አሜሪካ በየመን በፈጸመችው አዲስ ጥቃት 53 ሰዎች መሞታቸውን የሁቲ አማፂያን ገለፁ

የየመን ሁቲ አማፂያን አሜሪካ በፈጸመችው አዲስ ጥቃት አምስት ሕጻናትን ጨምሮ 53 ሰዎች መሞታቸውን ገለፁ።

አማፂ ቡድኑ ሰኞ ማለዳ በአል ጃኡፍ እና ሁዳይዳህ አካባቢዎች የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የገለፀ ሲሆን፣ የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ በበኩሉ ጥቃት መፈጸሙ እንደቀጠለ መሆኑን ተናግሯል።

አሜሪካ የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት አካል ነው ያለችውን "ወሳኝ እና የማያዳግም" የአየር ጥቃት ከቅዳሜ ጀምራ እየፈጸመች መሆኑን ተናግራለች።

ዋሽንግተን ከሟቾቹ መካከል አንዳንድ ቁልፍ የሁቲ አማፂያን አባላት እንደሚገኙበት የገለፀች ቢሆንም እስካሁን ድረስ ቡድኑ ይህን አላረጋገጠም።

የሁቲ መሪ አብዱል ማሊክ አል-ሁቲ አሜሪካ በየመን ላይ የምታደርገውን ጥቃት እስከቀጠለች ድረስ ታጣቂዎቹ በቀይ ባህር ላይ በሚተላለፉ የአሜሪካ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ ተናግረዋል።

የሟቾች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከተገለፀው መጨመሩን የገለፁት የሁቲ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አኒስ አል-አስባሂ በኤክስ ገጻቸው ላይ "አምስት ሕፃናት እና ሁለት ሴቶች"ን ጨምሮ 53 ሰዎች መሞታቸውን እና 98 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

ስማቸውን አህመድ ሲሉ የጠሩ አንድ የሁለት ልጆች አባት ስለ ጥቃቱ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ለ10 ዓመታት በሰነዓ ስኖር የጥይት ድምጽ፣ የከባድ መሳርያ ድብደባ እየሰማሁ ነው። ፈጣሪ በሚያውቀው ከዚህ በፊት እንደዚህ ያለ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክል ዋልትስ ለኤቢሲ እንደተናገሩት የቅዳሜው ጥቃት "በርካታ የሁቲ መሪዎች ላይ ያነጣጠረ እና የገደለ" ነው ብለዋል።

ለፎክስ ኒውስ እንደተናገሩት "ከባድ በሆነ ኃይል ነው ጥቃቱን የፈጸምነው፤ እናም ኢራንን ከዚህ በላይ በቂ መሆኑን ማስገንዘብ እንፈልጋለን።"

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፔት ሄግዝት የሁቲ ጥቃቶች እስኪቆም ድረስ "የማያቋርጥ" የሚሳኤል ጥቃት ዘመቻ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ሄግዝ በፎክስ ቢዝነስ ላይ ቀርበው በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ "በጣም ግልፅ መሆን እፈልጋለሁ፤ ይህ ዘመቻ በባህሩ ላይ በነጻነት የመቅዘፍ እና የተቀመጠውን ክልከላ የመቀልበስ ነው" ብለዋል።

ሁቲዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችውን እገዳ እስክታነሳ ድረስ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ማነጣጠራቸውን እንደሚቀጥሉ እና ጦሩ ለጥቃቱ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

እስራኤልን እንደ ጠላት የሚቆጥረው እና በኢራን የሚደገፈው አማፂ ቡድኑ፣ ሰነዓን እና የየመንን ሰሜናዊ ምዕራብ ይቆጣጠራል።

አማፂ ቡድኑ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የአገሪቱ መንግሥት አይደለም።

ሁቲዎች በእስራኤል እና ሃማስ መካከል በሚደረገው ጦርነት ፍልስጤማውያንን በመደገፍ የቆሙ መሆናቸውን የሚገልፁ ሲሆን፣ ምንም እንኳ እውነት ባይሆንም ዒላማ የሚያደርጉት ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ጋር የተገናኙ መርከቦችን ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።

እአአ ከሕዳር 2023 ጀምሮ ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚሳኤል፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና በትንንሽ ጀልባዎች በመታገዝ በደርዘን የሚቆጠሩ የንግድ መርከቦችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት ፈጽመዋል።

በዚህም ጥቃታቸው ሁለት መርከቦች እንዲሰጥሙ ያደረጉ ሲሆን ሦስተኛ መርከብ በቁጥጥር ስር አውለው አራት ሠራተኞችን ገድለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት አገራቸው የፈጸመችውን ጥቃት ይፋ ባደረጉበት ወቅት "ዓላማችንን እስክናሳካ ድረስ ከፍተኛ ኃይልን እንጠቀማለን" ብለው ነበር።

"የሁቲ ዘራፊዎች በኢራን እየተደገፉ ሚሳኤልን ወደ አሜሪካ አውሮፕላኖች በማስወንጨፍ ወታደሮቻችንን እና አጋሮቻችንን ዒላማ አድርገዋል" ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

አክለውም የሁቲ "የባህር ላይ ውንብድና፣ጥቃት እና ሽብርተኝነት በቢሊዮኖች" የሚቆጠር ዋጋ አስከፍሏል፤ ሕይወትንም አደጋ ላይ ጥሏል ብለዋል።

ትራምፕ ለሁቲዎችን በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት ጥቃታቸውን እስካላቆሙ ድረስ "ከዚህ በፊት አይታችሁት የማታውቁት የጥቃት መዓት ይዘንባባችኋል" ሲሉ ጽፈዋል።

ሁቲዎች ግን የሚፈጸምባቸው ጥቃት ለፍልስጤማውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደማይቀንሰው በመግለጽ የማያወላውል ምላሽ ሰጥተዋል።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ የአሜሪካ መንግሥት "የኢራንን የውጭ ፖሊሲ ምን መምሰል እንዳለበት የመናገር ሥልጣንም፣ መብትም የለውም" ብለዋል።

"ለእስራኤል የዘር ማጥፋት እና ሽብርተኝነት የምታደርጉትን ድጋፍ አቁሙ" ሲሉ እሁድ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

"በየመን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ግድያ ይቁም!" ሲሉም አክለዋል።

የሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአሜሪካ አውሮፕላን ጫኝ መርከቦች እና በበርካታ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ለተፈፀሙት ሁለት ጥቃቶች ማስረጃ ሳይሰጡ፣ አሜሪካ ለምትፈጽመው ጥቃት ምላሽ እርምጃ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን አንድ የአሜሪካ ባለስልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለፁት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች እሁድ ዕለት 11 የሁቲ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተው መጣላቸውን እና አንዳቸውም ወደ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧ አለመቅረባቸውን ተናግረዋል።

ይኹን እንጂ አሜሪካ ሁቲዎች አድርሰነዋል ስላሉት ሁለተኛው ጥቃት እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እሁድ ዕለት ተፋላሚ ወገኖች "ከ ሁሉም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲያቆሙ እና ከየትኛውም ጥቃት እንዲታቀቡ" ጥሪ አቅርበዋል።