ዩክሬን ከዩኬ ያገኘችውን ሚሳዔል ተጠቅማ የሩሲያን የኬሚካል ፋብሪካ አጠቃች

ዩኬ ሠራሹ ስቶርም ሻዶ ሚሳዔል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዩክሬን በዩናይትድ ኪንግደም በተሰራው ስቶርም ሻዶ ሚሳኤሎች የሩስያን የኬሚካል ፋብሪካ መምታቷን የአገሪቱ ጦር ማክሰኞ ዕለት አስታወቀ።

የሩሲያ የአየር መከላከያ ስርዓትን አልፎ የተፈጸመውን ጥቃት "ስኬታማ እርምጃ" ሲሉ የገለፁት የዩክሬን የጦር ኃይሎች በአጠቃላይ "ግዙፉ ሚሳኤል እና የአየር ድብደባ" ያደረሰውን ጎዳት እየገመገሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ክሬምሊን ምዕራባውያን ለዩክሬን የረዥም ርቀት ጥቃቶችን መፈጸም የምትችልበት የጦር መሳሪያ እንዳይሰጡ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።

ኪየቭ ግን ሞስኮ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን የሩሲያ ተቋማትን ዒላማ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብላለች።

የዩክሬን ጦር ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጹ ላይ ባሰፈረው ልጥፍ ላይ "የብራያንስክ ኬሚካል ፋብሪካ የወራሪው ግዛት ወታደራዊ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ቁልፍ ተቋም ነው" ብሏል።

አክሎም ፋብሪካው "የዩክሬንን ግዛት ለመምታት ባሩድ፣ፈንጂ እና የሮኬት ነዳጅ አካላትን እና ሚሳኤሎችን ያመርታል" ብሏል።

የሞስኮ ባለስልጣናት ስለ ጥቃቱ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።

ጥቃቱ የተፈጸመው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እና ሌሎች የአውሮፓ መሪዎች የሩሲያ መሪ ቭላድሚር ፑቲን "ሰላም ለመፍጠር ዝግጁ እስኪሆኑ" ድረስ "በሩሲያ ኢኮኖሚ እና በመከላከያ ኢንደስትሪው ላይ የሚያሳርፉትን ጫና እንደሚያሳድጉ" ቃል በገቡበት ቀን ነው።

በዩክሬን፣ በጀርመን፣ በፈረንሣይ፣ በጣሊያን፣ በፖላንድ፣ በዴንማርክ፣ በፊንላንድ፣ በአውሮፓ ኅብረት እና በኖርዌይ መሪዎች የተፈረመ የጋራ መግለጫ "ዩክሬን ከማንኛውም የተኩስ አቁም በፊት፣ ወቅት እና በኋላ በጣም ጠንካራ ቦታ ላይ መሆን አለባት" ይላል።

የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማዋ ላይ ረቡዕ ማለዳ ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መሰንዘሯን ተናግረዋል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል የዓይን እማኞችን ጠቅሶ በፋብሪካው አካባቢ የአየር መከላከያ የሚመስል ድምጽ መስማታቸውን ዘግቧል።

የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች የደረሱት ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዋይት ሐውስ ከተገናኙ እና የዩኤስ ፕሬዚዳንት የቶማሆክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ለኪየቭ ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑ ከተናገሩ በኋላ ነው።

ትራምፕ መጀመሪያ ላይ ከፑቲን ጋር በዩክሬን ስላለው ጦርነት ለመነጋገር በሚቀጥሉት ሳምንታት በቡዳፔስት ለመገናኘት ተስማምተዋል።

ነገር ግን ይህ ዕቅድ ትራምፕ "የሚባክን ስብሰባ" እንዲሆን አልፈልግም ማለታቸውን ተከትሎ ማክሰኞ ዕለት ለጊዜው እንዲዘገይ ተደርጓል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዋይት ሐውስ ባደረጉት ንግግር ሞስኮ ውግያ እያካሄደች ባለችበት ግንባር ላይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኗ አጣብቂኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለፈው ወር ትራምፕ ኪየቭ "ሁሉንም መሬቷን ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስ ትችላለች" በማለት ጦርነቱን በማስቆም ላይ የአቋም ለውጥ ያደረጉ መስለው ነበር።

ሩሲያ እአአ የካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ፈጽማለች።

በአሁኑ ጊዜ በ2014 የገነጠለቻትን ክሬሚያን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬይን ግዛት ትቆጣጠራለች።