ትራምፕ የአሜሪካ አንድ ሳንቲም እንዳይመረት ለግምጃ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጡ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት አንድ ሳንቲም ማምረት እንዲያቆሙ ታዘዙ።

ፔኒ እየተባለ የሚታወቀው የአሜሪካ አንድ ሳንቲም እንዳይመረት ትዕዛዝ ያስተላለፉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።

ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ነው ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፉት። "የታላቋ ሀገራችንን በጀት እንታደግ። አንድ ሳንቲም መቆጠብ ከቻልን እንኳ አንድ ነገር ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ይህ ውሳኔ ወጪ ለመቀነስ የሚደረግ መሆኑን በመልዕክታቸው አትተዋል።

ዶጅ በተባለ ምሕፃረ ቃል የሚታወቀው ኢላን መስክ የሚያስተዳድረው መሥሪያ ቤት ባለፈው ወር አንድ ሳንቲም ማምረት ኪሳራ ነው ሲል በኤክስ ገፁ ፅፎ ነበር።

የአሜሪካ አንድ ሳንቲም አቅም እና ጥቅሙን በተለመከተ ባለፉት ዓመታት በርካታ ክርክሮች ነበሩ።

"ይህ አላስፈላጊ ወጪ ነው" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ፅፈዋል።

የአሜሪካ አንድ ሳንቲም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"የግምጃ ቤት ሚኒስትሩ ፔኒዎችን ማምረት እንዲያቆም ትዕዛዝ አስተላልፊያለሁ" ብለዋል።

ዩኤስ ሚንት የተባለው ሳንቲም አምራች ተቋም በ2024 ባወጣው ሪፖርት አንድ ሳንቲም አምርቶ ለማሰራጨት 3.69 ሳንቲም ወጪ ይሆናል ብሎ ነበር።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እና የኮንግረስ አባላት ከዚህ ቀደም አንድ ሳንቲም እንዳይመረት ያመጡት ሐሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል።

አንድ ሳንቲም መመረት መቆም አለበት የሚሉ ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉት ዚንክ እና ኮፐር የተባሉት ማዕድናት ለወጪ ይዳርጋሉ ሲሉ ይከራከራሉ። ምርቱ መቆሙን የሚቃወሙ ደግሞ አንድ ሳንቲም የሸቀጥ ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል፤ እንዲሁም እርዳታ ለሚሰበስቡ ድርጅቶች መልካም ነው ይላሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ሀገራትም አንድ ሳንቲም ማምረት እያቆሙ ነው።

ካናዳ አንድ ሳንቲም ማምረት ያቆመችው በአውሮፓውያኑ 2012 ነው። በወቅቱ ሳንቲሙን ለማምረት የሚወጣው ወጪና የአንድ ሳንቲም የማምረት አቅም መዳከም እንደ ምክንያት ቀርበው ነበር።

ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ የጥሬ ገንዘብ ጥቅም ላይ መዋል መቀነስን ተከትሎ በ2024 አዲስ ሳንቲም አላተመችም። ባለሥልጣናት ገበያ ላይ ያለው የሳንቲም ዝውውር በቂ ነው ይላሉ።

የዩኬ ግምጃ ቤት እንዳለው አንድ ሳንቲም እና ሁለት ሳንቲም መመረት ባይቆምም ሰዎች ጥሬ ገንዘብ መሸከም እያቆሙ በመሆናቸው ለዓመታት እኒህ ሳንቲሞች አልተመረቱም።