ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጭኮን እያመረተች ለአገር ውስጥ እና ለባሕር ማዶ ገበያ እያቀረበች ያለችው ወጣት
የባሕል ምግቦች ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጋር የተሳሰሩበት ገመድ ጥብቅ ነው። በዓላትን ከማድመቅ ባሻገር ማንነትን፣ የተወለዱበትን አካባቢ፣ የቤተሰብን ትዝታ አጣምረው ይዘዋሉ።
በዚህም የተነሳ በአገር ውስጥ የሚኖሩም ሆነ ከአገረ ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የባሕል ምግቦችን ከቻሉ በራሳቸው ቤት ውስጥ ማዘጋጀት፣ ችሎታው ከሌላቸው ደግሞ የተዘጋጀውን ከገበያ ገዝተው በመጠቀም ከባሕላቸው ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለማጥበቅ እና ፍላጎታቸውን ለማሟላት ይጥራሉ።
ይህንን ያስተዋሉ በርካታ ግለሰቦች እና ድርጅቶችም በንግዱ አዋጭነት እየተሳቡ ቢዝነሱን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከልም ሃያት ቱባ ጉዬ አንዷ ናት። ሃያት ጭኮን ለአገር ውስጥ እና ለባህር ማዶ ገበያ ታቀርባለች።
“ለጭኮ ያለኝ ፍቅር ነው በንግድ ሥራው ላይ እንድሰማራ ያነሳሳኝ” ትላለች ወ/ት ሃያት እንዴት ወደ ጭኮ ንግድ እንደገባች ስትናገር።
ወ/ት ሃያት ምዕራብ አርሲ አዳባ ነው የተወለደችው።
ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ ጭኮ መመገብ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
“ጭኮ ባሕላዊ ምግብ ነው። ተወልጄ ባደግኩበት ስፍራ ደግሞ የተለየ ቦታ አለው። ትልልቅ ዝግጅት በሚኖርበት ወቅት ነው የሚቀርበው። በሠርግ ሥነ ስርዓት ላይም ይቀርባል። ከሽምግልና በኋላም እንደ መልካም ምኞት መግለጫ የሚቀርብ ምግብ ነው።”
ሃያት በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ ቡራዩ ከተማ ጭኮ በማዘጋጀት ለአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ላሏት ደንበኞች ታቀርባለች።
ለጭኮ ያላት ክብር እና ፍቅር በዚህ ሥራ ላይ እንድትሰማራ እንዳነሳሳት የምትናገረው ሃያት፣ ሰዎች ከውጭ አገር ሲመጡ ጭኮን ይዘው ለመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው በማየት ለዚህ ሥራ ሌላ መነሻ ምክንያት እንደሆናት ትናገራለች።
“ብዙ ሰዎች ከውጭ አገር ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ወደ አገር ቤት ሲመጡ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ጭኮ አዘጋጁልን የሚል ነው። ብዙ ሰው ጭኮን ይዞ ወደ መጣበት መሄድ ይፈልጋል። ለዚህም ደግሞ ቤተሰብ ለማዘጋጀት ይቸገራል። እኔም በጥሩ መንገድ ባዘጋጅ ይህንን ፍላጎት አሟላለሁ በሚል መነሻ ነው ሥራውን የጀመርኩት።”
ሃያት ጭኮን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጓትን ግብዓቶችን ከአዳባ በማምጣት፣ ቡራዩ ከተማ ላይ ደረጃውን በጠበቀ መልክ በማዘጋጀት ለደንበኞቿ እያቀረበች መሆኗን ትናገራለች።
“ገብስ ቅቤ እና ቅመማ ቅመሞችን እዚያው አዳባ ላይ አዘጋጃለሁ። ምክንያቱም የቤት ጣዕም እንዲኖረው አስቤ ነው። ከዚያም አምጥቼ ቡራዩ ላይ በማደባለቅ አዘጋጅቼ ለደንበኞቼ አቀርባለሁ።”
የዚህ ምግብ ዝግጅትም ከየትኛውም የእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መልክ ከተጠናቀቀ በኋላ ታሽጎ ለደንበኞች እንደሚቀርብ ታስረዳለች።
“የምንሰራው በመኖርያ ቤታችን ውስጥ በማሽን ነው። በእጅ አይነካም። ደንበኞቼ በአብዛኛው በኦንላይን ነው የሚያዙኝ። እኔ ደግሞ ትዕዛዛቸውን ተቀብዬ እነርሱ በፈለጉት ሰዓት አቀርብላቸዋለሁ።”
ሃያት ይህንን የጭኮ ንግድ ከጀመረች ዓመት ሊሞላት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከአገር ውጭ እና ከባሕር ማዶ የደንበኞቿ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ትገልጻለች።
“ይህ የጭኮ ንግድ እስካሁን አልተሰራበትም። አሁን ግን የሰው ፍላጎት እያደገ ነው። እኔም ትዕዛዞችን እየተቀበልኩ ነው። በአገር ውስጥ አንዳንድ ድርጅቶች በኬክ ፈንታ ጭኮን እየተጠቀሙ ስለሆነ እነርሱም ያዙኛል” በማለት ለዚህ ባሕላዊ ምግብ ያለው ፍላጎት እያደገ መጥቷል ትላለች።
ከዚህም በተጨማሪ በቅርብ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ላይም ይህንኑ የጭኮ ምግብ ማቅረቧን የምትናገረው ወ/ት ሃያት፣ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ መሪዎች ጭምር ከቀመሱ በኋላ እንደ ወደዱት ገልጸውላታል።
ሃያት በቋሚነት ተቀጥራ የምትሠራበት ድርጅት ቢኖርም፣ ለምግቡ ካላት ፍቅር የተነሳ በቤት ውስጥ እያዘጋጀች ለገበያ ታቀርባለች።
“እኔ በቋሚነት የምሠራው የግል ድርጅት ውስጥ ነው። ጭኮ የማዘጋጀቱን ሥራ ስለምወደው ጀመርኩት አንጂ እንደ ቢዝነስ አስቤው አልነበረም። አሁን ግን ተፈላጊነቱ በጣም ጨምሯል። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭም ሰዎች ለጭኮ ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል” በማለት ገበያዋ ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ትናገራለች።
ከዚህም የተነሳ የባሕላዊ ምግብ የሆነውን ጭኮ በዘመናዊ መንገድ በማስፋፋት በሰፊው ለማስተዋወቅ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ እና በውጭ በስፋት ለማቅረብ ዕቅድ አላት።