የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ በአጠቃላይ 16.6 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መወሰኑን አስታወቀ

የዓለም ባንክ በድጋፍ፣ ለዕዳ ሽግሽግ እና ለረዥም ጊዜ ብድር ክፍያ በአጠቃላይ 16.6 ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ባንኩ ማክሰኞ ምሽት ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ “የኢትዮጵያን የመጀመሪያ እና ቀጣይነት ያለው አካታች ዕድገት የልማት ማሻሻያ ፖሊሲ እርምጃ” ማጽደቁን አስታውቋል።

የባንኩ ቦርድ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እና ብድር ማጽደቁን አስታውቆ፤ ከዚህ መካከል የ1 ቢሊዮን ዶላሩ ድጋፍ ሲሆን፣ 500 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ብድር ነው።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ የለያዩ ማዕቀፎችንም ይፋ አድርጓል። በዚህ መሠረት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ ድጋፍ ይፋ ተደርጓል።

የዕዳ ክፍያ እንዲራዘም 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለአገሪቱ ተደርጓል።

ለበጀት ድጎማ ደግሞ በየዓመቱ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚውል የ6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ፣ ለዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ትብብር 320 ሚሊዮን ዶላር፣ 1.15 ቢሊዮን ዶላር የባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ እና 2.1 ቢሊዮን ዶላር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ትብብር ለኢንቨስትመንት ታገኛለች።

ይህ የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራውን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በገበያ ሥርዓት አማካይነት እንዲወሰን አድርጓል።

መንግሥት የወሰደው እርምጃ ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ጠቀሜታ አለው ይላል።

የውጭ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተገቢው መንገድ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን እና ለነዋሪዎች እንዲሁም ለአምራቾች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ያግዛል ብሏል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከወጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እና የገበያ ድርሻቸው እንዲያድግ ያበረታታል የተባለ ሲሆን፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማሻሻል አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካቶች የመንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያ የገበያ ንረትን የከፋ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ አሉታዊ ውጤቶችን ይዞ ይመጣል በሚል ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።