ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል እና ሊባኖስ ቀደም ሲል ምን ያህል ጊዜ ተዋግተዋል? በምን ምክንያት?
እስራኤል ሄዝቦላህ ላይ ለቀናት የዘለቀ የአየር ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ወደ ሊባኖስ ግዛት የእግረኛ ጦሯን አስገብታለች።
ነገር ግን እስራኤል አሁን የእግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ አስገብታ ወረራ ስትፈጽም የመጀመሪያዋ አይደለም።
ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገራት ኃይሎች መካከል በነበሩት ግጭቶች ያስከተሉት ውጤትም ጉራማይሌ ነው።
ታድያ የአሁኑ የእስራኤል ወረራ ከዚህ ቀደም ሠራዊቷ ከፈጸመው ተመሳሳይ የእግረኛ ጦር ዘመቻ በምን ይለያል?
1978: የመጀመሪያው ወረራ
እስራኤል በ1948 እንደ አገር ከተመሠረተች በኋላ ሊባኖስ ለፍልስጤማውያን ስደተኞች መዳረሻ ሆና ነበር። ከስደተኞቹ መካከል የፍልስጤም ታጣቂዎች የሆኑት የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) አባላት ይገኙበታል።
እነዚህ ታጣቂዎች ሊባኖስ ውስጥ ተቀምጠው እስራኤልን ማጥቃታቸው ነበር ሁለቱን አገራት ወደ ግጭት ያስገባቸው።
እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባኖስን የወረረችው በአውሮፓውያኑ 1978 ሲሆን፣ ይህም የሆነው የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅትን (ፒኤልኦ) ጥቃት ተከትሎ ነው።
ታጣቂ ቡድኑ በወቅቱ ወደ እስራኤል የባሕር ዳርቻ በመግባት አንድ አውቶብስን ማገታቸውን ተከትሎ ነበር።
በወቅቱ እስራኤል የባሕር ዳርቻው እልቂት ስትል በጠራቸው በዚህ እገታ 38 እስራኤላውያን ተገድለዋል።
በዚህም ምክንያት የእስራኤል ወታደሮች ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ገብተው ከሁለት ወራት በኋላ ወጥተዋል። ከዚያም በኋላ ቢሆን ከጎረቤት ሊባኖስ የሚመጣን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ወታደራዊ ሰፈር አቋቁመው እስከ አውሮፓውያኑ 2000 ድረስ ቆይተዋል።
በዚህ ወረራ 2000 ያህል የእስራኤል ወታደሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ በርካታ ንፁሃን ሊባኖሳውያንተገድለዋል። በእስራኤል ወገን ደግሞ 18 ወታደሮች ሞተዋል።
1982: ታላቁ ወረራ
የእስራኤል ወታደሮች የሊባኖስ የወደብ ከተማ የሆነችውን ሲዶንን ለገሊላ ሰላም ሲሉ በሰየሙት ዘመቻ ወቅት ይዘው ነበር።
ሊባኖስ ውስጥ የእስራኤል ወሳኝ የተባለው ወታደራዊ እርምጃ የተካሄደው በሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በአውሮፓውያኑ 1982 ነው።
በሺህ ዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል እግረኛ ወታደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንክ እና ከባድ የጦር መሳሪያ በታጠቁ መኪኖች ታግዘው እስራኤልን ሊባኖስ ውስጥ ተቀምጦ እያጠቃ የነበረውን ፒኤልኦን ለመውጋት በሚል ገቡ።
የእስራኤል ዓላማ በሊባኖስ ውስጥ መሽጎ ተደጋጋሚ ጥቃት የሚሰነዝረውን ፒኤልኦ ምሽጎች መደምሰስ ነበረ።
የእስራኤል ጦር በተለያዩ አቅጣጫ ወደ ሊባኖስ በመግባት በሳምንት ውስጥ የዋና ከተማዋ ቤይሩት ከተማ ዳርቻዎች ላይ ደረሰ።
በዚህ ማጥቃት ወቅት የእስራኤል ወታደሮች የፍልስጤም ስደተኞች ላይ በተፈጸመ የጅምላ ግድያ ተወንጅለዋል።
ከሦስት ወር በኋላም የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ውስጥ ቀጣይ ጥቃቶችን የሚከላከልበትን ቀጣና በመገንባት ጠቅልሎ ወጣ።
በዚህ ዘመቻ ወቅት 20 ሺህ ንጹሃን ሊባኖሳውያን ሕይወታቸውን ሲያጡ 654 ወታደሮች ደግሞ ተገድለዋል።
1996፡ አዲስ ጠላት አዲስ ወረራ
በአውሮፓውያኑ 1982 የእስራኤል ወረራ የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) አካባቢውን ለቅቆ ወጥቶ ዋና ቢሮውን በቱኒዚያ እንዲከፍት አስገድዶታል። ከዚህ በኋላ ግን ሌላኛው እስራኤል ጠላቴ ስትል የምትጠራው ሄዝቦላህ ተመሠረተ።
በ1996 (እአአ) ሚያዝያ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እስራኤል ሮኬት እየተኮሰ ያስቸገራትን ሄዝቦላህን ለመዋጋት ወደ ሊባኖስ ዘልቃ ገባች።
የእስራኤል የማጥቃት ዘመቻ እጅግ የተወሰነ የነበረ ሲሆን፣ በሁለት ሳምነት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ ችሏል።
በዚህም ጦርነት 250 የሊባኖስ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ፣ 13 የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ሞተዋል።
በእስራኤል በኩል ግን ምንም ወታደር እንዳልሞተባት ተዘግቧል።
ከዚህ በኋላ እስራኤል እና ሄዝቦላህ ጥርስ ተናክሰው የቆዩ ሲሆን ሮኬት ሲያስወንጭፍ፣ እስራኤል አየር ኃይልም ተደጋጋሚ የአየር ድብበዳ አካሄዷል።
2006፡ የ34 ቀኑ ጦርነት
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2006 የሄዝቦላህ ተዋጊዎች የእስራኤል ከተሞችን በሮኬት ደበደቡ። በተጨማሪም ሁለት የወታደራዊ መኪኖች ላይ ጥቃት ከፍተው 8 ወታደሮችን መግደላቸውን እንዲሁም ሁለት ማገታቸውን ተከትሎ እስራኤል የአጸፋ እርምጃ ከፈተች።
በወቅቱ እስራኤል ከፍተኛ የአየር ድብደባ ዘመቻ የከፈተች ሲሆን በሊባኖስ በተመረጡ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ከአየር እና ከባሕር ድብደባ አካሄዳለች።
ከዚያ በኋላም የእግረኛ ጦሯ የሊባኖስን ድንበር ተሻግሮ ገባ። ይህ ጦርነት 34 ቀናትን ፈጅቶ በተኩስ አቁም ስምምነት ነው ያበቃል። በሊባኖስ ወገን 1,191 ሰዎች ሲገደሉ፣ በእስራኤል ወገን 121 ወታደሮች እና 44 ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።
ወታደራዊ ተንታኞ ምን ይላሉ?
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አርታዒ ጄሬሚ ቦዌን እንደሚለው እስራኤል በሄዝቦላህ ላይ የወሰደችው እርምጃ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለጊዜውም ቢሆን ቀይሮታል።
“ባለፉት ሳምንታት እስራኤል ሄዝቦላህን አሽመድምዳዋለች፣ እንደ አሜሪካ እና እስራኤል ባለሥልጣናት ገለጻ ግማሽ ያህሉን የቡድኑን የጦር መሳሪያ አውድማለች። እንዲሁም ሊባኖስን ወርራለች።”
የእስራኤል ወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆነው ዮአቭ ስተርን ደግሞ እስራኤል በአውሮፓውያኑ በ2006 የተከተለችውን ስልት ልትደግም ትችላለች ብሏል።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1982 ካደረገችው በተቃራኒ በሊባኖስ የሚኖራትን ቆይታ ለአጭር ጊዜ ታደርገዋለች የሚል ትንታኔ አለው።
“የተፋጠነ እና የተጠናከረ ማጥቃት ከማድረግ ዝግ ያለ ይሆናል። የተጠና እና የተሰላ ወረራ ነው የሚሆነው፣ ይህም በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ ከተሞችን አንድ በአንድን መያዝን ይጨምራል” ይላል ስተርን።
አክሎም ሄዝቦላህ ለረዥም ጊዜ በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ ከተሞች ነበር መቀመጫውን ያደረገው። ያ ደግሞ እስራኤል እነዚህን ከተሞች እንዳትወር አልያም ቶሎ ለቅቃ አንድትወጣ አስገድዷት ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ከባለፈው ዓመት መስከረም ወር የሐማስ ጥቃት በኋላ በሊባኖስ ያለው ሁኔታ እና በእስራኤል ዘመቻ ላይ ለውጥ አለ።
እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ዘመቻ ሐማስን ማቀጨጭ ችላ ሊሆን ይችላል።
ምንም አንኳ ሄዝቦላህ ላይ ተደጋጋሚ ውጤታማ የአየር ጥቃት በማድረስ አመራሩን ማስወገድ እና መሠረተ ልማቱን ማውደም ቢቻልም በሊባኖስ ያለው ሁኔታ የበለጠ ፈታኝ ሊሆን ይችላል።
በአወስትራሊያ ናሽናል ዩኒቨርስቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት አሚን ሳይከል “ሄዝቦላህ ሐማስ አይደለም ነገር ገግ አሁንም በበቂ ሁኔታ የታጠቀ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ስፍራ ላይ የተቀመጠ ነው” ይላሉ።
“ለእስራኤል ወረራ ቡድኑ መጨረሻ የሌለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሊያውጅ ይችላል። ይህ ደግሞ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊም ሆነ ቁሳዊ ኪሳራ ይዞ ይመጣል” ሲሉ ያብራራሉ።
ጄሬሚ ቦዌን እስራኤል በጋዛ ዘመቻዋ አንዱን ዓላማዋን ገና አላሳካችም ይላል።
“ሄዝቦላህ በሁሉም ረገድ ከታየ በደቡባዊ ሊባኖስ ትልቅ ከመሬት በታች ዋሻዎች አሉት። እስራኤል ወደ ጋዛ ስትገባ አንደኛው ፍላጎቷ የነበረው የሐማስን የመሬት ውስጥ ዋሻዎችን ማፈራረስ ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረ ዓመት ሊሞላው ቢሆንም ይህንን ግን ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልቻለችም።”