በትራምፕ ታሪፍ የተጣለባት ቻይና የአጻፋ እርምጃ ወሰደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይና ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ ቻይና በአጸፋው ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ታሪፍን በአሜሪካ ምርቶች ላይ ጥላለች።
በሁለቱ ታላላቅ የዓለም ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገራት መካከል የተጀመረው የንግድ ጦርነት በተባባሰበት በዚህ ሰዓት ትራምፕ ሌሎች ሀገራት ላይም ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።
ባለፈው ማክሰኞ ትራምፕ በሁሉም የቻይና ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ መጣላቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህ በተሰማ በደቂቃዎች ውስጥ ቻይናም ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃ ነበር።
ትላንት ዕሁድ ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ የብረት እና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣል አስታውቀው ካዘሬ ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
ትራምፕ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሌሎች ሀገራት ላይም ታሪፍ ይጣላል ያሉ ሲሆን ሀገራቱን ግን በስም አልጠሩም።
ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ ከጣለቻቸው ታሪፎች መካከል የድንጋይ ከሰል እና በፈሳሽ መልክ ያለ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ የጣለቸው 15 በመቶ ታሪፍ ተጠቃሽ ነው።
በተጨማሪም በአሜሪካ ድፍደፍ ነዳጅ፣ የግብርና ማቀናባበሪያ ማሽኖች እና ከፍ ያለ መጠን ያላቸው የመኪና ሞተሮች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ጥላለች።
በሌላ በኩል ቻይና በዓለም ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው 25 የብረት ዓይነቶች የምታደርገው ኤክስፖርት ላይ ቁጥጥሯን አጥብቃለች። እነዚህ ብረቶች አንዳንዶቹ ለኤሌክትሪክ እና ወታደራዊ መሳሪያዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
ትራምፕ የቻይና ብረት እና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የሚጥሉትን የ25 በመቶ ታሪፍ ከማሳወቃቸው አስቀድሞ በሜክሲኮ እና ካናዳ ሁሉም ምርቶች ላይ እጥላለሁ እያሉ ሲዝቱበት የነበረውን የ25 በመቶ ታሪፍ ለማስቀረት ከሀገራቱ ጋር ተስማምተው ነበር።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸውም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው ነበር።
በብረት ላይ የ25 በመቶ በአልሙኒየም ላይ ደግሞ የ10 በመቶ ታሪፍ ጥለው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ የካናዳ፣ ሜክሲኮ እንዲሁም የብራዚል የንግድ ተቋማት ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ፍቃድ አግኝተዋል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ የሚጥሉ ሀገራት ላይ ተመሳሳይ የአጸፋ ታሪፍ እንደሚጥሉ ቃል ሲገቡ ሰምብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሚለኩ ተሽከርካሪዎች አሜሪካ ከምትጥለው ታሪፍ ከፍ ያለ እንደሆነ በመግለጽ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ተዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት ትራምፕ በአውሮፓ ህብረት ላይ "በጣም በቅርቡ" ታሪፍ እንደሚጥሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ሆኖም ከዩናየትድ ኪንግደም ጋር ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚችል ጠቁመዋል።












