ታዋቂዋ የደቡብ አፍሪካ የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ ወጣቶችን ለሩሲያ ጦር በመመልመል ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረበች

በታዋቂው የደቡብ አፍሪካ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ የሆነች ግለሰብ፤ ወንዶችን ለሩሲያ ጦር በመመልመል ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውላ ፍርድ ቤት ቀረበች።

የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዋ ናንኩሉሌኮ ፓትሪሺያ ማንቱላን ጨምሮ አምስት ሰዎች ፍርድ ቤት የቀረቡት፤ ደቡብ አፍሪካውያን ይፋዊ ፈቃድ ሳያገኙ የውጭ አገር ጦርን እንዳይቀላቀሉ የሚከለክለውን ሕግ በመጣስ ተከስሰው እንደሆነ ዐቃብያነ ሕግ ተናግረዋል። ተከሳሾቹ እስካሁን ድረስ የእምነት ክህደት ቃላቸውን አልሰጡም።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት 17 ዜጎች ተታልለው "በሚመስል ሁኔታ" ቅጥረኛ ወታደር ሆነው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ውስጥ እንዲሳተፉ መደረጋቸውን ኅዳር ላይ ገልጾ ነበር።

ይህ ጉዳይ በመንግሥት ይፋ ከተደረገ ወዲህ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ባለው ጉዳይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ይህ የመጀመሪያው ነው። የአገሪቱ ፖሊስ ግን የክስ ሂደቱ አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ሁለቱን ጉዳዮች አገናኝቶ መግለጽ እንደማይፈልግ አስታውቋል።

የ39 ዓመቷ ማንቱላ በታዋቂ የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን በሆነው 'ኤስኤቢሲ' ሥር በሚገኘው 'ኤስኤ ኤፍኤም' ላይ የሚተላለፈው 'ዘ ሞርኒንግ ብሊስ' የተሰኘ ፕሮግራም አቅራቢ ነች። በቁጥጥር ሥር መዋሏን በተመለከተ እሷም ሆነች መገናኛ ብዙኃኑ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዋ እና ሌሎች አራት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተሰማው የብዙዎችን ቀልብ ከሳበው የባለፈው ሳምንት ክስተት በኋላ ነው። ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ልጅ የሆነችው ዱዱዚሌ ዙማ ሳምቡድላ ከአገሪቱ ፓርላማ ለቅቃለች።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ልጅ ዘመዶቿን ጨምሮ 17 ደቡብ አፍሪካዊ ወንዶችን አታልላ ለሩሲያ እንዲዋጉ አድርጋለች የሚል ክስ ቀርቦባታል። ዙማ ሳምቡድላ ግን ይህንን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች።

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ የዐቃቤ ሕግ ባለሥልጣን፤ የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዋ ማንቱላ ዕድሜያቸው ከ21 እስከ 46 ከሚሆናቸው ሌሎች አራት ወንዶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሏን አስታውቋል። እያንዳንዱ ተከሳሾች የውጭ ሠራዊት እገዛ ቁጥጥር የተባለውን ሕግ በመተላለፍ ክስ ቀርቦባቸዋል።

እንደ ዐቃቤ ሕግ ገለጻ ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ዋና ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የተሰማሩ ፖሊሶች ከሰጡት ጥቆማ በመነሳት ነው።

ፖሊስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አድርገው ወደ ሩሲያ ሊጓዙ የሞከሩ ሦስት ሰዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ ተገልጿል። ግለሰቦቹ የተያዙት "አጠራጣዊ" ሁኔታዎችን በማሳየታቸው እንደሆነም ተነግሯል።

ዐቃቤ ሕግ እንደሚያስረዳው፤ ማንቱላ "አብረዋት የተከሰሱትን ሰዎች ጉዞ እና ወደ ሩሲያ ፌዴሬሽን ሠራዊት ለማስገባ የተካሄደውን ምልመላ አመቻችታለች።"

የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢዋ እና ሌሎቹ ተከሳሾች ሰኞ ዕለት በጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን አሁንም በቁጥጥር ሥር ናቸው። በዋስትና መብታቸውን ለማስከበር በሚቀጥለው ሳምንት በድጋሚ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፤ ቅጥረኛ ወታደር ተደርገው ከተወሰዱ እና በአሁኑ ሰዓት የጦርነት ቀጣና በሆነችው የዩክሬኗ ዶንባስ ግዛት ከሚገኙ 17 ሰዎች ጥሪ እንደደረሰው ያስታወቀው ኅዳር ወር ላይ ነበር።

ግለሰቦቹ፤ ቅጥረኛ ወታደር የሆኑት በቀረበላቸው አጓጊ የሥራ ውል ተታልለው እንደሆነ የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት "ከውጭ አገር ወታደራዊ አካላት ጋር የሚሰሩ ግለሰቦች ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ላይ የሚያደርሱትን ብዝበዛ" ኮንኗል።

ደቡብ አፍሪካውያኑን ለማስመለስ "በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች" እየተሠራ እንደሆነ ቢገለጽም እስካሁን ድረስ ውጤት አልተገኘም።