በመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪ ሲጓዙ የነበሩ 53 ኤርትራውያን ስደተኞች በደቡብ ኢትዮጵያ ተያዙ

ስደተኞቹ ሲጓዙበት ነበረ የተባለው የመከላከያ ተሸከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, Ale Zone Communication

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞቹ ሲጓዙበት ነበረ የተባለው የአገር መከላከያ ተሸከርካሪ

በመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ ኬንያ ሲጓዙ የነበሩ 53 ሕገ-ወጥ ኤርትራውያን ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኧሌ ዞን አስታወቀ።

ሕገ-ወጥ ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከትላንት በስቲያ እሁድ ኅዳር 16/2016 ዓ.ም. ምሽት እንደሆነ የዞኑ ሰላም እና የፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ አንጋቶም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በደላሎች አማካኝነት ተሰባስበው ጉዞ የጀመሩት ኤርትራውያኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መነሻቸውን ያደረጉ ናቸው።

ከተጓዦቹ መካከል ሴቶችም ያሉበት ሲሆን ስድስት ሕጻናትም መኖራቸውን የገለጹት አቶ አምሳሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ በወራት የሚቆጠር ዕድሜ ያላቸው እና ጡት የሚጠቡ ሕጻናት ጭምር እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ኧሌ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም በና ጸማይ ወረዳን በሚያዋስ አካባቢ ላይ ሲደርሱ መሆኑን አንድ የአካባቢው ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል። በወቅቱ ፓስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ሕጋዊ ሰነዶችን እንዲያሳዩ የተጠየቁት ስደተኞቹ ይህንን ማድረግ አለመቻላቸውን እኚሁ ምንጭ ተናግረዋል።

የሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አምሳሉ በበኩላቸው ስደተኞቹ የተያዙት በአካባቢው የነበሩ የፖሊስ አባላት በጥርጣሬ መኪናውን ካስቆሙ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል።

ኤርትራውያኑ የተጫኑት በኢትዯጵያ መከላከያ ሠራዊት “ኦራል” ተሽከርካሪ እንደነበር የገለጹት አቶ አምሳሉ፤ “እነዚህን ያመጣው ደላላ ነው። ደላላው እስከ መከላከያ ሠራዊት ድረስ ገብቶ ጥርጣሬ እንዳይኖር በዚያ መኪና እንዲጫኑ ተደርጓል” ሲሉ ስደተኞቹ በዚህ መኪና እንዲጓዙ ምክንያት ሆኗል ያሉትን ጉዳይ ጠቅሰዋል።

ይሁንና የመከላከያ ሠራዊት መኪና በምን አግባብ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ወደ ሌላ አገር ለማጓጓዝ አገልግሎት ላይ እንደዋለ በትክክል እንዳልታወቀም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመኪናው አሽከርካሪ በምን ምክንያት ꬅደተኞቹን ሲያጓጉዝ እንደነበረ ለቀረበለት ጥያቄ “አለቃዬ ነው ያዘዘኝ” የሚል ምላሽ መስጠቱን አቶ አምሳሉ ተናግረዋል።

ጉዳዩ በአቅራቢያው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት ክፍል ከተገለጸ በኋላ በትናንት [ሰኞ] ጀምሮ ከሠራዊቱ አመራር ጋር ንግግር ተደርጎ ተሽከርካሪውን እና አሽከርካሪውን መውሰዳቸውንም አክለዋል።

የኧሌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማግሴ ጉያሎ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

53ቱ ኤርትራውያን ስደተኞች እስካሁን ደረስ በዞኑ የኮላንጎ ዙሪያ ወረዳ አዳራሽ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን የሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አምሳሉ ገልጸዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ማግሴ በበኩላቸው ስደተኞቹን በአቅራቢያ ወደሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለማስገባት ንግግር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል በየብስ እና በአየር ወደ ኬንያ እና ወደሌሎች አገራት ይሻገራሉ።