የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት በተመድ ጉባዔ ላይ ሳሉ የአሜሪካ ቪዛቸው ተሰረዘ

ግራ ዘመሙ መሪ በኒው ዮርክ በተካሄደ ለፍልስጤም ድጋፍ የሚሰጥ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግራ ዘመሙ መሪ በኒው ዮርክ በተካሄደ ለፍልስጤም ድጋፍ የሚሰጥ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተገኝተዋል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮን ቪዛ እንደሚሰርዝ አስታወቀ።

ግራ ዘመሙ መሪ በኒው ዮርክ በተካሄደ ለፍልስጤም ድጋፍ የሚሰጥ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከተገኙ በኋላ ነው ውሳኔውን የገለጸው።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ፕሬዝዳንቱ መገኘታቸውን "እሳት አቀጣጣይ ድርጊት" ሲል ኮንኗል።

አሜሪካ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስን ጨምሮ 80 የፍልስጤም አመራሮች በኒው ዮርክ የተካሄደውን የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይታደሙ ቪዛ መከልከሏ አይዘነጋም።

ትናንት ማምሻውን ፕሬዝዳንት ፔትሮ ከኒው ዮርክ ወደ ቦጎታ ለመብረር ዕድቅ ይዘው እንደነበር አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የጠቀሳቸው የኮሎምቢያ መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል።

ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የትራምፕ አስተዳደር በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የተቃጣ ነው በሚል ያደረሰውን የአየር ጥቃት "የአምባገነንነት ድርጊት" ሲሉ ወቅሰዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በተጋራ ተንቀሳቃሽ ምሥል ፕሬዝዳንቱ በአቅራቢያቸው ለተሰበሰቡ ሰልፈኞች በድምጽ ማጉያ በስፓኒሽ ንግግር ሲያደርጉ ታይቷል።

ከንግግራቸው በኋላ ተርጓሚያቸው "የመላው ዓለም አገራት ከአሜሪካ የሚበልጥ ወታደራዊ ኃይል ለመገንባት መተባበር አለበት" ሲል መልዕክታቸውን አስተላልፏል።

"እዚህ ኒው ዮርክ ሳለሁ መናገር የምፈልገው ነገር የአሜሪካ ወታደሮች ሰብአዊነት ላይ አፈሙዝ መደቀን እንዲያቆሙ ነው። የትራምፕን ትዕዛዝ ጣሱና የሰብአዊነት ሕግን ተከተሉ" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮን ንግግር አጣጥሏል።

"የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት በኒው ዮርክ ጎዳና ቆመው የአሜሪካ ወታደሮች ትዕዛዝ እንዳይቀበሉ በመንገር ነውጥ ቀስቅሰዋል። በዚህ እሳት አቀጣጣይ ንግግራቸው ምክንያት ቪዛቸውን እንሰርዛለን" ሲልም በኤክስ ገጹ አስታውቋል።

የኮሎምቢያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር አርማንዶ ቤንዴቲ በበኩላቸው፤ አሜሪካ መሰረዝ የነበረባት የፔትሮን ቪዛ ሳይሆን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ቪዛ ነበር ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

"ሆኖም ግን ኔታንያሁን ኢምፓየሯ ስለምትጠብቀው እርምጃ መውሰድ የቻሉት እውነቱን በተናገሩት መሪ ላይ ነው" ብለዋል።

ኮሎምቢያ በዓለም ትልቋ የኮኬይን አምራች አገር ስትሆን፣ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት አሜሪካ በጀልባዎች ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከተገደሉት የተወሰኑት ኮሎምቢያውያን መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አሜሪካ እርምጃው በቬንዝዌላ የሚካሄድ የፀረ አደንዛዥ ዕፅ ንቅናቄ አካል ነው ትላለች።

ፔትሮ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአሜሪካና በኮሎምቢያ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

አሜሪካ የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስን ጨምሮ 80 የፍልስጤም አመራሮች በኒው ዮርክ የተካሄደውን የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እንዳይታደሙ ቪዛ መከልከሏ አይዘነጋም።