ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ወደ ሌላ ቦታ "እንዲሰፍሩ" እንደሚፈልጉ ተናገሩ
ከአስር ቀናት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን እንደ ፍርስራሽ ቦታ ቆጥረው "ሁሉንም ነገር ስለማጽዳት" ሲናገሩ እነዚህ አስተያየቶች ምን ያህል የታሰቡ እንደነበሩ ግልጽ አልነበረም።
ነገር ግን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተቀብለው ባናገሩበት ወቅት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ግልስጤማዊያን ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
አክለው ሀገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ "ጋዛን ጠቅልላ ለመያዝ" እንደምትሻ አሳውቀዋል።
ትራምፕ፤ ጋዛን "ከቦምብ በማፅዳት እና ምጣኔ ሀብቷን በማሳደግ" የፍልስጤም አስተዳደርን በመካከለኛው ምስራቅ ልዩ ሥፍራ እንደሚያደርጓትም ተናግረዋል።
ፕሬዝደንቱ ጋዛ እስክትገነባ ድረስ ፍልስጤማዊያን ከጋዛ ውጭ ባሉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እንዲሰፍሩ ሐሳብ አቅርበዋል። አንዳንድ ሀገራት ይህን የትራምፕ ሐሳብ እንደማይቀበሉት ማሳወቃቸው አይዘነጋም።
በሁለተኛው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን አሜሪካን የጎበኙ የመጀመሪያ መሪ የሆኑት ኔታኒያሁ የትራምፕ ዕቅድ "ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ" እንደሆነ ተናግረዋል።
ነገር ግን ይህ አስተያየት በአለም አቀፍ ህግ ፊት ቅቡልነት የለውም።
የትራምፕ አስተያየት ለተራ ፍልስጤማውያን ከሚኖረው መልዕክት ባለፈ፤ በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ በተደረገው የተኩስ አቁም እና የታጋቾች ማስለቀቅ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
ትራምፕ እና ባለሥጣኖቻቸው ፍልስጤማውያን በቋሚነት ከጋዛ ለቀው ሌላ ቦታ "እንዲሰፍሩ" ያቀረቡትን ጥሪ እንደ በጎ ይመለከቱታል። ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት ጋዛ "ፈራርሳለች" የሚል ነው።
በአለም አቀፍ ህግ ህዝብን በግዳጅ ለማዘዋወር መሞከር በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን ፍልስጤማውያንም ሆኑ የአረብ ሀገራት ይህንን ፍልስጤማውያንን የማባረር እና ከመሬታቸው ለማፅዳት ከቀረበ ግልፅ ሐሳብ በቀር ሌላ ትርጉም አይሰጡትም።
ለዚህም ነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግብፅ እና ዮርዳኖስ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ "ሊወስዱ" እንደሚችሉ ሲጠቁሙ የአረብ መሪዎች ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ እየጨመረ የመጣውን ሐሳቡን ውድቅ ያደረጉት።
ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ኳታር፣ የፍልስጤም አስተዳደር እና የአረብ ሊግ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ እንዲህ ያለው እርምጃ "የአካባቢውን መረጋጋት አደጋ ላይ ይጥላል" ብለዋል።
ፍልስጤማውያንን በእስራኤል ቁጥጥር ስር ከተያዙ ግዛቶች ማባረር እና የአይሁድ ሰፈሮችን በእነሱ ቦታ ማስፋፋት በእስራኤል ውስጥ ያለው የአክራሪ ብሔርተኛ ቀኝ ዘመሞች የረጅም ጊዜ ፍላጎት ነበር።
እኒህ ቀኝ ዘመሞች እስራኤል እና ሐማስ የደረሱትን የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የማስለቀቅ ስምምነት ይቃወማሉ።
ጋዛን እገነባታለሁ ያሉት ትራምፕ ፍልስጤማዊያን እንዲመለሱ ይፈቅድላቸው እንደሆነ ተጠይቀው "የዓለም ሕዝብ" በሙሉ የሚኖርበት ቦታ ይሆናል ብለዋል።
በተጨማሪም ጋዛን ሲቆጣጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች ይሳተፋሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ "አስፈላጊውን እናደርጋለን" ብለዋል።
ትራምፕ ያቀረቡት ሐሳብ አሜሪካ በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ አንፀባርቃው የማታውቀው እና ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ያሳየ ነው ተብሏል።