ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጫማ የመሥራት ጥበብን ከኢንተርኔት ተምሮ ዘመናዊ ጫማዎችን የሚሠራው ወጣት
ፍራኦል ከወላጆቹ የተማረው የእንጨት እና የብረታ ብረት ሙያ አለው።
በትምህርት ደግሞ አምቦ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ያጠናው የገጠር ልማት እውቀትም በእጁ ነው።
ከሁሉም ግን ልቡን የሚያሸፍተው ጫማ ነው።
ጫማን በአዲስ መልኩ ዲዛይን ማድረግ፣ አዳዲስ ፋሽኖችን መሞከር የሁልጊዜም ህልሙ ነው።
ፍራኦል ለጫማ ዲዛይኖች ካለው ፍቅር የተነሳ ኢንተርኔት ላይ መዋል ጀመረ።
የጫማ ሥራን ሀሁ ከኢንተርኔት ተማረ።
የአምቦ ነዋሪ የሆነው ፍራኦል፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ቤተሰቦቹ ይሰሩት የነበረውን የእንጨት እና የብረታ ብረት ሥራ ሲያግዝ ነው ያደገው።
ፍራኦል ለረዥም ጊዜ ሲሠራበት ከነበረው የራሱ እና የቤተሰቦቹ የእንጨት እና የብረታ ብረት ሥራ እንዲሁም ትምህርቱን ትቶ ‘በጣም እወደዋለሁ፤ ስጦታዬ ነው’ ወዳለው የጫማ ሥራ ተጠቃሎ ከገባ ሦስት ዓመት ሆኖታል።
“ጫማ እወዳለሁ። በተቻለኝ አቅምም ፋሽን ለመከተል እሞክራለሁ” የሚለው ፍራኦል፣ ሙሉ በሙሉ በራሱ የጫማ መሥራት የጀመረው በአጋጣሚ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ ጫማ የመሥራት ሃሳብ ብልጭ ያለለትን ጊዜ ሲያስታውስ “አንድ ጫማ ገዝቼ በኋላ ዲዛይኑን ጠላሁት። ያወጣሁበት ገንዘብ ቆጭቶኝ በትኜ ለምን እንደምፈልገው አልሰራውም ስል አሰብኩ” ይላል።
ፍራኦል በዚህ ጊዜ ጫማ የሚሰፋበት ማሽን አልነበረውም። ወስፌ እና ጅማት ክር ተጠቅሞ ጫማውን ወደ ሚፈልገው ዲዛይን ቀየረው።
“በራሴ ዲዛይን ሌላ ነገር ጨምሬበት መልሼ ሠራሁት። ከዚያም ‘እንዴ ጫማ መሥራት እችላለሁ’ ብዬ አሰብኩ።”
“ጫማ ሳይ ይህንን እንዲህ ባደርገው፣ ይህ ደግሞ እንዲህ ቢሆን የሚል ሃሳብ ሁሌም አእምሮዬ ውስጥ ይመላለሳል” የሚለው ፍራኦል፣ ሙሉ በሙሉ ዲዛይኑን አውጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራው ጫማ፣ ጂንስ ሱሪ እና ያለቀ የመኪና ጎማን አንደ ግብዓት ተጠቅሞ ነው።
“ከላዩ ጂንስ በዲዛይን ሠራሁ፣ ሶሉን ደግሞ ያገለገለ የመኪና ጎማ ተጠቀምኩ” ይላል።
ፍራኦል በዚህ መልኩ ዲዛይን ያደረገውን የመጀመሪያ ጫማን ለጓደኛው በስጦታ መልክ ሰጠ። አሻሽሎ የሠራውን ሁለተኛ ጫማ ደግሞ እርሱ አጌጠበት።
ከዚህ በመቀጠል ነው ሰፈር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አይተው ስለወደዱት፣ እንዲሠራላቸው ይጠይቁት ጀመር።
“ብዙ ሰው ሥራልን ይለኝ ጀመር። እኔም እየሠራሁ 300 እና 400 ብር መሸጥ ጀመርኩ። ትልቁ የሸጥኩበት ዋጋ 600 ነበር።”
ፍራኦል ይህ የጫማ ሥራ በጣም ደስታ የሚሰጠው ስለሆነ ያጠራቀመውን ገንዘብ ሁሉ አፍስሶበት ማሽን እና ሌሎች ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ገዛ።
ሙያውን ከኢንተርኔት
ፍራኦል ለተለያዩ ሙያዎች ፍቅር ያለው ቢሆንም፣ በተለየ ደግሞ ለጫማ ሥራ ከሁሉ ከፍ ያለ ፍቅር ስለነበረው አዲስ አበባ ሄዶ ቆዳ እየገዛ ይለማመድ ነበር።
ስለጫማ ሥራ ሙያ መደበኛ ሥልጠና ያልወሰደው ፍራኦል ሙያውን ለማዳበር ኢንተርኔትን በማሰስ በበይነ መረብ ላይ የሞላውን እውቀት በሰፊው መገብየቱን ይናገራል።
“ኢንተርኔት ቤቴ አስገብቼ ትኩረቴን ሁሉ በመስጠት እያንዳንዱን ነገር ለማወቅ ሞከርኩ። ዲዛይን ከማውጣት እስከ መጨረሻው የጫማ ምርት ሂደት ያለውን ሥራ የተማርኩት ከዚያ ላይ ነው።”
ፍራኦል በቂ እውቀት እና ክህሎት እንዳገኘ ሲያምን ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለበት ራሱን ጠየቀ።
“ፍላጎቴን መከተል አለብኝ። ብዬ ያለኝን ሁሉ እና ጊዜዬን ወደዚህ አዞርኩኝ። አንድም ጊዜ ጫማ የሚመረትበት ስፍራ በአካል ተገኝቼ አይቼ አላውቅም” ይላል ፍራኦል።
ለዚህም የከተማዋ አስተዳደር የሥራ ፈጠራን የሚያበረታቱ አካላት ልምድን እንዲቀስም እንዲያግዙት ቢጠይቅም በቂ ድጋፍ ስላላገኘ ራሱን ማስተማር እንደቀጠለ ይናገራል።
“ከኢንተርኔት የተማርኩትን ወደ ተግባር መቀየር አለብኝ ብዬ መርካቶ እየሄድኩ በ5ሺህ እና 10ሺህ ብር ቆዳ እየገዛሁ እለማመድ ነበር። ፍላጎቴ ስለነበር ገቢ ባያስገኝልኝም በጣም ደስተኛ ነበርኩ።”
አሁን ፍራኦል ጫማ የሚሰፋበት ማሽን ገዝቶ፣ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አሟልቷል። ነገር ግን አሁን ያለው ማሽን ቡትስ ጫማዎችን ለመሥራት አያስችለውም።
ይህንን ሥራ ብቻውን እንደሚሠራ የሚናገረው ፍራኦል፣ ከደንበኞቹ ትዕዛዝ እየተቀበለ የተሻለ ጥራት ያላቸው የቆዳ ጫማዎችን እያመረተ ገቢ እያገኘ ነው።
ደረጃውን የጠበቀ የጫማ ምርት ቢያንስ አራት ደረጃዎች፣ እንዲሁም ቢያንስ በአራት ሰዎች ስር ማለፍ እንዳለበት የሚገለጸው ፍራኦል፣ ሥራው ከእራሱ ባሻገር ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለው ይናገራል።
አሁን በተለያዩ ዲዛይኖች የሚሠራቸውን የቆዳ ቡትስ ጫማዎች እስከ 2000 ብር ይሸጣል።
ፍራኦል እንደሚለው አስፈላጊውን ድጋፍ እና ምቹ ሁኔታ ማግኘት ባለመቻሉ እየጨመረ የመጣውን የምርቱን ፈላጊዎች ቁጥር በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ አልቻለም።
“ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖረውም፣ በዚህ ሥራ ስኬታማ መሆኔ አይቀሬ ነው” ይላል።
ግቡን ሲናገርም ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ጫማዎችን በተለይ ‘ጀምስ ቡትስ’ የሚባሉትን የጥራት ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በአገር ውስጥ ማምረት ነው።
አክሎም የሌዘር ሶል ያላቸው ጫማዎች ከውጪ ስለሚገቡ ዋጋቸው ውድ መሆኑን ጠቅሶ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እና ጥራት ሠርቶ ለገበያ ማቅረብ ዋነኛ ፍላጎቱ ነው።
ለጫማ ሥራ ጥራት ያላቸው ግብዓቶች እና ለሥራው የሚውሉ ማሽኖች እና ቁሳቁሶች በጣም አስፈላጊ ናቸው የሚለው ፍራኦል፣ እነዚህ ከተሟሉ ከውጭ በሚመጡ ጫማዎች ደረጃ ጥራታቸውን የጠበቁ ጫማዎችን ማምረት የማይቻልበት ሁኔታ እንደሌለ ያስረዳል።