አሜሪካ የሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላቸው ዜጎቿ ለአስገዳጅ ምልመላ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አስጠነቀቀች

በሞስኮ የአሜሪካ ኤምባሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ በሩሲያ ያሉ ዜጎቿ አገሪቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ካለበለዚያ በዩክሬን ጦርነት ለአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ሊጋለጡ እንደሚችሉ አስጠነቀቀች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሩሲያ ላሉ ዜጎቹ ባወጣችው አዲስ ማስጠንቀቂያ ሩሲያ የአሜሪካና-ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላቸውን ነዋሪዎች ለመቀበል ፍቃደኛ ላትሆን ትችላለች ብሏል።

ከአስገዳጅ ምልመላም በተጨማሪ እስር ሊጠብቃቸው እንደሚችልም ነው የተገለጸው።

ማስጠንቀቂያው አያይዞም በሩሲያ ያሉ አሜሪካውያን ቀድሞውንም “ምክንያታዊ ያልሆነ ምርመራ እና ዛቻ ደርሶባቸዋል” ብሏል።

የሩሲያ ባለስልጣናት አሜሪካ አሻሽላ ያወጣቸውን ማስጠንቀቂያ አቃልለው ነው ያዩት።

ምን ያህል የአሜሪካ ዜጎች በሩሲያ እንደሚኖሩም ሆነ እንደተጓዙ መግለጫው ያልጠቀሰ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዜጎች ወደ ውጭ አገራት የሚያደርጉትን ጉዞ እንደማይከታሉ አስታውቀዋል።

ሩሲያ በባለፈው ዓመት በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን አገሪቱን ለቀው መሰደዳቸው ተዘግቧል።

ሆኖም አሁንም በሩሲያ ውስጥ ያሉ አሜሪካውያን “ትንኮሳ እንደሚያጋጥማቸው እና ኢላማ ሊሆኑ” እንደሚችሉም ነው የስቴት ዲፓርትመንት ያስጠነቀቀው።

በተለይም ጥምር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሩሲያ በምታደርገው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ምልመላ በአስገዳጅ ሁኔታ ሊሳተፉ ይችላሉም ብሏል።

“ሩሲያ ጥምር ዜግነት ያላቸውን ግለሶቦች አሜሪካዊነታቸውን ላትቀበል ትችላለች። እንዲሁም እነዚህ ዜጎች በአገሪቱ ባለው የአሜሪካ ቆንስላ ዕርዳታ እንዳያገኙ፣ በአስገዳጅ ሁኔታ በወታደርነት መመልመልና ከሩሲያ እንዳይወጡ መከልከል ወይም ሌሎች ዘመቻዎችን እንዲደግፉ ሊገደደሉ ይችላሉ” ሲል ማስጠንቀቂያው አትቷል።

በመንግሥት ስራ ላይ የነበሩትን ጨምሮ በተለያየ ስራ ዘርፍ የተሰማሩ የአሜሪካ ዜጎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ፣ ምርመራ እና እንግልት ደርሶባቸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አሜሪካ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎችን በተደጋጋሚ አውጥታለች ማለታቸውን የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።

“ይህንን ማስጠንቀቂያ ስንሰማ የመጀመሪያው አይደለም” ብለዋል።