ትግራይ በጦርነቱ የሞቱ የትግራይ ኃይል አባላትን እያሰበች ነው

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው ጦርነት የሞቱ የትግራይ ኃይል አባላትን ለማሰብ ከትናንት ጥቅምት 3/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሐዘን ቀን ታውጇል።

በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ የትግራይ ኃይል አባላት መርዶ ለቤተሰቦቻቸው በይፋ መነገሩንም ተከትሎ ነው የክልሉ መስተዳድር የሦስት ቀናት “ብሔራዊ የሐዘን ቀን ያወጀው”

በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 3/2015 ዓ.ም በመቀለ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት በነበረው ሥነ ስርዓት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ሕዝቡ በተገኘበት ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓታት ሕይወታቸውን ያጡ የትግራይ ኃይል አባላት መርዶ በይፋ ለቤተሰቦቻቸው በመንገር ተጀምሯል።

በመቀጠልም በሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለታጋዮቹ ክብር ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጓል።

ከትግራይ ክልል በተጨማሪ ከክልሉ ውጭ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እና ወዳጆችም ከጥዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት አድርገዋል።

በሰማዕታት ሐውልት በነበረው ዝግጅትም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ፣ የተለያዩ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት እና ቤተሰቦች የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥም በወጣቶቹ ህልፈት የተሰማቸውን ከፍተኛ ኃዘን ገልጸዋል።

ከመርዶው በኋላ በተለያዩ ቤተ እምነቶች የፍትሃት እና የጸሎት ሥነ ስርዓት ከንጋት ጀምሮ የተካሄደ ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናትም እንደሚቀጥል ተገልጿል።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የጧፍ የማብራት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “የታጋዮቹን ቆራጥነት እና የከፈሉትን መስዋዕትነት” በማጉላት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው “ ታጋዮቹ በከፈሉት መስዋዕትነት የትግራይን ሕዝብ ከምድረ ገጽ ከመጥፋት እንደታደጉት እና ህልውናውንም ማስቀጠል መቻሉንም’ ነው በዚህ ወቅት የገለጹት።

ከእሳቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በወጣቶቹ ህልፈት የተሰማቸውን ኃዘን ገልጸዋል።

“ዛሬ በትግራይ ክልል የማይለቀስበት ቤት የለም። የተሰውት ልጆቻችን በሕይወተ ስጋ ኖረው ቢሆን ብዙ ታሪክ መስራት ይችሉ የነበረ ቢሆንም እነዚህ የቤተሰብ እና የቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የአገር ተስፋዎች በእሸት በመቅረታቸው በሀዘን በተሰበረ ልብ ሁነን ነፍሳቸውን እንዲያሳርፍም” እንደሚጸልዩ በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

አቡነ ማትያስ ኢትዮጵያውያን ካለፉ የጦርነት ታሪኮች ባለመማራቸውም በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋርና በሌሎች ክልሎች ብዙ የሰው ደም ፈስሷል ብለዋል።

“ነገር ግን የፍጅት መጨረሻ ፍጅት ሆኖ አያውቅም እና አንድ ቀን ለመወያየት የምንቀመጥ ከሆነ ወጣቶችን ማስገበር እና በሬሳ ላይ ቆሞ መደራደር አንዳች ጥቅም እንደሌለው ከወዲሁ ልንገነዘብ ያስፈልጋል” ሲሉም በመደራደር ችግሮችን የመፍታት ባህልን ማዳበር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለሁለት ዓመታት የኤርትራ ጦር፣ የኢትዮጵያ መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኃይልና የሌሎች ክልል ኃይሎች በአንድ ጎራ እና የትግራይ ኃይሎች በሌላ ወገን ሆነው በተሳተፉበት ደም አፋሳሽ ጦርነት ምን ያህል ተዋጊዎች እና ሰላማዊ ሰዎች እንደሞቱ በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም።

ጦርነቱን ለማስቆም በተደረገው ሽምግልና የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት እንደተናገሩት በጦርነቱ 600 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ የተለያዩ ወገኖች በሁለት ዓመቱ ጦርነት የሞቱት ሰዎችን አሃዝ እስከ አንድ ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገልጻሉ።

በተለይም የጦርነቱ ዋነኛ ማዕከል በነበረችው እና ለረጅም ጊዜ ተዘግታ በቆየችው ትግራይ ውስጥ ብዙ ሰዎች በደረሰባቸው ጥቃት፣ በምግብ እና በመድኃኒት እጦት ለሞት መዳረጋቸውን በተለያዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

ነገር ግን እስካሁን በጦርነቱ የጠፋውን ሕይወት በተመለከተ በትክክል የታወቀ አሃዝ የለም።

በጦርነቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አጣሪ ቡድን በሪፖርቱ አስታውቋል።

በጦርነቱ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የጦር ወንጀሎች እና ዘር የማጽዳት ተግባር በጦርነቱ ተፋላሚ ወገኖች በተለያየ ደረጃ መፈጸሙም ተገልጿል።