በኔፓል 18 ሰዎች ከሞቱበት የአውሮፕላን አደጋ ፓይለቱ ብቻ በሕይወት ተረፈ

የፎቶው ባለመብት, Nepali Police
በኔፓል 18 ሰዎች ከሞቱበት የአውሮፕላን አደጋ የአውሮፕላኑ አብራሪ ብቻ በሕይወት ተረፈ።
አውሮፕላኑ ከመከስከሱ ከሰከንዶች በፊት በረራውን የሚቆጣጠርበት ክፍል በእቃ ጫኝ ኮንቴነር ተመቶ፣ ተገንጥሎ በመውደቁ በሕይወት መትረፍ እንደቻለ ተገልጿል።
ካፕቴን ማኒሽ ራታና ሻክያ በካታማንዱ አየር ማረፊያ ከደረሰው አደጋ ብቸኛው በሕይወት የተረፈ ሰው ነው።
አሁን በኔፓል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት ሲሆን፣ ለቤተሰቦቹ “ደኅና ነኝ” ብሎ መናገር እንደቻለም ተገልጿል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ፓይለቱ በረራውን የሚቆጣጠርበት ክፍል ተገንጥሎ ከወደቀ በኋላ በእሳት ሊያያዝ ሲል ነው በቦታው የደረሱት።
“ለመተንፈስ ተቸግሮ ነበር። መስኮቱን ሰብረን በፍጥነት አወጣነው” ሲሉ የኔፓል ፖሊስ ዋና አዛዥ ዳምባር ቢሽዋካርማ ተናግረዋል።
“ፊቱ በደም ተሸፍኖ ነበር። ወደ ሆስፒታል ስንወስደው መናገር ይችል ነበር” ብለዋል።
የኔፓል ሲቪል አቪዬሽን ሚኒስትር ባድሪ ፓንዲ፣ አውሮፕላኑ በረራ እንደጀመረ ድንገት ወደ ቀኝ እንደታጠፈና በአውሮፕላን ማረፊያው ምሥራቃዊ የመንደርደሪያ አካባቢ እንደተከሰከሰ አስረድተዋል።
የደኅንነት ካሜራ ተንቀሳቃሽ ምሥል እንደሚያሳየው፣ አውሮፕላኑ ከአየር ማረፊያው ከተነሳ በኋላ በእሳት የጋየ ሲሆን በቅርብ ርቀት በሚገኝ ተራራማ ስፍራ ተከስክሷል።
“ጫፉን ኮንቴነር መቶት ነበር። ከዚያም ራቅ ብሎ ተከሰከሰ። በረራ መቆጣጠሪያው ክፍል ግን ከኮንቴነሩ ጋር ስለተያያዘ አውሮፕላን አብራሪው በሕይት መትረፍ ችሏል” ብለዋል ሚኒስትሩ።

የፎቶው ባለመብት, Nepali Police
የተቀረው የአውሮፕላኑ ክፍል በአካባቢው ከሚገኝ ኮረብታ ጋር እንደተጋጨና ተሰባብሮ በእሳት እንደጋየም አክለዋል።
አብራሪው አደጋው በደረሰ “በአምስት ደቂቃ ውስጥ” ሕይወቱን ማትረፍ ተችሏል።
የኔፓል መከላከያ ባወጣው መግለጫ አብራሪው “በጣም ፈርቶ የነበረ ቢሆንም ራሱን አልሳተም ነበር”።
የወታደር መኪና ወደ ሆስፒታል ወዲያውኑ ወስዶታል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር መና ታፓ እንዳሉት፣ አብራሪው ጭንቅላቱና ፊቱ ላይ ጉዳት ደርሶበታል። ጀርባው ላይ የተሰበሩ አጥንቶችን ለመጠገን ቀዶ ሕክምናም ይደረግለታል።
“በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ያሉ ጉዳቶችን አክመናል። በጭንቅላት ሕክምና ክፍል ክትትል እየተደረገለት ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Nepali Police
ትናንት የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር ኬፒ ሻርማ አብራሪው ያለበትን ሆስፒታል ጎብኝተው ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝተዋል።
የአደጋው መንስዔ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል።
ትሪቡህቫን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳለው፣ ቅድመ ምርመራ የሚያሳየው አውሮፕላኑ ለአብራሪው የተሳሳተ አቅጣጫ እንደጠቆመ ነው።
“በረራውን እንደጀመረ መጓዝ የነበረበት ወደ ግራ ቢሆንም ወደ ቀኝ ነው የታጠፈው” ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ኔፓል ከበረራ ጋር የተያያዘ እክል በተደጋጋሚ እንደሚገጥማት ትተቻለች።
እአአ በ2023 በደረሰ አደጋ 72 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ መንስዔው አብራሪው በስህተት የአውሮፕላኑን የኤሌክትሪክ ኃይል መቁረጡ ነው።ከ1992 ወዲህ የደረሰ ከባድ የአውሮፕላን አደጋ ነው።
በ1992 በደረሰው አደጋ በፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የተሳፈሩ 167 ሰዎች ካታማንዱ አየር ማረፊያ ሲቃረቡ ሞተዋል።
ሳሩያ አየር መንገድ በኔፓል አምስት መዳረሻዎች አሉት። ሦስት ቦምባርዲየር ሲአርጄ 200-ጀት አውሮፕላኖች እንዳሉት ድረ ገጹ ይጠቁማል።












