የአውሮፓ ኅብረት ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ዩክሬንን ለመደገፍ ቃል ገባ

ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአውሮፓ መሪዎች ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የዩክሬንን "የገንዘብ ፍላጎቶች" ለመደገፍ ተስማሙ።

መሪዎቹ የዩክሬንን መከላከያ ለመደገፍ እንዳይንቀሳቀስ የተደረገ በቢሊዮን ዩሮ የሚገመት የሩሲያ ገንዘብ እንዲለቀቅላት ለማድረግ ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።

በቤልጂየም ባንክ ውስጥ የተቀመጠ 140 ቢሊዮን ዩሮ የሩሲያ ገንዘብን ለመጠቀም የቀረበው ሃሳብ ቤልጂየም ስጋቶቿን መግለጿን ተከትሎ እስከ መጪው ታሕሳስ ድረስ እንዲዘገይ ተደርጓል።

ይህ አከራካሪ እርምጃ በሩሲያ ላይ ሊጣሉ ከተያዙ ትልልቅ ማዕቀቦች መካከል አንዱ ነበር።

ረቡዕ ዕለት አሜሪካ የክሬምሊን የነዳጅ ገቢን ለመቀነስ ዒላማ ባደረገ መልኩ የነዳጅ አምራች ኩባንያዎቿ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

በብራስልስ የተካሄደው ስብሰባ አርብ ዕለት በለንደን ለማካሄድ ቀጠሮ ከተያዘለት ሌላ ጉባዔ ቀድም ብሎ የተካሄደ ነው።

በለንደንኑ ስብሰባ ላይ ሰር ኪር ስታርመር የአውሮፓ መሪዎች ለኪየቭ የሚሰጡትን ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዔሎች ቁጥር እንዲጨምሩ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩት፣ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን እና የኔዘርላንዱ ዲክ ሾፍ ጋር በመሆን "የፈቃደኞች ጥምረት" እየተባለ በሚጠራው ስብሰባ ላይ ይሳተፋሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ ሌሎች መሪዎች ስብሰባውን ኦንላየን እንደሚሳተፉ ማወቅ ተችሏል።

ባለፈው ሐሙስ የአውሮፓ ሚኒስትሮች በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ የሚገመት እንዳይንቀሳቀስ የተደረገ የሩሲያ ሀብት ለዩክሬን "የማካካሻ ብድር" በሚል እንዴት ሊሰጥ እንደሚችል በብራሰልስ ተወያይተዋል።

ብዙ የአውሮፓ ኅብረት መንግሥታት መሪዎቹ ዐዕቅዱን እንደሚደግፉ እና የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ መደበኛ የሕግ ምክረ ሃሳብ እንዲያዘጋጅ ይጠይቃሉ ብለው ጠብቀው ነበር።

ነገር ግን የተካሄዱ ረዣዥም ንግግሮች ፍሬ ሳያስገኙ በመቅረታቸው ዕቅዱ በአጭር ተቀጭቷል።

ከዚያ ይልቅ ኮሚሽኑን "በዩክሬን የፋይናንስ ፍላጎቶች ግምገማ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ድጋፍ አማራጮችን" ጠይቋል።

መግለጫው አክሎም "ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት እስክታቆምና በጦርነቷ ለደረሰባት ጉዳት ካሳ እስክትከፍል ድረስ የሩስያ ንብረቶቿ ሳይንቀሳቀሱ መቆየት ይኖርባቸዋል" ሲል በመግለጫው ላይ አስቀምጧል።

አሁን ዓላማው የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች በታህሳስ ወር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ነው።

የአውሮፓ ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ከስብሰባው በኋላ "ይህ በእርግጥ ቀላል ርዕስ አይደለም። በጣም የተወሳሰበ ነው። በተጨማሪም ግልጽ መሆን ያለባቸው ነጥቦች እንዳሉ ግልጽ ነበር።"

የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ ኅብረቱ "ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የዩክሬን የፋይናንስ ፍላጎቶች መሸፈኑን ለማረጋገጥ ቆርጦ ተነስቷል" ሲሉ አዎንታዊ አስተያየት ሰጥተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት "ሩሲያ ይህን በደንብ ልብ ልትለው ይገባል። ዩክሬን ራሷን ለመከላከል የሚያስፈልጋትን የገንዘብ አቅም ታገኛለች" ብለዋል።

በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ በብራስልስ የተገኙት ዜለንስኪ፣ የኅብረቱን ውሳኔ ኪየቭ በውጊያው ውስጥ የሩሲያን ገንዘብ እንድትጠቀም የሚያደረግ "የፖለቲካ ድጋፍ" ምልክት አድርገው በመውሰድ በደስታ ተቀብለውታል።

የሩስያ ገንዘብን በመጠቀም ዙሪያ በርካታ ውስብስብ የሕግ ጉዳዮች አሉ።

በተለይም ቤልጂየም እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉ ንብረቶችን ለመጠቀም ወደኋላ አፈግፍጋለች።

ምክንያቷ ደግሞ ሩሲያ ገንዘቡን ያስቀመጠው ዩሮክሊር የተሰኘ ተቋም ላይ ክስ ትመሰርታለች የሚል ነው።

የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ደ ዌቨር ዕቅዱን ከመደገፋቸው በፊት አገራቸው ተጨባጭ እና ጠንካራ ዋስትናዎች ያስፈልጋታል ሲሉ ዕቅዱ "ያልተኬደበት ቀጠና" መሆኑን ጠቁመዋል።

የቤልጂየም መንግሥት ዩሮክሊርን ለሙግት እንደሚያጋልጥ እና በመጨረሻም ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል በመጥቀስ ተከራክሯል።

"ይህ (ዐዕቅድ) ሕጋዊ ሊሆን ይችላል? ያ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ... ግልጽ የሆኑ መልሶች የሉም "ሲሉ ዴ ዌቨር ተናግረዋል።

"በማንኛውም ሁኔታ በክስ ውስጥ እንዘፈቃለን። ያ እርግጥ ይመስላል።"

ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ ነቅፋለች።

"ከብራሰልስ የሚደረጉ ማንኛቸውም የመውረስ ውጥኖች አሳዛኝ ምላሽ ማስገኘታቸው የማይቀር ነው" ሲሉ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ተናግረዋል።