ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮንጎ ግጭት ምክንያት ሩዋንዳ ከቤልጂየም ጋር ያላትን ግንኙነት አቋረጠች
ሩዋንዳ ከቤልጂየም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች።
ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግጭት ጋር በተያያዘ ቤልጂየም ሩዋንዳን "በተደጋጋሚ አናንቃለች" በሚል ነው ሩዋንዳ ግንኙነቷን ለማቋረጥ የወሰነችው።
ሩዋንዳ ለአማጺ ቡድኑ ኤም23 በምታደርገው ድጋፍ ምክንያት የአውሮፓ አገራት ማዕቀብ እንዲጥሉባት ቤልጄም ጥሪ ስታደርግ ቆይታለች።
የቤልጂየም ዲፕሎማቶች ኪጋሊን ለቀው እንዲወጡ 48 ሰዓታት ተሰጥቷቸዋል።
የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ቤልጄም የሩዋንዳ እርምጃ "ያልተመጣጠነ" ነው ስትል ወቅሳ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥም አስታውቃለች።
አሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት ሩዋንዳ ለኤም23 ድጋፍ እየሰጠች ነው ቢሉም ሩዋንዳ ሐሰት ነው ብላለች።
ሩዋንዳ ቤልጂየምን "የቅኝ ግዛት ቅዠቷን ማስቀጠል ትፈልጋለች" ስትል ከስሳለች።
"በቀጠናዊው ግጭት ወገንተኛ የሆነችው ቤልጄም ከሩዋንዳ በተጻራሪ ቆማለች። ውሸትና ማጭበርበር በመጠቀም በሩዋንዳ ፍትሐዊ ያልሆነ ነውጥ እንዲሰርጽ እያደረገች ነው። ይሄም ሩዋንዳንና ቀጠናውን ለማወክ ነው" ሲልም የሩዋንዳ መንግሥት ከሷል።
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ "ቤልጂየም፣ እናንተ ማን ስለሆናችሁ ነው? የኛ ኃላፊ ያደረጋችሁ ማን ነው? ሩዋንዳውያን በፈጣሪ እናምናለን።ፈጣሪ ቤልጄምን የሩዋንዳ መሪ አድርጓል?" ሲሉ ተናግረዋል።
የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሲን ፕሪቮት በማኅበራዊ ሚዲያ "ያልተገባ እርምጃ ነው። ከሩዋንዳ ጋር መግባባት ሲያቅተን ለንግግር ዝግጁ እንዳልሆኑ ያሳያል። በቤልጄም ያሉ የሩዋንዳ ዲፕሎማቶች ተቀባይነታቸው ተሽሯል" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በኤም23 እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታጣቂዎች ግጭት ምክንያት ወደ 7,000 ሰዎች ተገድለዋል።
ዩኒሴፍ እንዳለው ከ850,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ኤም23 ባለፉት ሁለት ወራት ቁልፍ ከተሞች የሆኑትን ጎማ እና ቡካቩ ተቆጣጥሯል።
ሩዋንዳ ለኤም23 የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም ዩኬ የተወሰነ ድጎማ አቋርጣለች።
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሩዋንዳ ጦሯን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንድታስወጣና ኤም23 ግጭቱን እንዲገታ ጠይቋል።