ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እናቷን ገድላ ሻንጣ ውስጥ በመክተት የተጠረጠረችው አሜሪካዊት ጥፋተኛ መሆኗን አመነች
እናቷን ገድላ ሻንጣ ውስጥ በመክተት ተጠርጥራ የነበረችው አሜሪካዊት ጥፋተኛ መሆኗን አመነች።
ግድያው የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ 2014 በኢንዶኔዥያዋ ከተማ ባሊ በሚገኝ አንድ የቅንጦት መዝናኛ ስፍራ ነው።
ወንጀሉ “የባሊ የሻንጣ ግድያ” የሚል ቅጽል ስም ያገኘ ሲሆን የ27 ዓመቷ ሄዘር ማክ እና እናቷ ወደ ባሊ የመጡትም ለመዝናናት ነበር።
ሄዘር ወንጀሉ ከተፈጸመ ከአንድ ዓመት በኋላም በኢንዶኔዥያ ተከሳ የ10 ዓመት እስር ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 2021 ከእስር ተፈታች።
አሜሪካ እንደደረሰችም ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውላለች።
አንድ የአሜሪካ ዜጋን ለመግደል በማሴር እና ፍትህን በማደናቀፍም ተከሳ ነበር።
ሄዘር የግድያ ወንጀሉን ማመኗን ተከትሎ አስርት ዓመታት እስር ይጠብቃታል ተብሏል።
አቃብያነ ህጉ በአሜሪካ የተከሰሰችበት ክስ አንድ ሰው ሁለት ጊዜ በተመሳሳይ ወንጀል ለመክሰስ የሚከለክሉ ህጎችን የማይጥስ ነው ማለታቸው በፍርድ ቤት ሰነዶች ላይ ሰፍሯል።
ለዚህም የሰጡት ምክንያት በአሜሪካ የተከሰሰችው በግድያ ሴራ ሲሆን የኢንዶኔዥያው ከዚህ ጋር የሚገናኝ አይደለም ብለዋል።
አሜሪካ በመጀመሪያ በተከሰሰሰችበት በአውሮፓውያኑ 2021 የግድያ ሴራ ሄዘር ጥፋተኛ አይደለሁም ብላም ነበር።
ከዚህም ክስ ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ ማገባደጃ ላይ ችሎቱን ለመጀመር ቀጠሮ ይዞ ነበር።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ግለሰቧ ጥፋተኝነቷን በማመኗ የእስሯን ብይን ለመወሰን ቀጠሮ ለታህሳስ ተሰጥቷል።
ሄዘር ጥፋተኛ መሆኗን ያመነችው ከአቃቤ ህግ ጋር በተደረሰ ስምምነት ሲሆን ይህም እስከ 28 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊያስቀጣት ይችላል።
የሄዘር ጠበቃ ለኒውዮርክ ፖስት እንደተናገሩት አቃብያነ ህጉ ቀደም ሲል ረዘም ያለ የእስር ቅጣት ሲያቀርቡ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን “ጥሩ የሚባል ስምምነት” ማቅረባቸውን ተከትሎ የእምነት ቃሏን ለመቀየር መወሰኗን ተናግረዋል።
ሄዘር በኢንዶኔዥያ የቀረበባት ክስ ባለጸጋና ምሁር የሆኑትን ሺላ ቮን ዊዝ ማክ የተሰኙት እናቷን ግድያ ከወንድ ጓደኛዋ ቶሚ ሼፈር ጋር በመተባበር ፈጽማለች የሚል ነው።
ጥንዶቹ ከግለሰቧ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ብር ለማግኘትም በሚል ነው የገደሏት ተብሏል።
የኢንዶኔዥያ አቃቤ ህግ ሄዘር የእናቷን አፍ ስታፍን የወንድ ጓደኛዋ ደግሞ ጭንቅላቷን በጎድጓዳ ሳህን ደጋግሞ መትቷታል ብሏል።
የሺላ አስከሬን የተገኘው በሻንጣ ውስጥ ነው።
በአሜሪካ የክስ መዝገብ ስሙ የተጠቀሰው የወንድ ጓደኛዋ ሼፈር አሁንም በኢንዶኔዥያ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለው።
ሄዘር በወቅት አስራ ስምንት ዓመቷና ነፍሰ ጡር ነበረች።
አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ሄዘር በኢንዶኔዥያ የተወሰነባት እስር በጣም የቀለለ ነው ሲሉ ወቀሳ አቅርበው ነበር።
በወቅቱ ውሳኔውን ያስተላለፉት ሶስቱ የኢንዶኔዥያ ዳኞች ቅጣቱ የቀለላት አራስ በመሆኗ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሆቴሉ ውስጥ ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ በአንድ ታክሲ የእቃ መጫኛ ላይ ትተውት ወረዱ።
የታክሲ አሽከርካሪውም ለፖሊስ ማሳወቁን ተከትሎም ግለሰቦቹ በባሊ ሌላ ሆቴል ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ።