ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ780 ሚሊዮን ዶላር ቢትኮይን የጠፋበት እንግሊዛዊ የከተማዋን ቆሻሻ መጣያ ለመግዛት ሃሳብ አቀረበ
የጄስም ሆዌል እጅግ ጠቃሚ መረጃዎቹን የሚያጠራቅምበት 'ሀርድ ድራይቭ' ከጠፋ 10 ዓመታት አልፈውታል። በውስጡ በመቶዎች ሚሊዮን ፓውንዶች የሚመነዘር ቢትኮይን ይዟል።
ምንም እንኳ ፍለጋው የማይታሰብ ቢሆንም እሱ ግን ዓላማውን ሳያሳካ የሚመለስ አይመስልም።
"ሥራዬ ይህ ነው። ከጠዋት እስከ ማታ" ይላል በፍፁም ታስፋ እንደማይቆርጥ በመናገር።
በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት የክሪፕቶከረንሲ ዋጋ እጅጉን ንሯል። የጄምስ ሀርድ ድራይቭ ውስጥ ያለው ቢትኮይን በአሁኑ ገበያ ቢሰላ 620 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም ከ780 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል።
ምንም እንኳ ጄምስ ከክሪፕቶከረንሲ ጋር የተገናኘ ሥራ ቢሠራም ሐሳቡ ያለው የከተማው የቆሻሻ ከሚጣልበት ስፍራ ላይ ነው።
የእንግሊዟ ኒውፖርት ከተማ ነዋሪ የሆነው ጄምስ እንደሚለው የቀድሞ የፍቅር ጓደኛው ናት በስህተት ሀርድ ድራይቩን ከቆሻሻ ጋር አውጥታ የጣለችው። ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ 2013 ነው።
የቆሻሻ መጣያው ሥፍራ የኒውፖርት ከተማ ምክር ቤት መሬት ነው። 8 ሺህ ቢትኮይን የያዘው ሀርድ ድራይቭ ከአስር ዓመታት በኋላም ከቆሻሻው መሐል እንዳለ ጄምስ ያምናል።
ባለፈው ወር የቆሻሻ መጣያውን እንዲያስስ ፈቃድ እንዲሰጠው አሊያም 495 ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ እንዲከፈለው ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያስገባው ጥያቄ በዳኛው ውድቅ ሆኖበታል።
አሁን በይግባኝ መጠያቂያው ፍርድ ቤት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዞ ራሱን ወክሎ ለመቅረብ ተዘጋጅቷል። የከተማዋ ምክር ቤቱ የቆሻሻ መጣያው ስፍራ አገለግሎቱ አብቅቷል በሚል በቅርቡ ሊዘጋው እንደሆነ ማሳወቁን ተከትሎ መሬቱን ለመግዛትም አቅዷል።
የኒውፖርት ምክር ቤት የጄምስን ጉዳይ በተለመከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ጄምስ የቢትኮይን ጥቅም ቀድሞ ከገባቸው ሰዎች መካከል ነው። በአውሮፓውያኑ 2009 ቢትኮይን ገና ዋጋው አነስተኛ ሳለ ነው ማከማቸት የጀመረው።
የኮምፒውተሩ ሀርድ ድራይቭ የአንድ ሞባይል ስልክ ያክል መጠን አለው። የቢትኮይን ዋጋ መናር ሲጀምር ነው ባለሙያዎችን አሰባስቦ በመቶዎቹ ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ዋጋ ያላቸውን ቢትኮይኖችን የያዘውን የመረጃ ቋት ፍለጋ የጀመረው።
የከተማ ምክር ቤቱ የቆሻሻ መጣያውን እንዲያስስ ፈቃድ እንዲሰጠው በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆኖበታል። ሀርድ ድራይቩን ካገኘ ወሮታ ለመክፈልም ቃል ገብቶ ያውቃል።
ምክር ቤቱ የቆሻሻ ሥፍራውን መነካካት ለአካባቢ ደኅንነት ጠንቅ ነው ሲል ይከራከራል።
ጄምስ አሁን ሁለት አማራጭ አለው። አንደኛው አቤቱታ በድጋሚ አስገብቶ መጠየቅ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከኢንቨስተሮች ጋር ተጣምሮ የቆሻሻ መጣያውን ሥፍራ መግዛት።
ግለሰቡ የቀጠራቸውን የሕግ አማካሪዎች አመስግኖ ከዚህ በኋላ ግን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ታግዞ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለቢቢሲ ይናገራል።
ኤአይን "በጣም የሚደንቅ ቴክኖሎጂ" ሲል ይገልፀዋል። ስለፍርድ ቤት እና ተያያዝ የሕግ ጉዳዮች በኤአይ ታግዞ ብዙ ዕውቀት እንደቀሰመ ሲናገር በሙሉ ልብ ነው።
የቆሻሻ መጣያውን ገዝቶ መሬቱን ቢቆፍረው የከተማ ምክር ቤቱ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚቀንሰው በማስረዳት ይግባኝ ለመጠየቅ አስቧል።
"እያንዳንዱ ቆሻሻ ወጥቶ ድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። በዚህ ሂደት ውስጥም ሀርድ ድራይቩን ማግኘት እንችላለን። በተዘዋዋሪ አዲስ የቆሻሻ መጣያ ይኖረናል ማለት ነው" ይላል።
የከተማ ምክር ቤቱ የጄምስ ሀርድ ድራይቭ የቆሻሻ መጣያው ሥፍራ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ የምክር ቤቱ ንብረት ሆኗል ሲል ይከራከራል።
ነገር ግን ጄምስ ንብረቱ ከእርሱ እውቅና ውጪ መጣሉን ተከትሎ የምክር ቤቱ መከራከሪያ ውሀ የማያነሳ ነው ይላል።
ጄምስ እንደሚለው የቆሻሻ መጣያውን ለመግዛት ከኢንቨስተሮች ጋር የመጀመሪያ ዙር ውይይት አድርጎ ከስምምነት ደርሷል። ኢንቨስተሮቹ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከዩናይትድ ስቴትስ እንደሆኑም ይናገራል።
ምክር ቤቱ የቆሻሻ መጣያውን ለመሸጥ ፍላጎት አላሳየም። የቆሻሻ መጣያው ሲዘጋ በሥፍራው ከፀሐይ ኃይል ማመንጫ ለማሥራት ምክር ቤቱ ዕቅድ አውጥቷል።
ጄምስ በሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠር ቢትኮይን የያዘው ሀርድ ድራይቭ 1.4 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ የተከመረበት ሥፍራ እንዳለ እርግጠኛ ነው።
አንድ ቀን ተስፋ ቆርጦ ቢትኮይኑን መፈለግ ያቆም እንደሆን ተጠይቆ "በፍፁም አላደርገውም" ሲል መልሷል።