ኬንያ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸውን ሰብሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ የጤና ጉዳት ያመጣል በሚል ለአስርት ዓመታት እግዳ ያቆየቻቸው ሰው ሠራሽ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው የእህል ዘሮች እና የእንስሳት ምግቦች ጥቅም ላይ እንዲወሉ እና ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ፈቀደች።
ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው ሰብሎች እና የእንስሳት ምግቦች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የፈቀደችው በአገሪቱ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የተባለ የከፋ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ነው።
አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳት ዊሊያም ሩቶ በአገሪቱ የእርሻ ምርትን ለማሳደግ ፊታቸውን ወደ የዘረ-መል ማሻሻያ ወደ ተደረገባቸው ሰብሎች ያዞሩ ይመስላል።
የዊሊያም ሩቶ መንግሥት አገሪቱ ድርቅን፥ ተባዮች እና በሽታን መቋቋም የሚችሉ ዘሮች ያስፈልጓታል ብሏል።
ከአስር ዓመታት በፊት የዘረ-መል ለውጦች የተደረጉባቸው ሰብሎች ለጤና ስጋት ናቸው በሚል በኬንያ ታግደው ነበር።
ኬንያ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው ሰብሎችን የማገዷ ውሳኔ የዘረ-መል ለውጥ ተመራማሪዎች እና አምራቾች ዋነኛ መገኛ በሆነችው አሜሪካ ተቀባይት አላገኘም ነበር።
ባለፈው ሐምሌ ወር የጆ ባይደን አስተዳደር የእርሻ ምርቶችን ንግድ ማሳደግን ጨምሮ አዲስ የአጋርነት ስምምነት ከኬንያ መንግሥት ጋር ተፈራርመው ነበር።
ይህ እርምጃ ምርትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ቢታመንም አንዳንዶች ውሳኔው አርሶ አደሮችን በውጪ ኩባንያዎች እና አገራት ላይ ጥገኛ እንዳያደርጋቸው ይሰጋሉ።












