጭቶች ነበር። [የኤስአይ ኮምፒውተር ሳይንቲስት] ዳግላስ ኢንግልባርት እአአ በ1962 አጠቃላይ ራዕዩ በሕብረተሰቡ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ችግሮች ለመፍታት እየተፈጠረ ነበር ብሏል።
ቢቢሲ፡ ከዛሬው በይነ መረብ ስለ አርፓኔት የሚያስታውሱት ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?
ዱቫል፡ በኤንግልባርት ቡድን ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ትልቁን ራዕይ በመጥቀስ የዛሬው በይነመረብ ብዙ ብሩህ የተሻሻለ ሃሳቦች ለውጥ አካል ነው።
ክላይን: የሌሎችን ሃብቶች የመጠቀም ችሎታው። ድረ ገጽ ስንጠቀም የምናደርገው ይህንኑ ነው። አርፓኔት ከአንድ ጣቢያ ወደ ሌላ የማዘዋወር እና በርካታ መንገዶችን ፅንሰ ሃሳብ ፈጠረ። ብዙ መንገዶችን በአንድ ጊዜ በመጠቀም የግንኙነት ፍጥነትን መጨመር አስችሏል። እነዚህ ጽንሰ-ሐሳቦች ወደ በይነመረብ ተላልፈዋል።
ለአርፓኔት የግንኙነት ፕሮቶኮሎችን ስናዘጋጅ የተለያዩ ችግሮችን አግኝተናል። ፕሮቶኮሎቹን አሻሽለናል፤ ወደ ኢንተርኔት የተላለፉ ብዙ ትምህርቶችን አግኝተናል።
ቢቢሲ፡ ስለ 55ኛ ዓመቱ ምን ይሰማችኋል?
ክሊን፡ ድብልቅ ስሜት አለው። በግሌ አስፈላጊ እንደሆነ ቢሰማኝም ትንሽ ግን ከመጠን በላይ ሆኗል። አርፓኔት እና ከእሱ የመነጩት ነገሮች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ለእኔ ይህ ልዩ በዓል ከብዙ ጉዳዮች አንዱ ነው።
ዱቫል፡ ኢንተርኔትን የመሰለውን ነገር አመጣጡን ማስታወስ ጥሩ ቢሆንም፣ በጣም አስፈላጊው ነገር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰቡ ዋና አካል ወደሆነው ለመቀየር የተሠራው እጅግ በጣም ብዙ ነው።
ቢቢሲ፡ የዘመናዊው በይነመረብ በመንግሥት ወይም በተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ባሉ አንዳንድ ትልልቅ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ውሏል። በይነመረብ ምን ሆኗል ብላችሁ ታስባላችሁ? በጣም የሚያሳስባችሁ ነገርስ ምንድን ነው?
ክላይን: በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ስልምንጠቀመው በጣም አስፈላጊ ነው። ዳግመኛ ባይኖርስ ብሎ መገመት ከባድ ነው። ነጻ ሆኖ በመንግሥት ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል የበይነ መረብ ግብይት፣ ባንኪንግ፣ የቪዲዮ ሥርጭት፣ የዜና ማሠራጫዎች፣ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ሌሎችም አዳዲስ ሃሳቦችን አዳብሯል። ለሕይወታችን በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ግን ለመጥፎ ድርጊቶች ዒላማ ሆኗል።
ነገሮች እንዴት እንደተበላሹ በየጊዜው እንሰማለን። ከፍተኛ የሆነ የግላዊ መረጃ መጥፋት አለ። በእኔ አስተያየት ትልልቅ ኩባንያዎች (ጎግል፣ ሜታ፣ አማዞን እና ሌሎችም) በጣም ብዙ ጉልበት አላቸው። ስለትክክለኛው መፍትሄ ግን እርግጠኛ አይደለሁም።
ዱቫል፡ እኔ እንደማስበው በየትኛውም አካል የበላይነት ላይ ትልቅ አደጋ አለ። የፖሊሲ እና የምርጫ ውጤትን በመቀየር ረገድ የሐሰት መረጃን ኃይል አይተናል። የኩባንያዎች ኃይልም በማኅበራዊ መስተጋብሮች እና ጎልማሶች እና ወጣቶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አይተናል።
ክላይን፡ በጣም ከሚያስፈራኝ ነገር አንዱ የሐሰተኛ መረጃ መስፋፋት ነው። አንድ ሰው "በይነመረብ ላይ አይቻለሁ" ሲል ስንት ጊዜ ሰምተሃል? ሁልጊዜ የውሸት መረጃን ማሠራጨት ቢቻልም ግን ደብዳቤዎችን ለመላላክ፣ ቢልቦርድ ለመትከል ወይም የቲቪ ማስታወቂያ ለማሠራት ገንዘብ ያስፈልግ ነበር። አሁን ርካሽ እና ቀላል ሆኗል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ሲደርሱ ይደጋገም እና እንደ እውነታ ይቆጠራል።
ሌላው ፍርሃት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሥርዓቶች ወደ በይነመረብ እገቡ በመሆኑ እነዚህ ሥርዓቶች ከተወገዱ ወይም ከተበላሹ ከባድ መስተጓጎል ይፈጠር ይሆናል። ለምሳሌ የመገናኛ ዘዴዎች ብቻ ሳይሆን የባንክ፣ የፍጆታ ዕቃዎች፣ የትራንስፖርት ወዘተ. . .
ዱቫል፡ ትልቅ ኃይል አለው፤ ነገር ግን እአአ በ1962 የኤንግልባርን ማስጠንቀቂያ ሳንሰማ የኢንተርኔትን በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም።
ቢቢሲ፡ በአርፓኔት ከነበራችሁ ጊዜ በመነሳት ዓለም ለሁሉም ሰው የተሻለች ቦታ እንድትሆን ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች አሉ?
ክላይን፡ የኢንተርኔት ነጻ መሆን ጥናቶችንን እና አዳዲስ አጠቃቀሞችን የሚፈቅድ ቢሆንም የቁጥጥር እጦት ደግሞ ወደ ችግር ሊያመራ ይችላል። አርፓ የአርፓኔትን የተወሰነ ቁጥጥርን አስቀምጧል። በዚህ መንገድ ሁሉም ነገር መሥራቱን ማረጋገጥ፤ የትኛዎቹ ሕጎች እንደሚያስፈልጉ ውሳኔዎችን ማድረግ፤ እንደ ድረ ገጽ ስሞች እና ሌሎች ችግሮችንም መፍታት ይችላሉ።
አንዳንዶቹን አሁንም ኢካን የሚያስተዳድረው ቢሆንም ወደፊት እንዴት እንደሚራመድ እና አሜሪካ በጣም ብዙ ቁጥጥር ይዛለች የሚለውን እና ሌሎች ላይ ዓለም አቀፍ አለመግባባቶች ነበሩ። ኔትዎርኩ እንዲሠራ ግን የተወሰነ ቁጥጥር አሁንም ያስፈልጋል።
አርፓኔትበአንጻራዊነት ትንሽ ስለነበረ በንድፍ፣ ፕሮቶኮሎች እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትልልቅ ለውጦችን መሞከር እንችል ነበር። ያ አሁን በጣም ከባድ ነው።
ዱቫል፡ በይነመረብን የሚያገኝ ሁሉ ኤአይን የሚያገኝበት ጫፍ ላይ ደርሰናል። አንዳንዶቹ ጎጂ ቢሆኑም በይነመረብ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ፈጣን እና ከፍተኛ ዕድገት ነበረው። ኤአይ አሁን በዚያ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከበይነመረቡ የማይነጣጠል ከመሆኑም ባለፈ ኤአይን የህልውና ስጋት ብሎ መጥራት ምክንያታዊ አይደለም። አደጋዎቹንም ሆነ ጥንካሬውን የምንገነዘብበት ጊዜ አሁን ነው።