ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች ‘እንቅልፍ ወስዷቸው’ መዳረሻውን አልፈው ነበር ተባለ
ከሱዳን የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎች "እንቅልፍ ጥሏቸው" መዳረሻቸውን አልፈው እንደነበር ተነገረ።
ይህን ዘገባ ቀድሞ ያወጣው ‘ዘ አቪዬሽን ሄራልድ’ እንዳለው ሰኞ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ በነበረው በረራ ላይ የነበሩት ሁለት አብራሪዎች በእንቅልፍ ምክንያት ቦሌ ለማረፍ ከፍታቸውን አልቀነሱም ብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ማብራሪያ በዕለቱ በአብራሪዎቹ እና በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መካከል ግንኙነት ተቋርጦ እንደነበረ አረጋግጦ፤ ለዚህ መንስኤው ምን እንደሆነ እየተጣራ ነው ብሏል።
አየር መንገዱ ዛሬ ነሐሴ 12/20014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአብራሪዎቹ እና በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች መካከል ግንኙነት በምን ምክንያት እንደተቋረጠ ያለው ነገር ባይኖርም፣ የጀመረው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚመለከታቸው የበረራ ሠራተኞች ከሥራ መታገዳቸውን ገልጿል።
የበረራ ቁጥር ኢቲ 343 ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ በ37ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ሲበር ነበር።
አውሮፕላኑ ከፍታውን እንዲቀንስ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አብራሪዎቹን በተደጋጋሚ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም ብሏል ዘ አቪዬሽን ሄራልድ።
ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ምላሽ ያልሰጡት አብራሪዎች ከአውሮፕላኑ የበረራ ሥርዓት የማስጠንቀቂያ ድምጽ ከማረፊያቸው መድረሳቸውን በማመልከት ‘አንቅቷቸዋል’ ተብሏል።
አውቶፓይለት አውሮፕላኑ ቀድሞ በሚሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ከፍታውን፣ ፍጥነቱን እና የበረራ መስመሩን ጠብቆ ወደ መዳረሻው እንዲበር የሚያደርግ ሥርዓት ነው።
ይሁን እንጂ የአውቶፓይለት ሥርዓቱ አውሮፕላኑ ከመዳረሻው ሲደርስ ሥርዓቱን በራሱ አቁሞ የማስጠንቀቂያ ድምጽ ማሰማቱን ዘ አቪዬሽን ሄራልድ አስነብቧል።
ፍላይትራዳር24 ላይ መመልከት እንደሚቻለው ቢያንስ ባለፉት 7 ቀናት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዕለቱ ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ በረራ ያደረገ ሲሆን፣ በረራው የሚፈጀው ጊዜም ከ1 ሰዓት ከ25 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ድረስ ነው።
ይሁን እንጂ ሰኞ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ከካርቱም አዲስ አበባ የነበረው በረራ አውሮፕላኑ ያረፈው 20 ደቂቃ ዘግይቶ ከ1 ሰዓት ከ49 ደቂቃ በረራ በኋላ ነው።
አውሮፕላኑ በሰላም ያረፈ ሲሆን፤ አየር መንገዱ ዛሬ በማኅበራዊ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ ላይ የተጓዦች ደኅንነት ከሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመልክቷል።
‘ክስተቱ እጅግ አሳሳቢ ነው’
ለቢቢሲ እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ትንታኔ የሚሰጠው የአቪዬሽን ተንታኙ አሌክስ ማቼራስ ክስተቱ እጅግ አሳሳቢ ነው ብሏል።
“በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ያጋጠመው ክስተት እጅግ አሳሳቢ ነው” ያለው አሌክስ ማቼራስ፤ ወደ መዳረሻው የተቀረበው የበረራ ቁጥር ኢቲ343 አውሮፕላን “ለምን ከፍታውን አልቀነሰም?” ሲል ጠይቋል።
የዘገባውን መውጣት ተከትሎ አሌክስ ማቼራስን ጨምሮ በርካቶች ክስተቱን በአብራሪዎች ካለው የሥራ ጫና ጋር አያይዘውታል።
ይህ የአቪዬሽን ተንታኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ አብራሪዎች ላይ ያለው ጫና የበረራ ደኅንነት ስጋት ሆኖ ቀጥሏል ሲል የጄት2 አየር መንገድ እሰጣ ገባን እንደምሳሌነት አያይዟል።
የብሪቲሽ አየር መንገድ የአብራሪዎች ማኅበር (ባልፕ) ከጥቂት ሳምንታት በፊት ጄት2 የተባለው አየር መንገድ አብራሪዎቹ ላይ የሥራ ጫና በማብዛት በአብራሪዎች ጤና እና በረራ ደኅንነት ላይ አሉታዊ ሁኔታን እየፈጠረ ነው ብሎ ነበረ።