የኬንያ ፍርድ ቤት፤ መንግሥት ፖሊሶችን ወደ ሄይቲ ለማሰማራት ያሳለፈውን ውሳኔ ውድቅ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአገሪቱ መንግሥት የወሮበላ ቡድኖችን ለመከላከል የፖሊስ መኮንኖችን ወደ ሄይቲ ለማሰማራት የያዘውን ዕቅድ አገደ።
የአገሪቱ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ፖሊሶችን ከኬንያ ውጪ ለማሰማራት የሚያስችል ሥልጣን ስላልተሰጠው ፖሊሶችን ወደ ሄይቲ መላክ ሕገወጥ ነው ሲሉ ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ የመንግሥትን ዕቅድ ውድቅ አድርገውታል።
ዳኛው አክለውም ምክር ቤቱ ሄይቲን ወደ መሳሰሉ አገራት ማሰማራት የሚችለው ፖሊሶችን ሳይሆን ወታደሮችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በሄይቲ ያለውን የወሮበሎች ሥርዓት አልበኝነት ለመቆጣጠር የሚሰማራውን ዓለም አቀፍ የፀጥታ ኃይል ኬንያ ለመምራት ከወራት በፊት ቃል ገብታ ነበር።
ዳኛው ውሳኔያቸውን ባብራሩበት ጊዜ መንግሥት የፖሊስ መኮንኖችን ወደ ሌላ አገራት ማሰማራት የሚችለው፣ በኬንያ እና በተቀባዩ አገር መካከል ስምምነት ካለ ብቻ መሆኑን የአገሪቱ ሕግ ጠቅሰው አስረድተዋል።
ወሮበላ ቡድኖች የአገሪቱን ዋና ከተማ ፖርት-አው-ፕሪንስ 80 በመቶ የሚሆነውን ክፍል መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፣ የሄይቲው ፕሬዝዳንት አሪየል ሄንሪ የተባበሩት መንግሥታት በአስቸኳይ ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ኃይሎችን እንዲያሰማራ ጠይቀው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ባለፈው ጥቅምት የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሚሰማራውን የፀጥታ ኃይል ኬንያ ለመምራት ፈቃደኛ መሆኗን ተቀብሎ፣ የኬንያ ፓርላማም የፖሊሶቹን ስምሪት አጽድቆት ነበር።
ዓለም አቀፍ የፖሊስ አባላት በሄይቲ የመሰማራታቸው ጉዳይ ከተሰማ በኋላ በአገሪቱ ውስጥ ድብልቅ ስሜት ተንጸባርቋል።
አንዳንዶች ስምሪቱ በአገሪቱ ሰላም በማውረድ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቅረፍ ዕድል ይፈጥራል በሚል በበጎ ጎኑ ሲቀበሉት፣ ሌሎች ደግሞ የፖሊስ ኃይሉን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት የገንዘብ እና የጊዜ ብክነት ነው ሲሉ ተቃውመውታል።
የኬንያ መንግሥት ውሳኔን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት የተቃዋሚዎች መሪ ኤኩሩ አውኩቶ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ የራሷን የፀጥታ ችግር ሳትፈታ ፖሊሶችን ወደ ሌላ መላክ ለሌለባት ኬንያ ድል ነው ብለዋል።
ጨምረውም ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የፖሊሶቹን ስምሪት ከምዕራባውያን ድጋፍን ለማግኘትና ዓለም አቀፍ ገጽታቸውን ለመገንባት የሚጠቀሙበት ጉዳይ ነው ሲሉም ተችተዋል።
የኬንያ መንግሥት የፖሊሶቹ ስምሪት ለአገሪቱ መልካም ስምን የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ ጠቃሚ ልምድ የሚገበይበት ይሆናል ሲል ተከራክሯል።












