ኢትዮጵያ የ27ቱን አስከሬኖች ጉዳይ ለማጣራት ባለሙያዎችን ወደ ዛምቢያ ልትልክ ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት ዛምቢያ ውስጥ መንገድ ዳር ተገኙ ስለተባሉት የኢትዮጵያውያን አስከሬኖች ጉዳይ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በመተባበር እንደሚያጣራ አስታወቀ።

ኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉት 27 አስከሬኖች እሁድ ዕለት ከዛምቢያ ዋና ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ መንገድ ዳር መገኘታቸውን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ ተከትሎ ነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምርመራ እንደሚያደረግ የገለጸው።

ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊያቋርጡ የነበሩ ናቸው የተባሉትን ሟቾች ጉዳይ ወደ ስፍራው ባለሙያዎችን በመላክ ከዛምቢያ መንግሥት ጋር ተባብሮ ማንታቸውን እንደሚያረጋግጥ አመለክቷል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው የተባሉ የ27 ሰዎች አስከሬን በደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ዛምቢያ መዲና ሉሳካ አቅራቢያ መንገድ ዳር “ተጥለው” የተገኙት እሁድ ዕለት ነው።

ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን በሚገኘው ንግዌሬሬ በተባለው አካባቢ መንገድ ዳር ተጥለው የተገኙት አስከሬኖች አገሪቱን አቋርጠው ይጓዙ የነበሩ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።

የአገሪቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዳኒ ምዋሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በድብቅ በዛምቢያ በኩል ሲሸጋገሩ የነበሩ ስደተኞች በሚጓዙበት ተሽከርካሪ ውስጥ አየር አጥሯቸው ሳይሞቱ እንዳለቀረ አመልክተዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም ከአስከሬኖቹ መካከል አንድ በሕይወት የተረፈ ሰው “ለመተንፈስ ሲያጣጥር” ተገኝቶ በአካባቢው ወደሚገኝ ሆስፒታል መወሰዱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሕገወጥ መንገድ የሚጓዙ ስደተኞች ከሚተላለፉባቸው አገራት መካከል ዛምቢያ አንዷ ናት።

የፖሊስ ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት የንግዌሬሬ አካባቢ ነዋሪዎች አስከሬኖቹን ያገኙት እሁድ ጠዋት በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር 12 ሰዓት አካባቢ ነው።

ፖሊስ በአስክሬኖቹ ላይ ካደረገው ምርመራ ለመረዳት እንደቻለው፤ ሕይወታቸው አልፎ ከተገኙት ሰዎች አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መሆናቸውን ከሟቾቹ ላይ ባገኛቸው ሰነዶች አረጋግጧል።

የ27ቱ ሰዎች አስከሬን መገኘትን ተከትሎ የዛምቢያ ፖሊስ ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው፣ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሕገወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር በድንበር አካባቢ በመኪኖች ላይ የሚያደርገውን ፍተሻ እንደሚያጠናክር ገልጿል።

“የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራችን እንዳመለከተው ሁሉም ወንዶች የሆኑና እድሜያቸው በ20 እና በ38 ዓመት ውስጥ የሚገመቱ 28 ሰዎች መንገድ ዳር ተጥለው አግኝተዋል” ብሏል ፖሊስ ስለክስተቱ ባወጣው መግለጫ።

ጨምሮም አስከሬኖቹ ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን በምትገኘው ንግዌሬሬ አካባቢ ሚንዉድ ንኾሲ በተባለ ስፍራ ባለው ቺሚኑካ በተባለ መንገድ ዳር ባልታወቁ ሰዎች ተጥለው መገኘታቸውን አመልክቷል።

ፖሊስ ከአካባቢው ነዋሪዎች ያገኘውን ጥቆማ ተከትሎ ሁሉም አስከሬኖች ወደ ዛምቢያ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የአስከሬን ክፍል መወሰደቻው ተገልጿል።

ባለፈው ጥቅምት ወር በተመሳሳይ የዛምቢያ ጎረቤት በሆነችው ማላዊ ውስጥም የ25 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን አስከሬን በጅምላ የተቀበረበት ስፍራ መገኘቱ ይታወሳል።

የማላዊ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ የእንጀራ ልጅን ከዚሁ ክስተት ጋር የሚያያይዝ ማስረጃ በማግኘቱ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ ለሕይወት አደገኛ በሆነ ሁኔታ በርካታ አገራትን በማቆራረጥ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ይሞክራሉ።

የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የማላዊ እና የዛምቢያ ፖሊሶች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ድንበር ያቋረጡ ናቸው ያሏቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያንን መያዛቸውን በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።

አሁንም ድረስ በርካቶች የአገራቱን ድንበሮች በሕገወጥ መንገድ በመሻገር ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ ባሻገርም በርካታ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በረሃብ እና በውሃ ጥም፣ በአውሬ በመበላት እና አሁን እንዳጋጠመው በርካታ ሆነው ተጨናንቀው በድብቅ በሚጓዙባቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ታፍነው ለሞት ተዳርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (አይኤምኦ) እንደሚለው ከአውሮፓውያኑ 2014 አንስቶ በአፍሪካ ውስጥ 12ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች የደረሱበት እንደማይታወቅ መዝግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዛምቢያ ኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ባለፈው ሐሙስ እንዳስታወቀው 10 ኢትዮጵያውን በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በመግባታቸው ለእስር መዳረጋቸውን ገልጾ፣ ከመካከላቸው ሁለቱ መታመማቸውን አመልክቷል።

በተጨማሪም የዛምቢያ መንግሥት የዜና እና የመረጃ አገልግሎት እንዳስታወቀው በርካታ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ከአገሪቱ እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት በሕገወጥ መንገድ ወደ ዛምቢያ ገብተው የሚገኙትን ኢትዮጵያውንን ቁጥር ለመቀነስ እየተወሰደ ካለው እርምጀ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ገደማ 34 ኢትዮጵያውን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ተብሏል።