በትግራይ የጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ሕዝባዊ ውይይት ላይ ተቃዋሚዎች አንሳተፍም አሉ

ውይይቱ

የፎቶው ባለመብት, Hailu Kebede (Salsay weyane) Twitter

በትግራይ ክልል በሚመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ በተጀመረው ሕዝባዊ ውይይት ላይ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይሳተፉ ቀሩ።

ሕዝባዊ ውይይቱ ዛሬ የካቲት 22/2015 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ በጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታ ኮሚቴው ላይ የገለልተኝነት እና የአሳታፊነት ጥያቄ ያላቸው በክልሉ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሂደቱ እንደማይሳተፉ አሳውቀዋል።

የጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ እንደተናገሩት በዚህ ውይይት ውክልና፣ የጊዜያዊ መንግሥቱ አላማ፣ የሥልጣን ክፍፍል እና የኮሚቴው ሥነ ምግባር ሰነድ ቀርቦ ይጸድቃል።

በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖርን ውክልናን በተመለከተ 30 በመቶ ለህወሓት፣ 25 በመቶ ለትግራይ ሠራዊት፣ 15 በመቶ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሚሰጥ ቢገለጽም በውይይቱ የትግራይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልተገኙም።

በውይይቱ አዳራሽ ለፓርቲዎቹ ተወካዮች ተይዘው የነበሩ መቀመጫዎች ባዶ ሆነው የሚያሳይ ምሥልም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥቷል።

የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ለማካሄድ የተቋቋመውን ኮሚቴ እንደማይቀበሉት ከዚህ ቀደም ያስታወቁት ተቃዋሚዎቹ፣ በአንድ ፓርቲ - በህወሓት የተመረጡ ናቸው በማለት የሰላ ትችት ሲዘነዝሩም ቆይተዋል።

ኮሚቴው የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ሌ/ጄኔራል ታደረሰ ወረደ እና አቶ ሙሉ ወርቅ ኪዳነማርያምን ጨምሮ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ሦስት ከትግራይ ኃይሎች፣ ሦስት ከህወሓት እና ሦስት ከሲቪክ ማኅበራት የተውጣጡ መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህ ውይይት ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደተደረገላቸው የተናገሩት የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ፀጋ ዘአብ ካህሱ ሂደቱ አቃፊና አሳታፊ አይደለም ይላሉ።

“ይሄ ኮሚቴ በሚመራው ሂደት ውስጥ መሳተፍ የአንድ ድርጅትን ዓላማ ማስፈጸም እና ማሳካት ነው ብለን እናምናለን። በሂደቱ ውስጥ ተሳትፈን የምናመጣው ለውጥ የለም። ምንም ዓይነት ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ ዕድል አላገኘንም” ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም የምሥረታ ኮሚቴው በአንድ ፓርቲ መቋቋሙን ገልጸው፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሰነድንም የተከተለ አይደለም በማለት ይተቻሉ።

ጊዜያዊ መንግሥት የሚመሰርተው ኮሚቴ “ሕጋዊ ዕውቅና ያለው በሕዝቡም ሆነ በባለድርሻ አካላት ቅቡልነት ያለው አይደለም” ሲሉም ይናገራሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የሕዝብ ግንኙነት እና ሚዲያ ኃላፊ አቶ ክንፈ ሐዱሽ በበኩላቸው፣ የምሥረታ ኮሚቴው የአንድ ወገን በመሆኑ አካታች እና አቃፊ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደምም ኮሚቴው የተመሰረተበትን ሂደት ግልጽ አለመሆኑን ጥያቄ ቢያነሱም ኮሚቴው የቀረበውን ሐሳብ ለመስማት ዝግጁነት የለውም ይላሉ።

“የኮሚቴው አስተባባሪዎች በተደጋጋሚ ሚዲያ ላይ እየወጡ ማንም የሚያደናቅፈን ኃይል የለም። ወደፊት ነው የምናየው ብለው እኛ የምናቀርበውን ጥያቄ ለመቀበል ፍቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል።

ይህ ጥያቄ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን የትግራይ ምሁራን፣ ነጻ የሆኑ ሲቪክ ማኅበራት፣ ተጽእኖ ያላቸው ግለሰቦች ሳይቀሩ ኮሚቴው “የሚያደርገው ሕጋዊነት እና ተቀባይነት የሌለው ሂደት እንዲስተካከል በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር” ይላሉ አቶ ክንፈ።

ሕዝባዊ ውይይቱ በአንድ ድርጅት ነው የተዘጋጀው ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ዶክተር ጸጋ ዘአብ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሐሳቦች ያልተካተተበት ሰነድ የሚጸድቅበት መድረክ ላይ ገብተው የሚመጣ ለውጥ እንደሌለው ተናግረዋል።

ተቃውሟቸውን በውይይቱ መድረክ ላይ ተገኝቶ ማሰማት አይሻልም? ወይም የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላቸው ሊቀ መንበሩ።

“የሚለወጥ ነገር የለም ያልናችሁን ተቀበሉ ነው የተባልነው። ስለዚህ አዳማቂ እና አሟሟቂ ከመሆን ውጪ መድረኩ ሐሳብ የሚንሸራሸርበት ወይም ደግሞ ክርክሮች የሚደረግበት አይደለም ያለቀ ነገር ነው” ብለዋል።

አቶ ክንፈ በበኩላቸው ጊዜያዊ መንግሥቱ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተለይም ትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎችን አቃፊ እና አሳታፊ ሊሆን ይገባል ሲሉም አጽንኦት ይሰጣሉ።

“የአንድ ወገን ያልተገባ የበላይነት ያለው ጊዜያዊ መንግሥት ለሕዝቡ የሚጠቅም አይደለም። ጊዜያዊ መንግሥት ለመመስረት እና የበላይ ለመሆን እየተንቀሳቀሰ ያለ ፓርቲ እየሰራው ያለውን ስህተት እንዲስተካከል ተጽእኖ ማድረግ ይገባል” ይላሉ።

ህወሓት አቃፊ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ሂደት እንዲከተል ሁሉም ግፊት ማድረግ እንዳለበት አቶ ክንፈ ያሰረዳሉ።

ከዚህ ቀደም ሌ/ጄኔራል ታደሰ ጊዜያዊ መንግሥቱን ለመመሥረት የሚያስችለው የሥራ ሂደት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ ሁኔታ ለማካሄድ እንደተሞከረ ተናግረዋል። ጨምረውም ይህ ሂደት ለትግራይ ሕዝብ ወሳኝ የታሪክ ሂደት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ተደራዳሪ ቡድን አባላት ውይይት ላይ የበጀት ጉዳይ በተነሳበት ወቅት በቀዳሚነት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ እንደሚለቀቅ ተገልጾ ነበር።

ከበጀትም ጋር በተያያዘ የጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡንም የትግራይ ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ አስታውቀው ነበር።