የማንችስተር ፖሊስ በአየር መንገድ አንድን ግለሰብ መደብደቡ ቁጣ ቀሰቀሰ

ግለሰቡ በፖሊስ ሲደበድብ

በማንችስተር አየር መንገድ ውስጥ አንድን ግለሰብ በወደቀበት ጭንቅላቱን ሲመታና ሲረግጥ የታየው ፖሊስ ቁጣ ቀስቅሷል።

ፊቱን ወደ መሬት ቀብሮ የነበረውን ግለሰብ መሬት ላይ ሳለ ፖሊሱ ሲደበድበው የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወጥቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያ በወጣው ተንቀሳቃሽ ምሥል፣ ሌሎች ፖሊሶች በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች እንዳይጠጉ ሲያስጠነቀቁ ይታያሉ።

የግሬተር ማንችስተር ፖሊስ እንዳለው፣ ፖሊሶች ማክሰኞ ዕለት በአውሮፕላን ማረፊያው ግብግብ መነሳቱን ተከትሎ አንድን ግለሰብ ለማሰር ሲሞክሩ ጥቃት ደርሶባቸው ነበር።

ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ከወጣ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማንችስተር ፖሊስ ጣቢያ ተሰብስበው ተቃውሞ አሰምተዋል።

ከተቃዋሚዎቹ አንደኛው “ከዚህ በኋላ ለፖሊስ ጭካኔ አንንበረከክም” ማለታቸው ተዘግቧል።

የፖሊስ ጣቢያው ተባባሪ መሪ ኮንስታብል ዋሲም ቻውድሪ “በማንችስተር አየር መንገድ የሰጠውነውን ምላሽ በማስመልከት በፖሊስ ጣቢያው ትናንት ምሽት የተካሄደው ተቃውሞ በሰላም ተጠናቋል” ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

የግሬተር ማንችስተር ፖሊስ እንዳለው፣ ድርጊቱን የፈጸመው ፖሊስ ከሥራው ታግዷል። ገለልተኛ የፖሊስ መርማሪ እንዲያጣራም ሪፖርት ተደርጓል።

ኮንስታብል ዋሲም ቻውድሪ “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለው ቪድዮ በጣም እንደሚያስደነግጥ እንገነዘባለን። ሰዎች መቆጣታቸውንም እንረዳለን” ብለዋል።

“ሰዎችን ለማሰር እንዲህ ያለ ኃይል መጠቀም ያልተለመደ ክስተት ነው። የፈጠረው ድንጋጤም ይገባናል” ሲሉም አክለዋል።

ፖሊሱ ከሥራ እንደታገደና ለምርመራ ሪፖርት እንደተደረገ ገልጸዋል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ ያለፈው ማክሰኞ በአየር ማረፊያው በሰዎች መካከል ግብግብ ተነስቶ ፖሊስ ወደስፍራው ተጠርቷል።

አንደኛውን ተጠርጣሪ ለማሰር ሲሞክሩ ሦስት ፖሊሶች “ከፍተኛ ጥቃት” እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

“በጥቃቱ መሣሪያቸውን ሊቀሙ ነበር። ሦስት ፖሊሶች ሕክምና እየተደረገላቸው ነው። አንድ ሴት ፖሊስ አፍንጫዋ ተሰብሯል” ብለዋል።

ሁለት ወንዶች የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ላይ ጥቃት በመሰንዘር፣ የፖሊስን ሥራ በማደናቀፍ ሲታሰሩ፣ ሌሎች ሁለት ወንዶች ደግሞ አካባቢን በማወክና የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታስረዋል።

‘ለማየት ይከብዳል’

የዓይን እማኙ አማር ሚንሀስ እንዳለው፣ ፖሊስ አንድ በ20ዎቹ ገደማ ወዳለ ሰው ተጠግቶ እንደሚታሰር ገልጾለት ከግድግዳ ጋር ሲያላትም ተመልክቷል።

ግለሰቡ ፖሊሶቹን በቡጢ ለመምታት ሲሞክር እንደነበር ገልጿል። ሌላ ግለሰብም ግብግብ ገጥሟል።

በዚህ ወቅት ፖሊሶች ግለሰቡን መሬት ላይ እንደጣሉት አማር ለቢቢሲ ገልጿል።

የግሬተር ማንችስተር ከንቲባ አንዲ ቡርንሀም “ቪድዮው ይረብሻል። በጣም አስጊ ነው” ብለዋል።

ለፖሊስ ኃላፊው ስጋታቸውን መግለጻቸውንም አክለዋል።

ብሔራዊ የጥቁር ፖሊሶች ማኅበር ፕሬዝዳንት አንዲ ጆርጅ “ቪድዮውን ለመመልከት ይከብዳል” ብለዋል።

“ፖሊስ መሆን ቀላል ሥራ ባይሆንም ከፍተኛ የሙያ ብቃት ይጠበቅብናል” ብለው በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትር ደሚ ዲያና ጆንሰን “አስደንጋጩን ቪድዮ አይቻለሁ። ከሕዝቡ የነተሳውን ቁጣም እረዳለሁ” ብለዋል።