“አሰሪዬ ሠራተኛዋን ገድላት ስመለከት ራሴን ሳትኩ”- ሕይወት ከአረብ አገር ስደት በኋላ

መሁባ ሁሴን ተወልዳ ያደገችው አማራ ክልል ወሎ ውስጥ ገርባ የሚባል አካባቢ ነው።

የ33 ዓመቷ መሁባ ፈታኝ የልጅነትን ጊዜያትን ማሳለፏን ትናገራለች።

እናትና አባቷ በመለያየታቸው ምክንያት ከስድስት ዓመቷ ጀምሮ በተለያዩ ሰዎች ቤት ተቀጥራ መሥራት ጀምራለች።

ለተቀጠረችበት ቤት ከብቶች ከመጠበቅ ባሻገር፣ ውሃ መቅዳት፣ የማገዶ እንጨት መልቀም እንዲሁም በግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩ የቤተሰቡ አባላት ምግብ በማድረስ ታገለግል ነበር።

በእርሻ ወቅት ጉልጓሎ ወይንም አረም ማረም ላይም ተሳትፎ ታደርግ አንደነበር ታስታውሳለች።

እርሷ እንደምትለው ይህንን ያደረጉት አባቷ ሲሆኑ፣ የሚከፈላትንም ደመወዝ እየተቀበሉ ወስደው ለግል ጥቅማቸው ያውሉ ነበር።

“እናቴ እና አባቴ ባለመስማማታቸው ምክንያት፣ አባቴ ከእናቴ ጋር እንድቀመጥ አይፈልግም ነበር” ትላለች ሙሀባ።

መሁባ ከብቶች ለመጠበቅ በተቀጠረችበት ቤት ይከፈላት ስለነበረው ስትናገር “በዓመት 10 ብር ነበር። እርሱንም እየመጣ የሚወስደው አባቴ ነው” ትላለች።

መሁባ የልጅነት ጉልበቷን ሁሉ አሟጣ ብታገለግላቸውም፣ በምግብ ረገድ ትበደል እንደነበር ትናገራለች።

“ከሥራው ጫና ባሻገር በቤት ውስጥ የምግብ እጥረት ነበረብኝ” የምትለው ሙሀባ፣ “ጠዋት ከቤት ስወጣ በትንሽዬ ኩባያ አሬራ ሰጥተውኝ፣ ስመለስ ማታ ደግሞ የቦሎቄ ንፍሮ ነበር የሚቀርብልኝ” ትላለች።

በዓለም ላይ 50 ሚሊዮን ሰዎች በዘመናዊ ባርነት ውስጥ ለተለያዩ የጉልበት ብዝበዛ መጋለጣቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶ ያህሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች ናቸው።

መሁባ የእድሜ እኩዮቿ ደብተር ይዘው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ስታይ ትጓጓ ነበር።

የትምህርት ፍላጎቷን ሰው ቤት እየሰራች ለማሳካት ግን አልቻለችም።

እድሜዋ ከፍ እያለ ሲመጣ እና መማር እፈልጋለሁ የሚል ጥያቄ ለወላጆቿ ስታቀርብ “እድሜሽ ለትዳር ደርሷል፤ ከአሁን በኋላ መማር አትችይም” በማለት ከለከሏት።

በዚህ ጊዜ ነው ከሰው ቤት ሠራተኝነት ወጥታ የቀን ሥራ በመጀመር ለመማር የወሰነችው።

“ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት ስወስን 13 ዓመት ይሆነኝ ነበር” ትላለች።

የቀን ሥራ ሠርታ በምታገኘው ገንዘብ የትምህርት መሳርያዎችን ገዛዝታ ትምህርት ቤት ተመዘገበች።

“በእርግጥ ከደብተር እና እስክቢርቶ የተረፈኝን ገንዘብ በሙሉ ያዋልኩት ለቤተሰቤ ነው” ብላለች።

የሚማሩ እህት እና ወንድሞች ስለነበሯት፣ እነርሱን እንዲሁም እናቷንም በአቅሟ እንደምትረዳ ትናገራለች።

ስድስተኛ ከፍል እስክትደርስ ድረስ በትምህርቷ ጎበዝ አንደነበረች የምትገልጸው ሙሀባ፣ የቀን ሥራ እየሰሩ ቤተሰብን መደገፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርትን መከታተል ፈተና ሆነባት።

ስለዚህ ለምን ወደ አረብ አገር ሄጄ የራሴንም የቤተሰቤንም ሕይወት አልለውጥም በማለት ወሰነች።

ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄደችው በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነት መሆኑን የምትናገረው መሁባ፣ ስድስት ወር ከሠራች በኋላ አሰሪዋ ደመወዟን በመከልከሏ ከምትሰራበት ቤት ጠፍታ ወጣች።

ከምትሰራበት ቤት ጠፍታ ሥራ ማግኘት ግን እንዳሰበችው ቀላል አልሆነላትም።

በደላላ አፈላልጋ ያገኘችው ሥራም ወደ ገጠር እንደነበር የምትናገረው መሁባ፣ የምትተኛው ደግሞ ከቤተሰቡ ንጽህና ቤት የሴራሚክ ወለል ላይ አነጥፋ ነበር።

“ሴራሚኩ ቀዝቃዛ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እጄን እና እግሬን ማንቀሳቀስ አቃተኝ” ስትል በወቅቱ የገጠማትን የጤና እክል ታስታውሳለች።

እጅ እና እግሯ አብጦ መንቀሳቀስ ባልቻለበት ወቅት በሳዑዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን እያስታመሟት ለአንድ ዓመት ያህል ቆየች።

ከዓመት በኋላ ግን በሳዑዲ ሰርቶ የመለወጥ ሕልሟ መክሰሙን ስትረዳ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች።

“ስመጣ ባዶ እጄን ነበር የተመለስኩት” ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።

“ለሦስተኛ ጊዜ ወደ አረብ አገር ልቤ ሸፈተ”

በኢትዮጵያ የተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች፣ የከፋ ድህነት እንዲሁም ሥራ ማጣት በርካታ ሴቶችን አደገኛ በሆነ መልኩ ወደ አረብ አገራት ሥራ ፍለጋ እንዲጓዙ ከሚገፉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በርካቶች የተጋነኑ ተስፋዎች ተነግሯቸው፣ ከፊታቸው የሚገጥማቸውን አደጋ ሳያገናዝቡ፣ በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነት ወደ አረብ አገራት ቢያመሩም፤ ያሰቡትን ሳያገኙ ቀርተው ባዶ እጃቸውን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ አሚናት አንዷ ናት።

አሚናት ወደ ዱባይ ስትሄድ 17 ዓመቷ ነበር።

ቤተሰቦቿ “እኔን የማስተማር አቅማቸው ዝቅተኛ ስለነበር ነው ወደ ስደት የሄድኩት” ትላለች።

ወደ ዱባይ የሄደችው በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነት እንደነበር የምትናገረው አሚናት፣ በወቅቱ 500 ድርሃም የወር ደሞዟ እንደሚሆን ተነግሯታል።

ያኔ ደግሞ ይህ 500 ድርሃም ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር፣ ሁለት ሺህ ብር አካባቢ ስለሚመጣ ደስተኛ ሆነች።

ዱባይ ደርሳ ሥራ ስትጀምር አሰሪዋ እጅግ ኃይለኛ መሆኗን ተረዳች።

ሥራውም እጅግ ከባድ ነበር። ከቤተሰቦቿም ጋር ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር መደዋወል አትችልም። ከቤትም መውጣት የተከለከለ ነው።

አሚናት ከአሰሪዋ ጋር ለመግባባት የሚያስችላት የቋንቋ ችሎታም አልነበራትም።

“ከእኔ በፊት ገብታ የነበረችው ልጅ ትንሽ ትንሽ ቋንቋቸውን ትችል ነበር” ትላለች።

የአሰሪዋን ስሜት ለመረዳት የድምጿን እና የፊቷን መለዋወጥ ብቻ እያየች የምትሰራው አሚናት፣ አንድ ቀን የተፈጠረው ነገር የሕይወት አጋጣሚዋን ቀየረው።

“አሰሪዬ ከእኔ ቀድማ ቤት ውስጥ ትሰራ ከነበረችው ልጅ ጋር ስትጣላ፣ ገደለቻት” ትላለች ሁኔታውን ስታስታውስ።

“አሰሪዬ ሠራተኛዋን ገድላት ስመለከት ራሴን ሳትኩ” የምትለው አሚናት የአእምሮ ጤናዋ ታወከ።

በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ አደረጓት። ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ ግን ባዶ እግሯን እንደነበረች፣ በእጇ ላይ ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳልነበር ታስታውሳለች።

ቤተሰቦቿ ወደሚገኙበት ደሴ ለመሳፈር የሚያስፈልጋትን ገንዘብ፣ ከመንገደኞች ተዋጥቶላት መምጣቷን ትናገራለች።

“ትንሽ አእምሮዬ ስለታወከ ቤተሰብ ጋር ሄጄም ለመቀመጥ ከባድ ነበር” ትላለች አሚናት።

ሠርቶ የመለወጥ ሕልሟ በደረሰባት የአእምሮ መታወክ የተስተጓጎለው አሚናት፣ ትንሽ ከተረጋጋች በኋላ ዳግመኛ ወደ አረብ አገር ሄዶ ሠርቶ ለመለወጥ አሰበች።

“በእርግጥ የደረሰብኝንም እያስታወስኩ ነበር። ነገር ግን አንዱ መጥፎ ቢሆን ሌላኛው አይሆንብኝም ብዬ ወሰንኩ” ትላለች።

ከዚያ ተመልሳ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ብትሄድም፣ የተወሰነ ጊዜ ከሠራች በኋላ ጓደኞቿ የሚከፈላት አነስተኛ በመሆኑ ወጥታ በግሏ መሥራት እንድትጀምር መከሯት።

ምክራቸውን ሰምታ ብትወጣም፣ እንደሷው ሕገወጥ ሆኖ ከሚኖር ልጅ ጋር የጀመረችው የፍቅር ግንኙነት እርግዝናን አስከተለ።

ከዚህ በኋላ በሳዑዲ መቆየት ስላልቻለች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ወለደች።

ወልዳ ተኝታም “ተመልሼ በባሕር መሄድ እቃጣ ነበር” ትላለች።

ሠርቶ ለመለወጥ የሚያስችል፣ ጥሩ ገቢ የምታገኝበት ሥራ መሥራት በአገር ውስጥ ማግኘት አለመቻሏ፣ ልቧን ለሦስተኛ ጊዜ ወደ አረብ አገር እንዲሸፍት አደረገው።

ሁለተኛ ልጇን ከወለደች በኋላ ግን ከዘመድም፣ ከጓደኛም ተበድራ ትንሽ ነገር ለመጀመር ወስና ‘ፓስቲ’ እየጠበሰች መሸጥ ጀመረች።

“በእግሬ ወደ አገሬ ተመለስኩ”

የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደሚያሳያው በዓለም ላይ 75.6 ሚሊዮን የቤት ውስጥ ሠራተኞች አሉ።

ይህንን ቁጥር በአፍሪካ ብቻ ብናየው 9.6 ሚሊዮን ሰዎች በቤት ውስጥ ሠራተኝነት ተቀጥረው ይሰራሉ።

በቤት ውስጥ ሠራተኝነት ተቀጥረው ከሚሰሩ ሰዎች መካከል ደግሞ 76̀ በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።

በእርግጥ የቤት ውስጥ ሠራተኝነት ለበርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል ቢፈጥርም፣ በዚያው ልክ ደግሞ ዝቅተኛ ተከፋይ፣ ዝቅተኛ ዋጋ የሚሰጣቸው እንዲሁም ረዥም ሰዓት ያለ እረፍት የሚሰሩ በመሆኑ የጉልበት ብዝበዛ ይደርስባቸዋል።

በተለይ በሕገወጥ መልኩ ወደዚህ ሥራ የሚገቡ ሰዎች ለጥቃት እና ለዘመናዊ ባርነት የተጋለጡ ናቸው።

የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ታገሰች ዳና ደግሞ ለዚህ ሌላዋ ማሳያ ትሆናለች።

ታገሰች ለምን ወደ ሱዳን እንደሄደች ስትጠየቅ “የልጆቼን ጉሮሮ መድፈን አቃተኝ” ትላለች።

ማጣት መቀነቷን፣ ችግር ማጀቷን ሲፈትነው ልጆቿን እና ባለቤቷን ትታ ወደ ሱዳን ለመሰደድ ሻንጣዋን ሸካከፈች።

ባለቤቷ በግብርና ሥራ ቢተዳደርም ያ ግን የቤተሰቡን ፍጆታ ሊያሟላ አልቻለም። በእርግጥ ባለቤቷ ልጆቿን እና እርሱን ትታ ስደት መምረጧ አልተዋጠለትም።

“ሰዎች ከአገር ቢወጡ ጥሩ ነው፤ ሠርቶ ራስን መለወጥ ይቻላል” ሲሉ ትሰማ ስለነበር የባለቤቷን ተቃውሞ ጆሮ ነፈገችው።

ደላላው ገንዘብ የሚያበድራት ካገኘች በአጭር ጊዜ ሠርታ ልትከፍላቸው እንደምትችል ስለነገራት አባቷን ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ እንዲሰጣት ለመነች።

አባቷም ልመናዋን ተቀብለው ብሩን ሲያበድሯት የተጠየቀችውን ከፍላ ወደ ሱዳን ጉዞ ጀመረች።

በእግር እና በመኪና ያደረጉት ጉዞ ፈታኝ እንደነበር የምትናገረው ታገሰች፣ ሱዳን ውስጥ ደላላው ሥራ አግኝቶላት ተቀጠረች።

ማለዳ ተነስቶ እስከሚመሽ ድረስ ብትሰራም አሰሪዋን ግን ማስደሰት አልቻለችም።

በየዕለቱ ድብደባ ይደርስባት እንደነበር የምትናገረው ታገሰች፣ በወር 1200 የሱዳን ፓውንድ ደመወዝ ሊከፈላት ተስማማታ የነበረ ቢሆንም አሰሪዋ ደስተኛ ባለመሆኑ ተባረረች።

በአገሩ የምታውቀው ማንም ሰው ስላልነበረ የምታደርገው ሁሉ ግራ ገባት።

“ከአምስት ወር በኋላም በእግሬ ወደ አገር ቤት ተመለስኩ” ትላለች።

ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላስ?

በ2021 አክሽን ኤይድ በጋና እና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ባርነትን ለመቀልበስ በሚል አንድ ፕሮጀክት አስተዋውቆ ነበር።

በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ከአረብ አገር የተመለሱ እና ለተለያየ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን የአክሽን ኤይድ መረጃ ያሳያል።

የአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ትነበብ ብርሃኔ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የሕገ ወጥ ስደት መሠረታዊ የሆነ የሥራ ዕድል አለመኖር ቁልፉ ችግር ነው” ይላሉ።

አክለውም ሴቶች መሠረታዊ የሆነ የሥራ ዕድል ቢመቻቸላቸው ሕገወጥ ስደትን እና የሰዎች ዝውውርን በተጨባጭ ሁኔታ መቀነስ እንደሚቻል ይጠቅሳሉ።

የአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ቢሮ ከኖርዌይ መንግሥት ባገኘው ድጋፍ በአማራ፣ በደቡብ ክልሎች እና አዲስ አበባ ከተማ 600 ከስደት የተመለሱ ሴትችን መደገፉን ጨምረው ገልጸዋል።

አክሽን ኤይድ እነዚህ ሴቶች የንግድ ክህሎት እና የቁጠባ ሥልጠና እንዲያገኙ ከተለያዩ አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይሰራል።

ታገሰች ሁለቱን ሥልጠናዎች ከወሰደች እና ስምንት ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል ተቀብላ መጀመሪያ የገዛችው አህያ መሆኑን ትናገራለች።

በቀሪው ብር ደግሞ በቆሎ በመግዛት የራሷን ንግድ ጀመረች።

ይህ ሥልጠና እና ብድር ግን ታገሰች ብቻ ሳትሆን ሙሀባ ሁሴንን እና አሚናት ሠይድንም ሕይወታችን ለመለወጥ ደፋ ቀና እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ሙሀባ የባልትና ንግድ ሥራ ውስጥ መግባቷን ስትናገር አሚናት ደግሞ ሳምቡሳ እየሸጠች ልጆቿን ታሳድጋለች።

ሙሀባ ከሳዑዲ ከተመለሰች በኋላ የወለደቻቸውን ሁለት ልጆች አስተምሮ ለቁምነገር የማብቃት ሕልም እንዳላት ስትናገር፣ አሚናት ደግሞ ዳግመኛ ፊቴን ወደ አረብ አገር አላዞርም ለሌሎችም ይህንን አልመክርም ትላለች።

የአክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር፣ ትነበብ ብርሃኔ “ሥራ ፍለጋ የሚሰደዱትን ጨምሮ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የቤት ውስጥ ሠራተኞች መብት መታገል አለብን” ይላሉ።

አክለውም “ለሚደርስባቸው እንግልት እና ጥቃት ቀጣሪዎች እና መንግሥት ተጠያቂ እንዲሆኑም መሥራት አለብን” ብለዋል።

አክለውም መንግሥት የሁሉንም የቤት ሠራተኞች ሰብዓዊ መብት እንዲያስጠብቅ እና እንዲያስከብር የዓለም አቀፉ ሠራተኞች ድርጅት ኮንቬንሽን 189ን ማጽደቅ እንደሚኖርበት ያሳስባሉ።

በአገር ውስጥ ያሉ ሕጎችም እነዚህ ወገኖች እኩል የሠራተኛ መብት እና ማኅበራዊ ጥበቃ እንዲያገኙ ከለላ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።