ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፍልስጤማውያን እና የአረብ ሀገራት የትራምፕን ጋዛን የመቆጣጠር ዕቅድ ተቃወሙ
የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡን አሜሪካ ጋዛን እንድትቆጣጠር እና በውስጡ የሚኖሩትን 2.1 ሚሊዮን ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ ቦታ የማስፈር ዕቅድን በፅኑ እንደሚቃወሙት ተናገሩ።
የፍልስጤም ሕዝብ መብት እንዲጣስ እንደማይፈቅዱ የገለጹት ማህሙድ አባስ፤ ጋዛ "የሀገረ ፍልስጤም ዋነኛ አካል" እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል። በጋዛ የሚገኙ ነዋሪዎችን በግዳጅ ማፈናቀል ከባድ ዓለም አቀፋዊ ሕግ ጥሰት እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
ለ15 ወራት ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረው ሐማስ በበኩሉ፤ ይህንን የትራምፕ ዕቅድ በቀጣናው "እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ" ነው ሲል ገልጾታል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋዛን አሜሪካ እድትቆጣጠር የማድረግ ሀሳብ እንደ ዮርዳኖስ እና ግብፅ ካሉት የቀጣናው ሀገራትም ተቃውሞ ገጥሞታል። ትራምፕ፤ እነዚህ ሀገራት አብዛኞቹን የተፈናቃሉ የጋዛ ነዋሪዎችን እንዲቀበሉ ይፈልጋሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ይህንን ሀሳብ ተቃውመዋል። ጋዛ የወደፊቷ ሀገረ ፍልስጤም ዋነኛ አካል እንደሆነ የገለጹት ጉቴሬዝ፤ "የትኛውም ዓይነት የዘር ማፅዳት" እርምጃን ተቃውመዋል።
ዋና ፀሐፊው፤ በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገ ስብሰባ ላይ የፍልስጤማውያን በራሳቸው መሬት ላይ እንደ የሰው ልጅ የመኖር መብት እየተሸረሸረ መሆኑን ተናግረዋል። "መላው [የፍልስጤም] ሕዝብ በአስፈሪ እና ስልታዊ በመሆነ መንገድ ሰብአዊነቱ ሲጓደል እና እንደ አጋንንት ሲደረግ" ዓለም ተመልክቷል ብለዋል።
ሌላኛዋ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገር ሳውዲ አረቢያ በበኩሏ ፍልስጤማውያን ከመሬታቸው "እንደማይንቀሳቀሱ" እና ሀገረ ፍልስጤም ካልተመሠረተች ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት እንደማታስተካክል አስታውቃለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ ግን የትራምፕ ዕቅድ "ታሪክ ቀያሪ" እና "ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ይህ ዕቅድ አሜሪካ በእስራኤል ፍልስጤም ግጭት ላይ የነበራትን እሳቤ ከመሠረቱ የናደ ነው።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ ጉብኝት ላይ ከነበሩት ኔትያናሁ ጎን ቆመው በሰጡት መግለጫ "አሜሪካ የጋዛ ሰርጥን ትቆጣጠራለች። በመሬቱም ላይ ሥራ እንሠራለን" ሲሉ ለዘጋቢዎች ተናግረዋል።
"[የመሬቱ] ባለቤት እንደሆናለን፤ ቦታው ላይ የሚገኙ ያልፈነዱ አደገኛ ቦንቦች እና ሌሎች መሳሪያዎችን የማክሸፍ፣ መሬቱን የማጽዳት እና የተበላሹ ህንጻዎችን የማስወገድ ኃላፊነት እንወስዳለን" ብለዋል።
እንደ ትራምፕ ገለጻ ይህንን ትልም ለማሳካት ፍልስጤማውያን ጋዛን ለቅቀው መውጣት እንዲሁም በዮርዳኖስ፣ በግብፅ እና በሌሎችም ሀገራት መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ስደተኞቹ ለመመለስ ይፈቀድላቸው እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ፤ "የዓለም ሕዝብ" በጋዛ እንደሚኖር ከተናገሩ በኋላም "ፍልስጤማውያንም" ሲሉ ተደምጠዋል።
የፍልስጤም አስተዳደር ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ይህንን ዕቅድ ተቃውሞታል። "ይህ ጥሪ ከባድ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰትን ያመለክታል" ያሉት ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ፤ "ሀገረ ፍልስጤም ሳይመሰረት በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት አይመጣም" ሲሉ አስገንዝበዋል።