ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕጻናትን ለሥልጣን እና ለሀብት በሚል እየሰረቁ የሚገድሉት የሴራ ሊዮን ጠንቋዮች
በሴራ ሊዮን ከጥንቆላ ጋር በተያያዘ በሚፈጸም ግድያ የተነሳ በርካታ ቤተሰቦች ተደናግጠዋል። ቢቢሲ አፍሪካ አይ ከጀርባው ያለውን የሰዎች አካል ሽያጭን በሚመለከት ምርመራ አድርጓል።
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ የተወሰኑ አንባቢዎችን ሊረብሽ የሚችል ዝርዝሮችን ይዟል
ሳሊ ኮሎኮህ የ11 ዓመት ልጇ ከአራት ዓመት በፊት "ብላክ ማጂክ" በተባለ ጥንቆላ የተነሳ ተገድሎ ማንም የተጠረጠረ እና ለፍርድ የቀረበ ባለመኖሩ ትንገበገባለች።
ለቢቢሲ አፍሪካ አይ "ሕመም ውስጥ ነኝ፤ ልጄን ገደሉት፤ እና ሁሉም ዝም አለ" ስትል የልጇ ፓፓዮ ወሳኝ የአካል ክፍሎቹ፣ ዐይኖቹን እና አንድ እጁን ጨምሮ ተወስደው እንዴት እንዳገኘችው ገልፃለች።
ዓሣ ለመሸጥ ወደ ገበያ በሄደበት አልተመለሰም።
ቤተሰቡ ለሁለት ቀን ያህል ፈለገ፤ በመጨረሻ ግን ያገኘው ተቆራርጦ በጉድጓድ ውስጥ የተጣለ አስከሬኑን ብቻ ነው።
"ልጆቻችንን ሁሌን ጥንቁቅ እንዲሆኑ ነው የምንነግራቸው። ገበያ እቃ ለመሸጥ የሚሄዱ ከሆነ ወደ ጫፍ አትሂዱ፤ ከማታውቁት ሰው ምንም ነገር አትቀበሉ፣ ይህ ነገር በተደጋጋሚ ነው በዚህ አገር የሚከሰተው" ትላለች ካሎኮህ።
በማዕከላዊ ሴራ ሊዮን በተደጋጋሚ አገሬው 'ጁጁ' ሲል ከሚጠራው ጥንቆላ ጋር የተያያዙ ወሬዎች ይሰማሉ።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን በቂ ምርመራ ሲያደርጉ አይታይም።
በፓፒዮ ጉዳይ ፖሊስ "ለጥንቆላ ተብሎ የተገደለ" መሆኑን እንኳን ማረጋገጥ አልፈለገም።
አንድ ሰው የሚገደለው ጁጁ እየተባለ የሚጠራውን የጥንቆላ ሥርዓት የሚያካሄዱ ሰዎች የአካል ክፍሎቹን ወስደው እንዲጠቀሙበት በሚል ነው።
በእንዲህ ዓይነት የጥንቆላ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሀብትን እና ሥልጣንን ለደንበኞቻቸው ቃል ይገባሉ።
ደንበኞቻቸውም እነዚህ አጭበርባሪ ጠንቋዮች የሚሉት ሁሉ እውነት አንደሆነ በማመን ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይከፍላሉ።
8.9 ሚሊዮን ሕዝብ ባለት ሴራ ሊዮን አንድ የአስከሬን ምርመራ ባለሙያ ብቻ ያላት ሲሆን፣ ባለሥልጣናት ከፍተኛ የሆነ የባለሙያ እና የገንዘብ እጥረት ስላለባቸው እንዲህ ዓይነት ወንጀሎችን ለመከታተል እና ለመመርመር ይቸገራሉ።
በሴራ ሊዮን በጥንቆላ ማመን እጅጉን ከማኅበረሰቡ ጋር የተቆራኘ ነው።
በርካታ የፖሊስ ባልደረቦች ራሳቸው በእንዲህ ዓይነት እምነት የተያዙ በመሆናቸው በጁጁ ጥንቆላ የተጠረጠሩ ሰዎችን ለመመርመር ፈቃደኛ አይሆኑም።
ስለዚህ ግድያዎቹን ማን እንደፈጸማቸው፣ ለምን እንደተፈጸሙ ሳይታወቁ ይቀራሉ።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ቡድን የጁጁ ጥንቆላን አካሂድ ነበር፣ ሥርዓቱን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ የአካል ክፍሎችን አቀርብ ነበር ያሉ ሁለት ሰዎችን አግኝቷል።
ሁለቱም ግዙፍ የሆነ መረብ አካል መሆናቸውን ሲገልጹ፣ አንዱ ደግሞ በምዕራብ አፍሪካ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ደንበኞች ማፍራቱን ተናግሯል።
ቢቢሲ ይህንን የግለሰቡን ንግግር ማረጋገጥ አልቻለም።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ አንድ አባል ማንነቱን ደብቆ፣ ስሙን ኦስማን በሚል ቀይሮ፣ ፖለቲከኛ እንደሆነ እና ሰው መስዋዕት ተደርጎለት ሥልጣን ማግኘት እንደሚፈልግ ገልጾ ቀረበ።
ቢቢሲ ጥንቆላውን የሚያካሄደውን ሰው ለማግኘት በሴራ ሊዮን ሰሜናዊ ግዛት፣ ወደ ጊኒ ድንበር ተጠግቶ የሚገኘው ካምቢያ ወረዳ ውስጥ ባለ ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ወደ ሚገኝ መኖሪያው ሄዷል።
ራሱን ካኑ በማለት የሚጠራው ይህ ጠንቋይ ፊቱን በሙሉ የሸፈነ ለሥርዓቱ የሚለበስ ጭምብል አጥልቋል።
ጭምብሉ ማንነቱን ከመደበቁ ባሻገር አለኝ ለሚላቸው ፖለቲካዊ ግንኙነቶች እንደሽፋን ሆኖ አገልግሎታል።
"እኔ በጊኒ፣ በሴኔጋል እና በናይጄሪያ ውስጥ ከአንዳንድ ትላልቅ ፖለቲከኞች ጋር እሠራ ነበር። ቡድን አለን። አንዳንድ ጊዜ በምርጫ ወቅት፣ ሌሊት ይህ ቦታ በሰዎች የተሞላ ነው" ሲል ተናግሯል።
የምርጫ ወቅት ወላጆች በጣም አደገኛ የሚሉት ጊዜ ነው።
እገታ እና ጠለፋ የሚበረክትበት ጊዜ በመሆኑ ልጆቻቸውን እንዲጠነቀቁ የሚነግሩበት እና የሚመክሩበት ወቅት ነው።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ስፍራው ቢቢሲ በተጓዘበት ወቅት ካኑ የበለጠ በራስ መተማመን ስለተሰማው ለኦስማን የሥራው አካል የሆነውን የሰው ራስ ቅል አውጥቶ አሳየው።
"ይህንን አየህ? ይህ ለሆነ ሰው የተዘጋጀ ነው። ለእርሱ ነው ያደረቅኩለት። የሴት ልጅ የራስ ቅል ነው። ዛሬ ወይንም ነገ መጥቶ ይወስዳል ብዬ አየጠበቅኩ ነው።"
በተጨማሪም ከተቀመጠበት ጀርባ ያለውን ጉድጓድ አያሳየ "የሰውን አካል የምንሰቅለው በዚህ ስፍራ ነው፤ እዚህ እናርዳለን፣ ደሙም ወደዚያ ይወርዳል…ትልልቅ አለቆች እንኳን ሥልጣን ሲፈልጉ ወደዚህ ይመጣሉ፤ የሚፈልጉትን እሰጣቸዋለሁ" አለ።
ኦስማን የሴት እጅ እና እግር ለአምልኮ ሥርዓቱ እንዲውል እንደሚፈልግ ሲገልጽ ካኑ ወደ ማስላት ገባ።
"የአንዲት ሴት ዋጋ 70 ሚሊዮን ሊዮን [የሴራ ሊዮን ገንዘብ ወይም 3,000 ዶላር] ነው።"
ቢቢሲ ማንንም ሰው አደጋ ላይ ላለመጣል በመፈለግ በድጋሚ አላገኘውም።
ካኑ አጭበርባሪ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ምርመራ ለማድረግ የሚያግዙ ማስረጃዎችን ለአካባቢው ፖሊስ አስረክቧል።
እንደነዚህ ዓይነት የጥንቆላ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወንዶች አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን የባሕል መድኃኒት አዋቂ በማለት ይጠራሉ።
ይህ ስያሜ ብዙ ጊዜ በአካባቢው የሚገኙ ቅጠላ ቅጠሎችን እና ስራ ስሮችን በመጠቀም የተለመዱ በሽታዎችን የሚፈውሱ ሰዎች የሚገለገሉበት ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ1990ዎቹ በአሰቃቂ የእርስ በርስ ጦርነት የተጎዳችው እና የኢቦላ ወረርሽኝ ማዕከል የነበረችው ሴራ ሊዮን በአውሮፓውያኑ 2022 አንድ ሺህ የሚጠጉ ዶክተሮች እንዳሉ ሲመዘገብ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች ቁጥር ግን 45 ሺህ ያህል ነበር።
በምዕራብ አፍሪካ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች በእነዚህ የባሕል መድኃኒት ቀማቂዎች ላይ የተደገፉ ናቸው።
በአእምሮ ጤና ሕመም የሚሰቃዩ እና ሌሎች ታካሚዎቻቸውን ለማከም የሚጠቀሙበት መድኃኒት እና ቁሳቁስ በምሥጢራዊነት እና የመንፈሳዊነት ባህሪ የተላበሰ ነው።
የሴራ ሊዮን የባህል ሕክምና ባለሙያዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኩ ታራዋሊ እንደ ካኑ ያሉ "አሳሳች" ጠንቋዮች ለባሕላዊ ሐኪሞች መጥፎ ስም እየሰጡ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
"የራሳችንን ገጽታ ለማጽዳት በጣም ጠንክረን እየሠራን ነው። ተራው ሰው አይረዳውም፤ ስለዚህ እኛን [ሁላችንንም] እንደ መጥፎ የባህል መድኃኒት አዋቂ አድርገው ይመድቡናል። አንድ የበሰበሰ ዓሳ በሙሉ ዓሳውን በሙሉ ያበላሸዋል...እኛ ፈዋሾች ነን እንጂ ገዳይ አይደለንም" ሲሉ ለቢቢሲ አፍሪካ አይ ተናግረዋል።
ታራዋሊ ከመንግሥት እና ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለታካሚዎች የባሕላዊ ሕክምና ክሊኒክ ለመክፈት እየሞከሩ ነው።
ለዚህ ሥርዓት ከሚፈጸመው ግድያ ጀርባ ያሉት የሥልጣን እና የገንዘብ ጥማት ያላቸው ሰዎች ናቸው በማለት ያምናሉ።
"አንድ ሰው መሪ መሆን ሲፈልግ… የአካል ክፍሎችን ከሰዎች ላይ ይወስዳሉ። ያንን ለመስዋዕትነት ያቀርቡታል። ሰዎችን አቃጥለው አመዱን ለሥልጣን ይጠቀሙበታል። ዘይቱን ለሥልጣን ይገለገሉበታል።"
በርካታ ሴራ ሊዮናውያን ራሳቸውን ሙስሊም ወይም ክርስቲያን ብለው በሚለዩባት አገር ለጥንቆላ ተብለው የተፈጸሙ ግድያዎች ቁጥር በውል አይታወቅም።
በዩናይትድ ኪንግደም የአበርስትዋይት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ኢማኑኤል ሳርፖንግ ኦውሱ "በአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም በሚል የሚፈጸሙ ግድያዎች እንደ የተለየ ወይም በነፍስ ግድያ ስር ተካትተው በይፋ አይመዘገቡም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አንዳንዶች አደጋ፣ የዱር እንስሳት ጥቃት፣ ራስን ማጥፋት፣ የተፈጥሮ ሞት በሚል በተሳሳተ መንገድ ይከፋፈላሉ፤ ወይም ይመዘገባሉ… አብዛኞቹ አጥፊዎች ምናልባትም 90 በመቶ ያህሉ አልተያዙም።"
ቢቢሲ ከዋና ከተማዋ ፍሪታውን ወጣ ብሎ በሚገኘው ዋተርሉ በተባለው በአደንዛዥ ዕፅ እና በሌሎች ወንጀሎች የታወቀ አካባቢ ሌላ ተጠርጣሪ የአካል ክፍሎችን አቅራቢ አግኝቷል።
ራሱን ኢዳራ እያለ የሚጠራው ሰው ራሱን ኡስማን ብሎ ለሚጠራው እና በስውር ካሜራ ለያዘው የቢቢሲ ባልደረባ "ብቻዬን አይደለሁም እስከ 250 የሚደርሱ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች አሉኝ" ሲል ተናግሯል።
ኢዳራ "እኛ የማንሠራባቸው የሰው አካል ክፍሎች የሉም፤ አንድ ጊዜ የሆነ የሰውነት ክፍል ከጠራን ያመጣሉ፤ ሥራውን ተከፋፍለን ነው የምንሠራው" ሲል ተናግሯል።
ቀጠለና አንዳንድ ግብረ አበሮቹ ሰዎችን በመያዝ ረገድ እንዴት ጎበዝ እንደሆኑ ገለጸ።
ኦስማን ለሁለተኛ ጊዜ ባገኘው ወቅት የሚያግቱትን ሰው ፍለጋ በየምሽቱ መውጣት ለመጀመር እንደተዘጋጁ ከሚናገሩ ሰዎች የአንዳቸውን የድምጽ መልዕክት አሰማው።
ኦስማን ከዚህ በላይ እንዳይቀጥል ቢነግረውም በኋላ ግን ደውሎለት ቡድኑ የሚያጠምደውን ሰው መለየቱን ነግሮታል።
ቢቢሲ የፖሊስ ኮሚሽነር ኢብራሂም ሳማን በጉዳዩ ላይ አነጋግሯል።
በተባለው አካባቢ በመሄድ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊሶችን እንደሚያሰማሩ ቢናገሩም፣ የፖሊስ ባልደረቦቹ እንደዚህ ባሉ ሥራዎች ላይ የሚያግዟቸውን ታራዋሊን ሳይገኙ ይህን ማድረግ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
"አንድ አደገኛ ጠንቋይ የሰዎችን አካል ተጠቅሞ እንደሚሠራ መረጃ ስናገኝ ከባህላዊ ሕክምና ባለሙያዎች ጋር አብረን እንሠራለን" ሲሉ ረዳት ሳጅን አሊዩ ጃሎ ተናግረዋል።
በመቀጠልም አንዳንድ መኮንኖች አጭበርባሪ የባሕል መድኃኒት አዋቂዎችን ስለመታገል ያላቸውን አጉል እምነት ሲገልጹ "እኔ ሄጄ በራሴ ላይ ነገር አልቀሰቅስም። ከእውቀቴ በላይ የሆነ የራሳቸው ሥልጣን እንዳላቸው አውቃለሁ ይላሉ" ብለዋል።
ኢዳራ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ጣሪያው ውስጥ የደበቀው ቢላ ተይዟል።
ታራዋሊ የሰው አጥንት፣ ፀጉር እና ከመቃብር ላይ የተወሰደ የሚመስል የቆሻሻ ክምር እንዳለ በመግለጽ ለማስረጃነት መፈለግ ጀመሩ።
ኢዳራ እና ሌሎች ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለፖሊስ ይህ በቂ ነበር።
በሰኔ ወር ጥንቆላ በመፈጸም እና ለጥንቆላ ሥርዓት ግድያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያዎችን ይዘው በመገኘት ተከሰሱ።
ለቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ብለው በመከራከራቸው የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ለተጨማሪ ምርመራ እየተጠባበቁ ነው።
በካምቢያ ስለሚገኘው ካኑ ከፖሊስ ምንም የተገኘ ተጨማሪ መረጃ የለም።
ቢቢሲ በሚቀርብበት ክስ ላይ ለማነጋገር እና ተጨማሪ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ ወደ ስልኩ ደጋግሞ ቢደውልም ሊያገኘው አልቻለም።
በሴራ ሊዮን ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ ክሶች ሳይቀሩ ተዳፍነው የሚቀሩበት አጋጣሚዎች አሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት በፍሪታውን አንድ የዩንቨርስቲ መምህር ከጠፋ በኋላ አስከሬኑ ፖሊስ ዋተርሉ በሚገኘው የባህል መድኃኒት አዋቂ ቤት ነው ሲል በገለጸው ስፍራ ተቀበሮ ተገኘ።
ጉዳዩ በነሐሴ 2023 ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲታይ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ክትትል እንዳልተደረገ እና በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩትም በዋስ መለቀቃቸውን ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ይህንን ዘገባ እየሠራ በነበረበት ወቅት በዚህ ዘገባ ላይ ተሳታፊ የነበረ የቢቢሲ ባልደረባ ወንድም ልጅ የ28 ዓመቷ ፋትማታ ኮንቴህ በማኬኒ ተገድላለች።
ቤተሰቡ ፍትህ ለማግኘት ተመሳሳይ ፈተና ገጥሟቸዋል።
የፀጉር ሥራ ባለሙያ እና የሁለት ልጆች እናት የነበረችው ይህች ግለሰብ በልደት ቀኗ ማግስት አስከሬኗ መንገድ ዳር ወድቆ ተገኝቷል።
ነዋሪዎች ለቢቢሲ በቅርብ ሳምንት ውስጥ ሁለት አስከሬኖች በተመሳሳይ ስፍራ ተጥለው መገኘታቸውን ይናገራሉ።
የሟች በርካታ የፊት ጥርሶቿ ጠፍተዋል፤ ይህም ሕብረተሰቡ የአምልኮ ሥርዓት ለመፈፀም የተደረገ ግድያ እንደሆነ እንዲያምን አድርጎታል።
አንድ ሐዘንተኛ ቤተሰብ "ምንም ጉዳት የማታደርስ ሴት ነበረች፤ በጣም ሰላማዊ እና ታታሪ ነበረች" ስትል ገልጻታለች።
የፋትማታ ግድያ ትክክለኛ መንስዔ ምን እንደሆነ ላናውቀው እንችላለን። ቤተሰቧ አስከሬኗ ምርመራ እንዲደረግለት ወደ ፍሪታውን ልኳል።
ይህን ግን የአገሪቱ ፖሊስ ማድረግ አይችልም። ነገር ግን የአስከሬን ምርመራው ውጤት ጠንካራ ማስረጃ ስላላስገኘ እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው የለም።
እንደ ፓፓዮ እናት ሁኔታ ፖሊስ ከሚፈጸሙ ግድያዎች ጀርባ ያሉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ባለመቻሉ ማኬኒ በሚባለው አካባቢ የሚገኙ ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ችላ የመባል ስሜት፣ ፍርሃት እና ሽብር ነግሷል።