ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማይናማር ጦር በአንድ ገዳም ላይ 28 ሰዎችን በመግደል ተከሰሰ
በደቡብ ሻን ግዛት በሚገኝ አንድ ገዳም ቢያንስ 28 ሰዎች በማይናማር ጦር ተገድለዋል ተባለ።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ናይ ኔይን በምትባል መንደር ላይ ወታደሮች በከባድ መሳሪያ ጥቃት መክፈታቸውን መንግሥትን እየታገለ ያለው አማጺ ቡድን፣ የካረኒ ህዝቦች መከላከያ ኃይል (ኬኤንዲኤፍ) አስታውቋል።
በማይናማር ከሁለት ዓመት በፊት የተፈጸመውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በጦሩ እና በታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖች መካከል እየተደረጉ ያሉ ጦርነቶች አስከፊነታቸው ጨምሯል።
ከነዚህም መከከል ዋና መዲናዋ ናይ ፒ ታው ከታይላንድ ጋር በሚዋሰነው ድንበር መካከል ያለው አካባቢ አንዱ ሲሆን ስፍራው ከባድ ውጊያዎችን አስተናግዷል።
ቅዳሜ ከሰዓት ጦሩ በአየር ኃይልና በከባድ መሳሪያዎች በመታገዝ ወደ መንደሩ በመግባት በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው ያገኟቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አንደገደሉ ኬኤንዲኤፍ አስታውቋል።
ከኬኤንዲኤፍ የተገኘ ቪዲዮ እንደሚያሳየ ቢያንስ 21 አስከሬኖችን ያሳየ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የተወሰኑት የቡድሃ መነኮሳት የሚለብሱትን ብርቱካናማ ካባ የለበሱም ይገኙበታል።
አስከሬኖቹ በበርካታ ጥይቶች ተበሳሳስተዋል። ቪዲዮው በተጨማሪ የገዳሙ ግድግዳዎች በጥይት ተበሳሳስቶ አሳይቷል።
“ጦሩ መንደርተኞቹን በገዳሙ ፊት ለፊት እንዲሰለፉ አድርጎ መነኮሳቱን ጨምሮ ሁሉንም በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት እንደገደላቸው እናምናለን” በማለት የኬኤንዲኤፍን ቃለ አቀባይን ዋቢ አድርጎ የሃገር ውስጥ ጋዜጣ የሆነው ካንታራዊዲ ታይምስ ዘግቧል።
ቡድኑ ሌሎች ሰባት አስከሬኖችን በትንሿ መንደር ላይ ማግኘቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጦሩ በመንደሩ ላይ አነጣጥሯል ባለው ጥቃት በአካባቢው ዙሪያ ያሉ አንዳንድ ህንጻዎች እና ቤቶች መቃጠላቸውንም ቡድኑ አክሎ ገልጿል።
የመንደሩ ነዋሪዎች በአካባቢው ከፍተኛ ክብር በሚሰጣቸው መነኮሳት ባሉበት ገዳም መጠለላቸው ከጥቃቱ እንደሚያተርፋቸው ያምኑ ነበር ተብሏል። ጦሩ ከመድረሱ በፊትም በመንደሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል።
ስለደረሰው ጥቃት ዝርዝር ሁኔታ ለማጣራት አስቸጋሪ ቢሆንም ባልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አረመኔያዊ ጥቃቶች ለማይናማር አዲስ አይደሉም።
በተለይም ጦሩ ስልጣን በመፈንቅለ መንግሥት መቆጣጠሩን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ለዚህም የተሰጠው ምላሽ ከባድ ጥቃቶች መሆኑ ተነግሯል።