በድሬዳዋ ከተማ እና በሶማሌ ክልል "ሲንቀሳቀሱ የነበሩ" የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት "አመራር እና አባላት" መገደላቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, dire tv
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና በሶማሌ ክልል ሲንቀሳቀስ የነበረ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቡድን "አመራር እና አባላት የነበሩ 43" ግለሰቦች መገደላቸውን እንዲሁም ሌሎች "እንደተማረኩ" እና "እጅ እንደሰጡ" የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የታጣቂ ቡድኑ ኃይል በአካባቢው በተንቀሳቀሰበት ወቅት "ሁለት የፖሊስ አባላትን" ጨምሮ መግደሉን እንዲሁም ዘመቻው ሲካሄድ "የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ" የፀጥታ ኃይል አባላት እንዳሉም ተገልጿል።
መንግሥት "ሸኔ" በማለት በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ክንፍ ላይ ተወስዷል የተባለውን እርምጃ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች ይፋ የተደረጉት የድሬዳዋ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ትናንት ሰኞ ጥቅምት 17/2018 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ ነው።
የፖሊስ ኮሚሽነሩ እንደሚናገሩት ከአጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል "ከምዕራብ ሐረርጌ በተለይም ከአንጫር ዲንዲን አካበቢ" የተነሱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ወደ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የገቡት ከአንድ ወር በፊት "መስከረም 19" ቀን ነው።
ወደ ከተማ አስተዳደሩ የተንቀሳቀሰው የታጣቂ ቡድኑ ክንፍ አባላት ብዛት "ከ70 እስከ 80" መሆኑ እንደተደረሰበትም አስረድተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ዓለሙ ገለጻ፤ ታጣቂ ቡድኑ "የምሥራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች የሆኑትን የኦሮሚያ፣ የሶማሌ እና ድሬዳዋ አዋሳኝ ስፍራዎች የመሸሸግ" ዕቅድ ነበረው።
ኮሚሽነሩ፤ ቡድኑ "በተለያዩ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ ኢኮኖሚ እና ኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ የሽብር ጥቃቶችን" የመፈጸም ዕቅድ እንደነበረው በማንሳት ከስሰዋል።
በተጨማሪም ቡድኑ "ጭናቅሳ እና ዳሪሁ" በተባሉ አካባቢዎች ላይ "ቤዝ" በመመሥረት፣ "ሥልጠና አድርጎ ራሱን የማስፋፋት" ሐሳብ እንደነበረው ተናግረዋል።
"ዋና ዓላማው፤ በምሥራቅ ሐረርጌ ጋራ ሙለታ ሄዶ፣ ሌላ ቤዝ መመሥረት እና በዚያም እንደዚሁ የሥልጠና ቦታ በማመቻቸት፣ ራሱን ከግዜ ወደ ጊዜ አስፍቶ ምሥራቅ ኢትዮጵያን የግጭት፣ የሽብር ቀጣና፣ የብሔር ብሔረሰቦች ግጭት ቀጠና ለማድረግ ያለመ ነበር" ሲሉም ወንጅለዋል።
"ከዚያ ተነስቶ በጅቡቲ መስመር በደንገጉም በታችም በሶማሌ ክልል በኩል ያሉትንም በማጥቃት ሽብር ለመፍጠር ነው እንግዲህ ጠላት ያቀደው" ብለዋል።
ታጣቂ ቡድን ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ "ሁለት" የፖሊስ አባላት፣ "ሦስት" የሚሊሻ አባላት እንዲሁም አንድ "መምህርን" መግደሉን በመግለጫው ላይ አንስተዋል።
በሶማሌ ክልል "ሲቲ ዞን ላስዴሬ አካባቢ" ውስጥም "አራት የቻይና መንግሥት ሠራተኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን" በቡድኑ ታግተው እንደነበረ እና "አራት ሚሊዮን ብር" ተከፍሎ መለቀቃቸውን ጠቅሰዋል።
በድሬዳዋ ከተማ እና ሶማሌ ክልል መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር የተባለውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ክንፍ "ለማጥቃት እና ለማጥፋት" ሰባት የፌደራል እና የክልል የጸጥታ አካላትን በአባላትነት የያዘው "የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ግብር ኃይል" ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
የፀጥታ ኃይሎቹን ጥምረት በመወከል መግለጫ የሰጡት ኮሚሽነር ዓለሙ እንደሚያስረዱት፤ ከግብረ ኃይሉ አባላት መካከል "የመከላከያ ሠራዊት ምስራቅ ዕዝ" እና "የምሥራቅ ኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል" ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Dire Dawa Government Communication Affairs Bureau
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ "የወንጀል መከላከል ኃይል"፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ "ፀረ ሽምቅ እና ልዩ ኃይል" እንዲሁም የሶማሌ ክልል "ልዩ ኃይል" አባላትም ግብረ ኃይሉ ውስጥ መካተታቸውን ጠቅሰዋል። የድሬዳዋ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል ሚሊሻ አባላትም ተሳትፎ እንደነበራቸው አክለዋል።
ግብረ ኃይሉ በታጣቂ ኃይሉ ላይ ያካሄደውን ዘመቻ የጀመረው "በአንድ ወር ለመጠናቀቅ" በማቀድ እንደሆነ የሚናገሩት ኮሚሽነር ዓለሙ፤ ሦስት ዘርፎች ተከፋፍለው "መረጃ የማጠናከር"፣ "ኦፕሬሽኑን በተግባር የማካሄድ" እና "ምርመራ ማካሄድ" ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ዕቅዱን "ተግባራዊ ሳያደርግ፣ ፍጹም በሆነ በእነዚህ ሰባት የጸጥታ ኃይል ተከቦ ካለበት እንዲወጣ አድርጎ፣ ከተቀበረ ጉድጓድ በማውጣት ሜዳ ላይ ሲገኝ እንግዲህ እርምጃ ተወስዶበታል" ብለዋል።
ኮሚሽነር ዓለሙ፤ "በዚህ መሠረት 43 የጠላት ኃይል ተገድሏል። ከዚህ 43 ውስጥ ዋናው መሪ ጃል ሀረርጌ ወይም ኢቲመር የሚባለው እርምጃ ተወስዶበታል ሞቷል። [...] የእሱ ምክትል የተባሉት ጃል ቦባስ እና ጃል ራሳ የሚባሉት ደግሞ፤ ጃል ቦባስ ተመትቶ የተያዘ ሲሆን ጃል ራሳ እንዲሁ ተማርኳል" ሲሉም አብራርተዋል።
"25" የቡድኑ አባላት "እንደተማረኩ" እና "እጅ እንደሰጡም" የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውንም ተናግረዋል። ከታጣቂ ቡድኑ ጋር "በሴል፣ በፋይናንስ፣ በመረጃ፣ ገንዘብ በማስተላለፍ፣ በተለያየ ሁኔታ ሲረዱ የነበሩ"፤ "34 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች" በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አክለዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ተፈጽሟል በተባለው እገታ ውስጥ የተሳተፉ እንደሚገኙበትም ገልጸዋል። ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የተከፈለው "አራት ሚሊዮን ብር" የገባበት የባንክ አካውንት እንዲታገድ ተደርጎ፤ በሒሳብ ቁጥሩ "ሲጠቀሙ የነበሩ" የቡድኑ "ደጋፊዎች" መያዛቸውንም ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ዓለሙ፤ "እነኚህ ለሕግ ቀርበው ወደ ዘጠኝ መዝገብ ተጣርቷል። ከዘጠኙ አራቱ መዝገብ ለዐቃቤ ሕግ ሙሉ በሙሉ ተሟልቶ ወደ ክስ መክፈት እና ለችሎት ማቅረብ የደረሰበት ሲሆን አምስት መዝገብ ደግሞ በአሁን ሰዓት በማጣራት ላይ ነው ያለነው" ብለዋል።
የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ "በተለየ ወጥቶ ለሕግ እንደሚቀርብ" አስታውቀዋል። ዘመቻው በተካሄደበት ወቅትም "የደም፣ ላብ፣ የሕይወት መስዋዕትነት" የከፈሉ የግብረ ኃይሉ አባላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነር ዓለሙ፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና አጎራባች አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት ከታጣቂ ቡድኑ "ነጻ" መሆናቸውን ተናግረዋል።















