ብዙዎችን የሚያሳቅቀው መጥፎ የአፍ ጠረንን የሚፈጥረው ምንድን ነው?

በግሪክ አፈ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስፈሪ ባለ ብዙ ጭንቅላቱ አውሬ ሃይደራ ከባድ ከሆነወ መጥፎ የአፍ ጠረኑ የተነሳ አፉ የሸተተው ሰው ሁሉ ሕይወቱ ያልፋል ይባላል።

ምንም እንኳ ይህ የግሪክ አፈ ታሪክ የተጋነነ ቢመስልም አንዳንዶቻችን በተለይ ከእንቅልፍ ስንነሳ ባለን መጥፎ የአፍ ጠረን ወይም አንዳንድ ምግቦች በሚያመጡብን መጥፎ ጠረን ሳንረበሽ አንቀርም።

መጥፎ የአፍ ጠረን ደካማ ከሆነ የአፍ ንጽህና አጠባበቅ በተጨማሪ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

መጥፎ የአፍ ጠረን በሆድ እና በደም ዝውውር ሥርዓት ውስጥ እንዲሁም የሳይነስ ችግር መኖሩን ሊጠቁም ይችላል።

በሠለጠኑ አገራት የትንፋሽ ናሙና በመውሰድ የችግሩ ምክንያት እስከመለየት ተደርሷል።

የአፍ ጠረንን ከሚያበላሹ የጤና እክሎች መካከል አንዱ ከስኳር በሽታ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ነው። የስኳር ህመም የሚከሰተው በሰውነት ውስጥ ያለ ስኳር (ግሉኮስ) ኃይል ለሚሰጠው የሰውነት ህዋስን ማግኘት ሳይችል ሲቀር እና በደም ዝውውር ውስጥ ሲበዛ ነው።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ በቂ ኢንሱሊን ሳይኖር ሲቀር ወይም ኢንፌክሽን ሲያጋጥም ሰውነት ኃይል ለማግኘት ስብን ወደ ኬቶንስ ይቀይራል።

ይህ ኬቶንስ ታዲያ ጠንከር ያለ ጠረን አለው። ኬቶንስ በደም ውስጥ ሲከማች በቀላሉ ሽታው በአፍ ጠረን በኩል ይወጣል። ይህም መጥፎ የአፍ ጠረን እንዲኖር ያደርጋል።

ታዲያ የስኳር ህመም ብቻ አይደለም በሰውነት ውስጥ የኬቶን ምርት እንዲጨመር የሚያደርጋው።

አንዳንዶች ሰውነት ለመቀነስ በሚደርጉት ጥረት በሰውነታቸው የኬቶን መጠን ይጨምራል። ሰዎች ለረዥም ሰዓታት ያለምግብ ሲቆዩ ሰውነት በውስጡ ያለውን ስብ ወደ ኃይል ለመቀየር ኬቶንስ ያመርታል።

ከዚህ በተጨማሪ 5፡2 የሚባለው በቀን ሁለት ጊዜ የመመገብ ጾም እንዲሁ በተመሳሳይ መርህ ላይ የተመሠረተ ነው።

ሰዎች የሚወስዱትን የካሎሪ መጠን በመገደብ በቀን ሁለት ጊዜ ብቻ መመገባቸው፤ ሰውነት ኬቶንስ እንዲያመርት ይገደዳል።

እንደዚህ ዓይነት የጾም ሰልቶች ሰዎች ክብደታቸውን እንዲቀንሱ ቢያስችላቸውም ጾሙ የጎንዮሽ ችግር ማስከተሉ አይቀርም።

ከአንዱ በፍጥነት የሚታየው የጎንዮሽ ጉዳት መጥፎ የአፍ ጠረን ነው።

ባክቴሪያ እና የአፍ ጠረን

የአፍ ጠረንን ከሚያበላሹ ሌሎች ምክንያቶች መካከል ሌላኛው ሽታ ያላቸው ባክቴሪያዎች ከመጠን በላይ ማደግ ነው።

በአፋችን ውስጥ ለማጽዳት አዳጋች የሆኑ እና ባክቴሪያዎች ሊያድጉባቸው እና ሊኖሩባቸው የሚችሉ በርካታ ቦታዎች አሉ። በተለይ ደግሞ የአፋንችን የኋለኛ ክፍል እና ጉሮሮ አካባቢ ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው።

ጉሮሮ የምግብ፣ የፈሳሸ እና የአየር መተላለፊያ ቦታ ነው። አንዳንድ ሰዎች በጉሮሮ ውስጥ እባጭ ነገር ይፈጠርባቸዋል።

በዚህ ምክንያት ጉሮሮ አካባቢ ምግብ እና ፍሳሽ ነገር በመጠራቀም መጥፎ ጠረን እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

ባክቴሪያ እንዲሁ አፍ ውስጥ የሰውነት መቆጣት ሊያስከትል ይችላል። የቶንሲል ህመም እና ከጥርስ ህመም ጋር ተያይዞ ፈሳሽ ነገር የሚቋጥሩ እባጮች መጥፎ የአፍ ጠረን ይፈጥራሉ።

የአፍ ጠረን ምርመራ

ሐኪሞች መጥፎ የአፍ ጠረን ናሙናን በመውሰድ የችግሩ ምንጭ ምን እንደሆነ በመለየት መፍትሄ ሊሰጡ ይችላሉ።

ለምሳሌ ሄሊኮባክተር ፓይሎሪ የተባለው ባክቴሪያ የሆድ መቆጣትን ያስከትላል። ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው ዩሬአ የተባለ ንጥረ ከመስጠጣቸው በፊት እና ከሰጡ በኋላ የአፍ ጠረን ናሙናን በመውሰድ ምርመራ ያደርጋሉ።

በምርመራቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይድ የሚያገኙ ከሆነ ሄሊኮባክተር የተባለው ባክቴሪያ መኖሩን ያረጋግጣል።

የሆድ መነፋትን እና የሆድ ቁርጠትን የሚያመጡ የባክቴሪያዎች ዕድገት እንዲሁ የአፍ ጠረንን ሊያበላሹ ይችላሉ።

በተመሳሳይ ሐኪሞች የሆድ መነፋትን የሚያስከትለው ባክቴሪያ በሆድ ውስጥ እንደሚገኝ በምርመራ ካረጋገጡ የአፍ ጠረን መለወጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሊረዱት ይችላሉ።

አንዳንዴ ሰዎች የራሳቸው የአፍ ጠረን ሽታ ምን እንደሆነ ስለማይለዩ እርስዎ የጤና ችግር እንደሌለብዎ እርግጠኛ ከሆኑ እና የአፈ ጠረንዎ የሚያሳስብዎ ከሆነ የራስዎትን የአፈ ጠረን መፈተሽ ይችላሉ።

የቆየ ልማድ የሆነው የመዳፍ መገጣጠሚያን በምላስ መንካት ነው። ከዚያ እርጥበቱ እስኪደርቅ ጠብቀው ያሽትቱት።

የአፈ ጠርንዎ መጥፎ መሆኑን ከተረዱ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?

ሁለት ቀላል የሚባሉ እርምጃዎች ለመጥፎ የአፈ ጠረን ሁነኛ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ። የመጀመሪያው የአፍ ድርቀትን ማስወገድ ነው። እንደሚታወቀው የአፈ መድረቅ የመጥፎ የአፍ ጠረን አንዱ መንስኤ ነው። ስለዚህ ውሃ እና ፈሳሽ ነገሮችን አብዝቶ በመውሰድ የአፈ እርጥበትን ማስጠበቅ አንዱ አማራጭ ነው።

ሁለተኛው የአፈ ንጽህናን መጠበቅ ነው። ይህ ታዲያ ጠርስን መቦረሽን ብቻ ማለት አይደለም። የአፈ ንጽህና መጠበቅ ማለት ምላስን ማጽዳት እንዲሁም በጥርሶች መካከል ባክቴሪያ እንዳይፈጠር ማጽዳትን እንዲሁም የጥርስ ሐኪም ጋር ለምርመራ መሄድን ያካትታል።

ማጨስ እንዲሁ ለመጥፎ የአፈ ጠረን ምክንያት ስለሆነ ማጨስ ለማቆም የአፈ ጠረን ለመጠበቅ ሌላ ምክንያት ይሆናል።