ቀይ ባሕር ውስጥ ያሉ እስያን ከአውሮፓ የሚያገናኙ ገመዶች መቆረጣቸው ተገለጠ

ቀይ ባሕር ውስጥ ያሉ እስያን ከአውሮፓ የሚያገናኙ በርካታ ገመዶች መቆረጣቸውን አንድ የቴሌኮም ኩባንያ እና የአሜሪካ ባለሥልጣን ገለጡ።

መቀመጫውን ሆንግ ኮንግ ያደረገው ኤችጂሲ ግሎባል ኮሚዩኒኬሽንስ እንዳለው ከ15 ገመዶች አራቱ በመበጣሳቸው ምክንያት ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ተገዷል።

ገመዶቹ በምን ምክንያት እንደተበጠሱ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

የአሜሪካው ባለሥልጣን በበኩላቸው ገመዶቹ ሆነ ተብለው ይቆረጡ አሊያም በመርከቦች መልኅቅ ይጎተቱ ለማወቅ ምርመራ ጀምረናል ብለዋል።

በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና ያለው የየመን መንግሥት ባለፈው ወር በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር ወለል ላይ ያሉ ገመዶችን ሊያጠቁ ይችላሉ ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

የየመንን ቀይ ባሕር ሰሜናዊ ጠረፍ አብዛኛውን ክፍል የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ባለፈው ሳምንት ገመዶች አልበጠስንም ሲሉ አስተባብለዋል።

አማፂያኑ አክለው ገመዶቹ ተጎድተውም ከሆነ በአሜሪካ እና በብሪታኒያ ጦር ጥቃት ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ወቅሰዋል።

የሁቲ አማፂያን በኤደን ባሕረ-ሰላጤ በኩል የሚያልፉ የጭነት መከርቦችን ዒላማ ማድረጋቸውን ተከትሎ የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ኃይሎች የአፀፋ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ሁቲዎች እንደሚሉት ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በጋዛ በሚደረገው ጦርነት ለፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ነው።

ኤችጂሲ ግሎባል ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ቀይ ባሕር ውስጥ ካሉ ገመዶች አራቱ መቆረጣቸውን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ ድርጅቱ ወደ አውሮፓ የሚሄደውን ኔትዎርክ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኝ ገመድ በመተካት ደንበኞቹ አገልግሎት እንዳይቋረጥባቸው ማድረግ ችሏል።

የአፍሪካው የቴሌኮም ድርጅት ሲኮም “ባደረግነው የመጀመሪያው ዙር ማጣራት ገመዱ የተበጠሰው የየመን ግዛት በሆነው የቀይ ባሕር ክፍል ላይ ነው” ሲል ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግሯል።

አንድ የፔንታገን ባለሥልጣንም ሲቢኤስ ለተሰኘው የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃል የቴሌኮም ገመዶች ጉዳት እንደደረሰባቸው አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት ግሎብስ የተሰኘው የእስራኤል ድረ-ገፅ አራቱ ገመዶቹ የተበጠሱት በየመን አማፂያን ነው ብሎ ቢጽፍም ማስረጃ ግን ማቅረብ አልቻለም።

ስካይ ኒውስ አረቢያ በበኩሉ ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ የየመን አማፂያን ቀይ ባሕር ውስጥ ገመዶቹን “እያፈነዱ ነው” ብሏል።

የሁቲ አማፂያን እኒህን ወቀሳዎች አይቀበሏቸውም።

በሌላ በኩል የሁቲ አማፂያን የላይቤሪያ ባንዲራ እያውለበለበች ቀይ ባሕር ላይ ስትጓዝ የነበረች የስዊድን መርከብ ላይ ሁለት ሚሳዔሎች መተኮሳቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ገልጧል።

ከተተኮሱት አንደኛው ሚሳዔል መርከቧን ቢያገኛትም በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም።

የሁቲ ወታደራዊ ቃል-አቀባይ ያህያ ሳሬያ መርከቧ የእስራኤል ናት ብለው “የእስራኤል መርከቦች በእኛ በኩል በፍፁም አያልፉም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።