አስከፊው የአሳድ ማሰቃያ እስር ቤት ምን ይመስላል?

ሳይድናያ የሚባለው እና በኮረብታማ አካባቢ የተገነባው እስር ቤት ለመድረስ ከመሃል ደማስቆ በመኪና ግማሽ ሰዓት ይፈጃል።

መግብያ በሩ በሶሪያ አብዮታዊ ባንዲራ ቀለማት በሆኑት አረንጓዴ፣ ነጭ እና ጥቁር ደምቋል። አዲሶቹ ቀለሞች የቦታውን አስከፊ ሁኔታ አልቀየሩትም።

በሩን ዘልቆ ለሚገባ ሰው ተመሳሳይ ጉዞ ያደረጉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያን ያጋጠማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያስብ ያስገድዳል።

እአአ በ2011 የሶሪያ ጦርነት ከጀመረበት ማግስት አንስቶ በሳይድናያ ከ30 ሺህ በላይ እስረኞች መሞታቸው ይገመታል። በአሳድ አገዛዝ ዘመን ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶች እና ህጸናት ጭምር የገቡበት አይታወቅም። ቁጥራቸው ከ100 ሺህ በላይ ይደርሳል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ በእዚህ እስር ቤት ያሳለፉ ናቸው።

ሌሎች የአሳድ እስር ቤት እንደሳይድናያ ጭካኔ አልተሞላባቸውም። በሌሎች እስር ቤቶች ስልክ መደወል እና ቤተሰቦች እንዲጎበኙ ይፈቀዳል።

ሳይድናያ ግን የጨለማው እና የበሰበሰው አገዛዝ ልብ ምት ነበር። ምን እንደተፈጠረ ሳይታወቀ እዚያ ተወስደው መገደልን መፍራት ሰፍኖ ነበር። የአሳድ መንግስት የማስገደድ እና የጭቆና ሥርዓትም ዋና መገለጫ ነበር።

ባለሥልጣናት እዚያ እነማን ታስረው እንደነበሩ ለቤተሰቦች አይነግሩም። ከዚህም የባሰ አለው ብለው እንዲፈሩ በመፍቀድ ሌላ ጫና መፍጠሪያ መንገድ ነው።

የቢቢሲው ዠርሚ ቦዌን አስፈሪ የሚባሉ በርካታ እስር ቤቶችን መመልከቱን ይገልጻል። የሊቢያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል ጋዳፊ በትሪፖሊ የነበራቸውብ አቡ ሳሊም እና በአፍጋኒስታኗ ካቡል አቅራቢያ የሚገኘውን ፑል-ቻርኪን ጨምሮ ሌሎች አስፈሪ እስር ቤቶች ነጻ በወጡ በቀናት ውስጥ በቦታዎቹ ተገኝቶ ተመልክቷል።

አንዳቸውም እንደሳይድናያ መጥፎ እና አደገኛ አልነበሩም። በተጨናነቁ ክፍሎች ውስጥ ወንዶች መጸዳጃ ቤት የመግባት ዕድል ባለማግኘታቸው በፕላስቲክ ከረጢቶች መሽናት ይገደዱ ነበር።

በሮቹ ሲሰበሩ መሬት ላይ ይተኙባቸው የነበሩባቸውን ብርድ ልብስ እና ሌላም የቆሸሸ ልብሳቸውን ትተው ወጥተዋል። በሳይድናያ የሚፈጸሙ ማሰቃያዎች እና ግድያዎች ተመዝግበዋል።

በመጪዎቹ ወራት ውስጥ በእስር ቤቱ ስለሚፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊቶች አዳዲስ መረጃዎች ከቀድሞ እስረኞች እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ሳይድናያ ሲደርሱ አሳድ አገዛዛቸውን ለማዳን የሰበሩትን አገር ለማስተካከል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማየት ይችላሉ። አሁን እስር ቤቱ ክፍት ሆኗል። ሶሪያ የገጠማት ፈተና ሁሉ ማሳያም ሆኗል።

ቁ የነበረውን እውነታ እንዳያጠፉ ማድረግ ለወደፊቱ መጻኢ ዕድል ትልቅ አካል ነው።

መዝገቡ

አንዱ ፈተና ገዥው አካል በተጎጂዎቹ ላይ ያደረገውን በትክክል መመዝገብ ነው። ባለፈው አንድ ሳምንት በጎ ፈቃደኞች የሳይድናያን መዝገብ ለመጠበቅ ወደ እስር ቤቱ ሄደዋል።

ወረቀቶች በየቢሮዎች እና በእስር ቤቱ ግቢ ውስጥ ጨምር ተበታትነዋል። ቤተሰቦች የሚያውቁትን ስም፣ ቀን ወይም ቦታ ለማግኘት በማሰብ ወረቀቶቹን እያነሱ አየት አየት አድርገው ያስቀምጣሉ።

የወረቀቶቹ መበታተን አንድ ሰው በበሽር አል አሳድ ሶሪያ የተደረገውን ነገር ለማጥፋት የሞከረ ይመስላል።

ሳፋና ባክሌህ የተባለች ሙዚቀኛ ለበጎ ፈቃደኞቹ ጭንብል እና ጓንቶችን እያከፋፈለች ፎቶግራፍ ማንሳትን ጨምሮ ሰነዶችን ስለሚሰበሰብበት ሁኔታ መመሪያ ትሰጣለች።

ሳፋና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሌሉበት እና ማስረጃዎች እና ሰነዶች እየጠፉ በመሆናቸው በራሳቸው ተነሳሽነት እየሠሩ ነው ትላለች።

"አንድ ቤተሰብ እንኳን የሚፈልገውን ሰው እዚህ አለመኖሩን ቢያውቅ፣ ሞቷል ቢባል ወይም ሆስፒታል ውስጥ መሞቱን ቢያውቅ ለእኔ በቂ ነው። በጣም የተመሰቃቀለ ነው. . . ይህን ሁሉ ትርምስ የሚዘግቡት ዓለም አቀፍ ተቋማት የት ናቸው?" ትላለች ሳፋና።

የጠፉ ሰዎች የት ደረሱ የሚለው ብቻ አይደለም የሚጠበቀው። አንድ ቀን ወንጀለኞች ለፍርድ ሊቀርቡ ይችላሉ። ሰነዶቹ ደግሞ ማስረጃ ይሆናሉ።

በጎ ፈቃደኞቹ ያገኙት እውነቷ አስደነግጧቸዋል። ሁሉም ሶሪያውያን እስር ቤቶቹ መጥፎ መሆናቸውን ቢያውቁም ሳይድናያ ከጠበቁት በላይ የከፋ ነበር። ከበጎ ፈቃደኞች አንዷ የሆነችው ዊዳድ ሀላቢ ለአንድ ሰዓት ያህል ስትመለከት ቆይታ የፊትን ጭምብሏን አውልቃ ማልቀስ ጀመረች።

"እዚህ ያየሁት ለሰው ልጅ የማይመጥን ህይወት ነው። እንዴት እንደሚኖሩ፣ ልብሳቸው፣ እንዴት እንደተነፈሱ፣ ምን እንደበሉ፣ ምን እንደተሰማቸው? ለማሰብ ሞክሪያለሁ" ትላለች።

"በጣም አስፈሪ ነው. . .አሳፋሪ። በየወለሉ ላይ የሽንት ከረጢቶች አሉ። መጸዳጃ ቤት መሄድ ስለማይችሉ ሽንት በፕላስቲክ ከረጢት መጠቀም ነበረባቸው። ሽታው ከባድ ነው፤ ጸሐይ ወይም ብርሃን አያገኙም። እኛ መደበኛ ህይወታችንን ስንኖር ሰዎች እዚህ ይኖሩ ነበር ብዬ ማመን ይከብደኛል።"

ፍትህ ወይስ በቀል?

ለሶሪያውያን እና ለአዲሶቹ አስተዳዳሪዎች ጥፋተኞችን ተከታትሎ ለመቅጣት ከባድ ይሆንባቸዋል። ባሽር አል አሳድ ከቤተሰባቸው ጋር ወደ ሩስያ ተሰደዋል። እንደማንኛውም የቤተሰቡ አባል በጥቃት እና በሙስና ስሙ የሚነሳው ወንድማቸው ኢራቅ ውስጥ እንዳለ ይገመታል።

የአሳድ የአጎት ልጆች ወደ ሊባኖስ ለማምለጥ ሲሞክሩ በአማጺያኑ እጅ ወድቀዋል። ከመካከላቸው አንደኛው በተኩስ ልውውጥ መገደሉን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከሳምንት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ መኪኖች ተስፋ የቆረጡ እና ከአገዛዙ ጋር የተወሰነ ግንኙነት ያላቸው እና በአዲሲቷ ሶሪያ ለመኖር ስጋት አለብን ብለው የሚያምኑ ቤተሰቦች ወደ ሊባኖስ ድንበር ለመግባት ተሰልፈው ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ወደ አገራቸው ለመግባት በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ ነበር።

ውሎ ይደር እንጂ በሽር አል አሳድ፣ የቤተሰቡ አባላት እና አንዳንድ ለአገዛዙ ጠመንጃ የያዙትን ለመክሰስ ህጋዊ ሂደት ሊኖር ይችላል። ማስረጃ ማሰባሰብ ለዚህ ጠቃሚ ይሆናል። በአገዛዙ መጨረሻዎቹ ሰዓታት እና ከዚያ በኋላ በተፈጠረው ግራ መጋባት ወቅት ተጠያቂዎች በመሸሻቸው ለፍርድ ማቅረብ ከባድ ይሆናል ማለት ነው።

በሳይድናያ እስር ቤት ዘመዶቻቸውን ለማግኘት የሚጥሩ ቤተሰቦች በሚያዩት ነገር ሁሉ እየተሸበሩ ነው።

የተወሰኑ ሰዎች ግቢው ውስጥ ተሰብስበው ከመሬት ያነሱትን ፋይል እየወረወሩ በዝምታ እያጨሱ ነበር። ሁሉም ፍላጎታቸው መጪው ጊዜ በፍትህ ላይ መገንባት ያለበት መሆኑን ነው። የጠፉ ልጆች፣ ወንድሞች እና የአጎት ልጆችን የሚፈልጉት ሰዎች ሳይድናያ የጅምላ መቃብር ስፍራ ነው ብለው ይጠሩታል። የበሽር አል አሳድን አንገት ተቆርጦ ማየት ይፈልጋሉ። ከመካከላቸው አንዱ "አንገቱ መቆረጥ እንዳለበት" ሲናገር ሌሎቹም በመስማማት አጉረመረሙ።

አህመድ የተባለው ወጣት በህልሙ ስለሚያየው የሚፈልገው ወንድሙ በህይወት እንዳለ እንደሚያስብ ተናግሯል። አህመድም በሳይድናያ ሦስት ዓመታትን አሳልፏል።

"በጣም መጥፎ ጊዜ ነበር። ምግብ፣ ሁሉም ነገር ስቃይ ነበር። እየተሰቃየን ነበር" ብሏል።

እአአ በ2014 በስለላ ድርጅት ባልደረቦች ቁርሱን ከሚበላበት የተወሰደበት መሐመድ ኻላፍ ልጁ ጀብርን ሲፈልግ ነበር።

"እኛ ብዙ ነን። ከቃሚሽሊ፣ ከሃሳካ፣ ከዲር አል-ዙር፣ ከአል ራቃ የመጡ ሰዎች ዘመዶቻቸውን እየፈለጉ ነው። አሁንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦቻቸውን ልጆቻቸውን በየመንገዱ እየፈለጉ ነው። እኔ ብቻ አይደለሁም" ይላል።

በአንደኛው ክፍል ውስጥ የአሌፖ ወጣቶች ተበታትነው ያገኙትን የእስር ቤት የደንብ ልብስ ቆርቆሮ ላይ እያቃጠሉ የታሰሩ እና የጠፉ ወንድሞቻቸውን እየፈልጉ ነበር።

እንደሌሎች በሳይድናያ መረጃ ወይም አስከሬን እንደሚፈልጉ ሰዎቹ ሆቴል ለማረፍ የሚሆን ገንዘብ አልነበራቸውም። እናም ወንድሞቻቸው ታስረው እንደተገደሉ በሚያምኑበት እስር ቤት ለመዋል ለማደር ተገደዋል።

ከአሌፖ ከመጡት አንዱ የሆነው ኢዜዲን ኻሊል እአአ መስከረም 1 ቀን 2015 በገዥው መንግስት የተወሰደውን ወንድሙን ዜና ይፈልጋል።

"በሕይወት ስለሞን ስለመሞቱ አናውቅም። ከሞተ አስከሬኑን ሊሰጡን ይገባል። መሞቱን ይንገሩን። እኛ ማወቅ ብቻ እንፈልጋለን። ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ እንፈልጋለን።"

ጓደኛው መሐመድ ራድዋን ደግሞ እአአ በ2012 የታሰሩትን ወንድም እና የአጎቱን ልጅ እየፈለገ ነው። አገዛዙ ከመውደቁ በፊት በነበረው ምሽት 22 ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው መኪናዎች አስከሬኖችን ለማንሳት ወደ እስር ቤቱ መግባታቸውን ወሬዎች እየተናፈሱ ነበር። ወሬው ባይረጋገጥም ግን መሐመድ እና ኢዘዲን እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነበሩ።

መሐመድ የተዳከመ ቢመስልም በንዴት ጦፏል። ለአሳድ መልዕክቱን አስተላለፈ።

"አሳማ ሆይ 22ቱን ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው መኪናዎች የት ወሰድካቸው? በዚህ ወንጀል የተሳተፈ ሁሉ እና በሳይድናያ ማረሚያ ቤት ያገለገለ ሁሉ ለፍርድ ይቅረብ። ሁሉም! በጽዳት ሥራ ላይ የተሠማሩ ቢሆንም ሁሉም መቅረብ አለባቸው" አለ።

"ምክንያቱም እየሆነ ያለውን ነገር ካወቁ ቢያንስ ወዳጆቻቸው እንደተገደሉ፣ እንደታረዱ፣ እንደተሰቀሉ ወይም እንደተሰቃዩ ለታራሚ ቤተሰቦች መንገር ነበረባቸው።"

ሁለቱም "አላህ በቂዬ ነው፣ እርሱም የሁሉም ጉዳይ ባለቤት ነው" በማለት ኢስላማዊ ጸሎት አድርሰው ጨርሱ።

አሳድ እና ጀሌዎቹ ሲቀጡ ለማየት ያላቸው ረሃብ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከሚጠበቁ ክስተቶች አንዱ ሊሆን ይችላል። ሶሪያውያን ያሰቃዩዋቸው ሰዎች ሲቀጡ ማየትን ያልማሉ።

ሙስና

የአሳድ ጎሳ ሶሪያን እንደ ባንክ ሒሳቡ ተጠቅሞባታል። ትርፋማ ሊሆኑ በሚችሉ ንግዶች ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ችለዋል። ትርፋማውን የቴሌኮም እና የሞባይል ገበያን ተቆጣጥረዋል። እነሱ ገንዘብ ሲሰበስቡ፣ ሶሪያውያን በጦርነት በተዳከመው ኢኮኖሚ ኑሮአቸውን ለመግፋት ሲታገሉ እና በዘር እና በሙስና በተጨማለቁ የአገዛዙ ወዳጆች እጅ ሲወድቁ ከረሙ። አዲሶቹ የሶሪያ ገዥዎች ትልቅ ዕዳ ወርሰዋል። አገሪቱ ገንዘብ ምንዛሪም እጅጉን ተዳክሟል። ሁለት መቶ ዶላር የፕላስቲክ የቆሻሻ መጣያ ከረጢት በሚሞላ የሶሪያ ፓውንድ ይመነዘራል።

ሙስና እስከ እስር ቤት ድረስ ዘልቋል። ለዓመታት ተስፋ የቆረጡ ተጎጂዎች እና ቤተሰቦች እስር ቤት ላለመወርወር ትልቅ ገንዘብ ለመክፈል ተዘጋጅተው ነበር።

ሃሰን አቡ ሽዋርብ ሞት ለሽብር በሚለው ቅጣት 11 ተፈርዶበታል። ይህ ህግ የአሳድ መንግስት ለአመጺያን ይጠቀምበት የነበረውን ቃል ነው። የ31 ዓመቱ ሃሰን የትጥቅ ቡድን ውስጥ ገብቶ አያውቅም። ፓስፖርት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን አግኝቶ በካናዳ ለመማር የቀረበለትን ጥያቄ ለመቀበል በሚሰናዳበት ወቅት መታሰሩን ተናግሯል።

ወንድሙ እንደተናገረው ቤተሰቡ ሃሰንን ነጻ ለማውጣት በአምስት የተለያዩ አጋጣሚዎች 50 ሺህ ዶላር ጉቦ ከፍለዋል። በሁሉም አጋጣሚዎች ገንዘቡን የተቀበሉ ሙሰኛ ባለስልጣናት ሃሰንን ሳይፈቱ ቀርተዋል። አገዛዙ ከመውደቁ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሌላ ሙሰኛ ዳኛ ሃሰንን ለመፍታት ለሌላ 50 ሺህ ዶላር እንደሚሰጠው ተነገረው።

ሃሰን አቡ ሽዋርብ በወታደራዊ መመርመሪያ ጣቢያ ለ80 ቀናት ታስሮ በነበረበት ወቅት ስቃይ ደርሶበታል። ከደረሱበት ጉዳቶች መካከል አሰቃዮቹ አንድ እግሩን ሰብረውታል። ሃሰን ከሦስት ቀናት ስቃይ በኋላ ህይወቱ ካለፈ የ49 ዓመት ሰው ጋር አብረው እንደነበሩ ተናግሯል። በኋላም የእስር ቤቱ ጠባቂዎቹ ግለሰቡ በስትሮክ ሞቷል ሲሉ መዝግበዋል።

ሃሰን ወደ ቤት በመመለሱ በጣም ተደስቶ ነበር።"እናቴ ከ11 ዓመታት በኋላ ስትይዘኝ የነበረውን ስሜት መግለጽ አልችልም። ወደ ቤትህና ወደ ሰፈርህ መመለስን የመሰለ ነገር የለም።"

እንደ ብዙ ሶሪያውያን ሃሰን ስለወደፊቱ ያለው ብሩህ ተስፋ የሚጀምረው የቀድሞ የአገዛዝ መሪዎች እና ተባባሪዎች ለድርጊታቸው እንዲሰቃዩ ቆርጦ በመነሳት ነው።

"መቀጣት አለባቸው። እኛ የሰው ልጆች እንጂ ድንጋይ አይደለንም:: የገደሉ በአደባባይ ይገደሉ:: ይህ ካልሆነ ግን ይህንን ጊዜ አናልፍም።"

"መርሳት እና ወደ ፊት መጓዝ አለብን። ይህ ለመላው ሶሪያውያን ደስታ ነው። ወደ ሥራችን እና ኃላፊነታችን መመለስ አለብን። መርሳት አለብን። የትላንቱን አልፈነዋል። ሃዘኑ ከኋላችን ነው።"

የሃያት ታህሪር አል ሻም መሪ በጦርነት ጊዜ ይጠቀምበት የነበረውን አቡ መሐመድ አል ጆላኒ የሚለውን ስሙን በመተው ትክክለኛ ስሙ አህመድ አል ሻራን መጠቀም ጀምሯል። የስም ለውጡ ወደ ፊት የመመልከትን መልዕክት ይዟል። አህመድ አል-ሻራ ፍትህን በእጃቸው የሚያስገቡ ሰዎች የሚፈትሩትን ትርምስ ካልፈለገ ፍትህን ማስቀደም ይኖርበታል።

መጪው ጊዜ ከባድ ነው። ያለፈው ጊዜ በህመም የተሞላ ነው። ደማስቆ ውስጥ አንድ የጋራ ዕዳ ከህዝብ ጫንቃ ላይ የተነሳ ያህል ነው የተፈጠረው ስሜት።

ሶሪያውያን ችግሮቻቸው ምን ያህል ጥልቅ እንደሆኑ ያውቃሉ። በአሳድ ውድቀት የተፈጠረውን ብሩህ ተስፋ ለመጠበቅ፣ ሶሪያውያን ለውጥን ማየት ይፈልጋሉ።