የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሰዓታት ባጋጠመው “የሲስተም ችግር” ምን ያህል ብር ወጪ ሆነ?

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ተፈጠረ በተባለው ችግር ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መውጣቱ እየተነገረ ነው።

ከዚህ በፊት በአገሪቱ የባንክ ሥራ ታሪክ አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ በተከሰተው በዚህ ችግር የባንኩ ደንበኞች ካስቀመጡት የገንዘብ መጠን ውጪ ከገንዘብመስጫ ማሽኖች (ኤቲኤም) እንዲሁም ከሞባይል ባንኪንግ ከፍተኛ መጠን ያለው ብር ወስደዋል።

ይህንንም ተከትሎ ባንኩ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎቶችን በማቆም ችግሩ ለመቆጣጠር መቻሉን ያሳወቀ ሲሆን፣ ነገር ግን በዚህ ክስተት ምን ያህል ብር ወጪ እንደተረገ ወይም እንደተዘዋወረ በይፋ የሰጠው አሃዝ የለም።

የተለያዩ መንጮች ከባንኩ የወጣው የብር መጠን ከመቶ ሚሊዮኖች አስከ ቢሊዮኖች ብር ባንኩ ጤናማ ያልሆነ ባለው መንገድ መዘዋወሩን ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።

ቢቢሲ ይህንን አሃዝ በተመለከተ ከባንኩ ኃላፊዎች ማረጋገጫ ወይም ማስተባበያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፣ በደፈናው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ መደረጉን ብቻ አመልክተዋል።

አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) የዜና ወኪል ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ ችግር ባጋጠመው ወቅት የተወሰደበት ገንዘብ 2.4 ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዶላር) መሆኑን አመልክቷል።

የዜና ወኪሎ ጨምሮም ባንኩ በሰዓታት ውስጥ ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖቹ የወጣውን እና በሞባይል አማካይነት የተዘዋወረውን ገንዘብ ለማስመለስ ጥረት መጀመሩን ዘግቧል።

ባንኩ የገጠመውን ችግር ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ አቶ አቤ ሳኖ ሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቃሚዎች የሌላቸውን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ማዘዋወር የቻሉት የባንክ ሥርዓቱን በማሻሻል ሂደት ወቅት በተፈጠረ ክፍተት እንጂ የበይነ መረብ ጥቃት ደርሶበት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አክለውም የሲስተም ችግር አጋጥሟል በተባለበት አርብ ምሽት በነበሩ ሰዓታት ውስጥ መጠኑ በይፋ ያልተገለጸ “ጤናማ ያልሆነ” ያሉት የገንዘብ ዝውውር መካሄዱን ገልጸዋል።

በአገሪቱ ትልቁ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በየዕለቱ በመላው አገሪቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በተለያዩ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ዘዴዎች ያንቀሳቅሳል።

ባንኩ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ላይ ችግር በገጠማው ጊዜ በነበሩት ሰዓታት ውስጥ ጤና ማየሆኑትን ጨምሮ ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ዝውውር መከናወኑን አመልክቷል።

በባንኩ ላይ የሲስተም ብልሽት የመከሰቱን አጋጣሚ ተጠቅመው በባንክ ሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው በርከት ያለ የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የተባሉት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸው ጭምር ይፋ ተደርጓል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች በዕለቱ በሂሳባቸው በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ወደ ሲቢኢ ብር አካውንታቸው እንዲሁም ወደ ወሌሎች ባንኮች ገንዘብ ማዘዋወራቸውን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም በምሽት በትምህርት ተቋማቱ ውስጥ እና በአቅራቢያው ባሉ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤቲኤም) አካባቢ ረዣዥም ሰልፎችን ሰርተው ጥሬ ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ እንደነበረ ተማሪዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገንዘብ መክፈያ እና ማዘዋወሪያ ሥርዓቱ ላይ ያጋጠመው ችግር በተማሪዎች ዘንድ በስልክ አማካይነት በስፋት መሰራጨቱንም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ አቶ አቤ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ የእራሳቸው ባልሆነው የገንዘብ ዝውውር ውስጥ የገቡት ባንኩ የሳይበር ጥቃት አጋጥሞት እንደሆነ እና ሊደረስብን አይችልም በሚል የተሳሳተ ግምት ነው ብለዋል።

ባንኩ ችግሩ በሥርዓቱ ላይ መከሰቱን ተከትሎ አገልግሎቶች እንዲቋረጥ በማድረግ ለገጠመው ክፈተት መፍትሄ ከሰጠ በኋላ የባንክ ሥራውን መልሶ ጀምሯል።

“የተቋረጠውን አገልግሎት ካስጀመርን በኋላ ወደ ግብይቶች ምርመራ ነው የገባነው። በዛ ያለ ግብይት ያደረጉትን ለይተን የፍትሕ አካላት እንዲያውቁት አድርገናል” ያሉት አቶ አቤ ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የተካሄደ ነው።

ቢሆንም ግን ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ የተደረጉ ጤናማ እና ጤናማ ያልሆኑ የገንዘብ ዝውውሮች እንዲሁም እየተመለሰ ያለው ገንዘብ እየተለየ እና ኦዲት እየተደረጉ በመሆናቸው ከባንኩ የወጣውን የገንዘብ መጠን ከመናገር ተቆጥበዋል።

ኤፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ባንኩ ገንዘቡን ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ከቅዳሜ ጀምሮ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በመሆን ያላግባብ ወጪ የተደረገ ገንዘብ እንዲመለስ ጥሪ ሲያደርግ ነበር።

ቢቢሲ ሰኞ ዕለት ያናገራቸው የዲላ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዳረጋገጡት የፌደራል ፖሊሶች በጊቢው ውስጥ መታየታቸውን እና ገንዘብ ያዘዋወሩ ተማሪዎች ሲመልሱ ነበረ ብለዋል።

ባንኩ በዚህ ጤናማ ያልሆነ ባለው የገንዘብ ዝውውር አማካይነት ብር የወሰዱ ሰዎች በተደረገው ጥሪ መሠረት ገንዘቡን የሚመለሱ ከሆነ ክስ እንደማይመሠርት፣ ከዚያ ውጪ ግን የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖር ገልጿል።

ከገንዘብ መክፈያ ማሽኖች የወጣ እና በሞባይል ባንክ የተዘዋወረው ገንዘብ ለግብይት አገልግሎት ከመዋላቸው ባሻገር ወደ ሌሎች ባንኮች መሸጋገራቸው ተነግሯል።

ባንኩ ችግሩ በተከሰተበት ዕለት የነበሩ ዝውውሮችን አግዶ ምርመራ ከማድረጉ በተጨማሪ ከንግድ ባንክ ሂሳብ ገንዘብ ገቢ የተደረገባቸው የሌሎች ባንኮች ሂሳቦችም እንዳይንቀሳቀሱ መድረጉን ቢቢሲ ከምንጮቹ መረጃ አግኝቷል።

የደንበኞ ሂሳብን ካገደቡ የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ዳሽን ባንክ ሲሆን፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቀ የባንኩ ሠራተኛ በንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ችግር ማጋጠመ ከተገለጸ በኋላ በባንኩ ያሉ አንዳንድ ሂሳቦች ለጊዜው እንዲታገዱ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት ላይ ችግር በተፈጠረ ጊዜ ከንግድ ባንክ ወደ ዳሽን ባንክ ከ4500 በላይ የገንዘብ ዝውውሮች መደረጋቸውን ያረጋገጡት የባንኩ ባልደረባ፣ በዚህም ምክንያት ማጣራት እስኪደረግ በርካታ የዳሽን ባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ተደርገዋል።

ባንኩ እስካሁን በይፋ ምን ያህል ገንዘብ እንደተወሰደበት ባይገልጽም የባንኩ ፕሬዝዳንት ግን ከፖሊስ ጋር በመተባበር ባንኩ የተወሰደበትን ገንዘብ ለማስመለስ ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ የማይገባቸውን ገንዘብ የወሰዱ ሰዎች ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ዋነኛው ባንክ

ከ80 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱ ውስጥ በደንበኞች እና በቅርንጫፎች ብዛት እንዲሁም በገንዘብ አቅም ቀዳሚ የሆነ ግዙፍ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም ነው።

እንደ ስታቲስታ መረጃ ከሆነ በሃብት ብዛት በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ቀዳሚ የሆነው ንግድ ባንክ እአአ 2022 አጠቃላይ ንብረቱ 23 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

አንድ ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ ሃብት መሰብሰብ የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱ ዋነኛ ተቋማት ከሚባሉት ጥቂት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

በእአአ 2020/21 የበጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያገኘው ባንኩ በዚሁ የበጀት ዓመት 735 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ማድረግ መቻሉን ይፋ አድርጎ ነበር።

በ1935 ዓ.ም. የተመሠረተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ40 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን እና ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ቅርንጫፎች በአገሪቱ ያሉት ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ውጪም በጎረቤት አገራት ቅርንጫፎች አሉት።