በ20 አገራት የሚገኙ ሴቶችን በበይነመረብ የወሲብ ብዝበዛ የፈፀመው አውስትራሊያዊ ተፈረደበት

ሙሐመድ ዜይን ኡል አቢዴን ራሺድ፣ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው በ20 አገራት ከሚገኙ 286 ሰዎች ጋር በተያያዘ በተመሰረተበት 119 ክሶች ነው።

የፎቶው ባለመብት, ABC News/Hugh Sando

በአውስትራሊያ በመላው ዓለም ከሚገኙ ከመቶ በላይ ሴቶችን ካሜራ ፊት ወሲባዊ ትዕይንት እንዲያሳዩ በማድረግ ስማቸውን ያጠፋ ነበር የተባለ ''ዝነኛ ዩቲዩበር'' የ17 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ሙሐመድ ዜይን ኡል አቢዴን ራሺድ፣ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ዩኬን፣ አሜሪካን፣ ጃፓን እና ፈረንሳይን ጨምሮ በ20 አገራት ከሚገኙ 286 ሰዎች ጋር በተያያዘ በተመሰረተበት 119 ክሶች ነው።

ተከሳሹ ዒላማ ካደረጋቸው ሴቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ16 በታች ነበር።

የ29 ዓመቱ ተከሳሽ ሴቶቹን ካጠመደ በኋላ የተላላካቸውን ልቅ መልዕክቶች እና ምስሎች ለወዳጆቻቸው እልካለሁ እያለ በማስፈራራት የተለያዩ ጥቃቶችን ያደርስ ነበር ተብሏል።

የአውስትራሊያ ባለስልጣናት በአገሪቱ ታሪክ “እጅግ የከፋ የወሲብ ብዝበዛ ክስ” ነው ብለዋል።

የአውስትራሊያ የፌደራል ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ዴቪድ ማክሊን “ግለሰቡ የጥቃት ሰለባ ያደረጋቸው ላይ ያሳየው ጭካኔ፣ ክብርን ማዋረድ እና ፍርሀት በአውስትራሊያ ከታዩ የወሲብ ብዝበዛ ክሶች ሁሉ የከፋው ነው” ብለዋል።

“እንዲህ ዓይነቱ በበይነ መረብ የሚደረግ የወሲብ ብዝበዛ እና ጥቃት በጣም አደገኛ እና ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የአእምሮ ቁስለት ትቶ ያልፋል” ሲሉም አክለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ውሳኔውን ያሳለፉት ዳኛ አማንዳ ቡሮውስ ራሺድ የፈጸመው ወንጀል በአገሪቱ ውስጥ “ሊስተካከለው የሚችል ሌላ ወንጀል የለም” ማለታቸውን የአውስትራሊያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤቢሲ) ዘግቧል።

ራሺድ በበይነ መረብ ላይ ሴቶቹን ለወሲብ ከማጥመዱ እና ከማማለሉ በፊት ራሱን የ15 ዓመት አሜሪካዊ ዝነኛ ዩቲዩበር አድርጎ ያቀርብ እንደነበር ተነግሯል።

ከዚያ በኋላ እርሱ ፈጽሙ የሚላቸውን አጸያፊ የወሲብ ትዕይንቶች፣ አንዳንዴ ቤት ውስጥ ካሉ እንስሳት እና ሕጻናት ጋር ሳይቀር፣ ካልፈጸሙ የተላላኳቸውን መልዕክቶች ለጓደኞቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው እንደሚልክ ያስፈራራ ነበር።

ራሺድ በተደጋጋሚ ለሴቶች ጥላቻ ካላቸው የበይነ መረብ ማኅበረሰብ አባላት ጋር በመሆን፣ አንዳንዴ 98 ሰዎች ያህል በተገኙበት፣ በቀጥታ ስርጭት የሚፈፀሙ አስነዋሪ የወሲብ ድርጊቶችን እንዲመለከቱ ያደርግ እንደነበር ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ ተመስክሮበታል።

ግለሰቡ ዒላማ ያደረጋቸው አብዛኞቹ ታዳጊዎች ራሳቸውን ለማጥፋት መሞከራቸውን የነገሩት ሲሆን አንድ ታዳጊ ራሷ ላይ ጉዳት ስታደርስ የሚያሳይ ምሰል ልኮለት ነበር ተብሏል።

ነገር ግን ራሺድ ያሉበትን “ከፍተኛ ፍርሀት” እና “ከፍተኛ ጭንቀት” እያወቀም ማስፈራራቱን እና መወንጀሉን እንደቀጠለበት ዳኛዋ መናገራቸውን የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኀን፣ ኤቢሲ፣ ዘግቧል።

ራሺድ የተያዘው በ2020 ኢንተርፖል እና የአሜሪካ ወንጀል መርማሪዎች የአውስትራሊያ ባለስልጣናትን ካገኙ በኋላ ነው።

ራሺድ ይህንን ክሱን ሲከታተል የ14 ዓመት ታዳጊን መኪናው ውስጥ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈጸም ወንጀል ተከስሶ የአምስት ዓመት ፍርድ ተፈርዶበት በማረሚያ ቤት ነበር።