ከቻይና ጋር የተፋጠጠችው ታይዋን አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን ወደ አንድ ዓመት ልታራዝም ነው

የታይዋን ጦር አባል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታይዋኗ ፕሬዝዳንት ታይ ኢንግዋን የሀገራቸው ዜጎች የሚሰጡት አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ከ አራት ወራት ወደ አንድ አመት እንደሚራዘም አስታወቁ።

ራሷን እንደ ራስ ገዝ አስተዳደር የምትቆጥረው ደሴቲቷ፤ አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን ከአራት ወራት ወደ አንድ ዓመት ከፍ ያደረገችው ከቻይና ጋር የገባችበትን ውጥረት ተከትሎ ነው።

ፕሬዝዳንቷ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አዲሱን ውሳኔ ከቻይና ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ለመመከት የታይዋንን የመከላከል አቅም ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

“ሰላም ከሰማይ አይወርድም. . . ታይዋን በአምባገነኖች ጦር ግንባር ፊት ለፊት ትገኛለች” ብለዋል

ፕሬዝዳንቷ ወታደራዊ አገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ ዜጎች የሚወስዷቸው ስልጠናዎች ከአሜሪካና ከሌሎች ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ካላቸው በምንዋሳቸው መሳሪዎች የተጠናከር ይሆናል ብለዋል።

ጨምረውም የታይዋን የአሁኑ የመከላካያ ስርዓት ከቻይና የሚመጣውን ጽብ አጫሪነት ለመመከት በቂ አይደለም ሲሉ ጠቁመዋል።

የቻይና ጦር አቅም ከአለም ታላላቅ እና እጅግ ከተራቀቁ ሰራዊቶች መካከል አንዱ ነው።

የተይዋን ሠራዊት እንደ አውሮፓውያኑ ከ1990ዎቹ ጀምሮ እድሜያቸው ከ18 ላለፈ ወንዶች ያስቀመጠውን አስገዳጅ ስልጠና የጊዜ መጠን እየቀነሰ መጥቷል።

ቀጥለው ባሉት አስርት ዓመታት አስገዳጅ ወታደራዊ አግለግሎቶች ወደ 10 ቀጥሎም ወደ 4 ወራት ዝቅ ተደርጓል።

አዲሱ አስገዳጅ ውሳኔ ታይዋን አዲስ ፕሬዝዳንት ከምትመርጥበት የፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያው ወር ጀምሮ ተግበራዊ መደረግ ይጀምራል።

ፕሬዝዳንቷ “ይህ እጅግ ከባድ ውሳኔ ነው። ነገር ግን እንደ ፕሬዝዳንት እና እንደ ጦር ሃይሎች መሪ ብሄራዊ ጥቅማችንን እና የዲሞክራሲያችንን መንገድ ማስጠበቅ ሊሻር የማይችል ኃላፊነት” ነው ብለዋል።

አክለውም “ማንም ጦርነት አይፈልግም። . . . የቻይና ወታደራዊ ጸብ አጫሪነት ሊታይ በሚችል መልኩ እየጨመረ ነውም” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ደሴቲቱን ከጎበኙ በኃላ በቻይናና በታይዋን መካከል ያለው ውጥረት ከሯል።

በወቅቱ ቤጂንግ ታይቶ የማይታወቅ ወታደራዊ ልምምድ በታይዋን ዙሪያ በሚገኝ የውሃ አካል አድርጋ ምላሽ ሰጥታለች። ታይዋንም ልምምዱ “እጅግ ጸብ አጫሪ ነወ” ብለዋለች።

ባለፈው ጥቅምት ወር የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ በቤጂንግ በተካሄደው የኮሚኒስት ፓርቲ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ታይዋንን ለመጠቅለል ኃይል የመጠቀሙን ሀሳብ እንዳልቀየሩ ገልጸዋል።

በዛው ሳምንት የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ቻይና ከታይዋን ጋር የመዋሃድ ሃሳቧን “ከዚህ በፊት ሲጠበቅ ከነበረው ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማድረግ ትፈልጋለች” ሲሉ ጠቁመዋል።

ቻይና ተዋጊ ጀቶችን እና ድሮኖችን ጨምሮ ባለፈው ሰኞ የጦር አውሮፕላኖቿ የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው እንደገቡ ከተሰማ በኃላ እንደ አዲስ ውጥረት ነግሷል።