ፈረንሳይ በጨረራ መጠን ምክንያት የአይፎን 12 ሽያጭን አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳይ አይፎን 12 ከልክ በላይ ጨረራ ያመነጫል በሚል የስልኩ ሽያጭ እንዲታገድ አዘዘች።
ትናንት መስከረም 1/2016 ዓ.ም. የሬዲዮ ሞገዶችን የሚቆጣጠረው አካል አይፎን 12 ከሚፈቀደው የኤሌክትሮማግኔቲክ ራዲዬሽን በላይ እያመነጨ ነው ብሏል።
ተቋሙ ስልክ አምራቹ አፕል ችግሩን በሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች በአስቸኳይ የማይቀርፍ ከሆነ በመላው አገሪቷ ተሽጠው የሚገኙ አይፎን 12 ስልኮችን ለመሰብሰብ እገደዳለሁ ሲል ጠንከር ያለ አቋሙን አስታውቋል።
የፈረንሳዩ የሬዲዮ ሞገዶች ተቆጣጣሪ ድረጅት ይህን ይበል እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት ስልኮች የሚያመነጩት የራዲዬሽን መጠን በሰው ልጆች ጤና ላይ እክል እንደሚፈጥር ምንም ማረጋገጫ የለም ይላል።
አይፎን 12 ከሦስት ዓመታት በፊት እአአ መስከረም 2020 ላይ ለገበያ የቀረበ ሲሆን በመላው ዓለም በከፍተኛ መጠን ከተሸጡ የአፕል ምርቶች መካከል አንዱ ነው።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በተቋሙ ውሳኔ እንደማይስማማ ለቢቢሲ ገልጿል።
አፕል ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ በራሱ ላብራቶሪ እና ገለልተኛ በሆነ ሦስተኛ ወገን ቤተ-ሙከራ የተገኙ ወጤቶች አይፎን 12 የሚያመነጨው ጨረራ በጤና ላይ ጉዳት እንደማያስከትል እና ከደረጃ በላይ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ማረጋገጫዎችን ለመንግሥታት ተቆጣጣሪዎች አቅርቤያለሁ ብሏል።
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አምራቹ ጨምሮም አይፎን 12 የጨረራ መጠኑ በሰዎች ላይ ጉዳት እንደማያስከትል በመላው ዓለም ባሉ ተቆጣጣሪዎች እውቅና ያለው ምርት ነው ይላል።
የፈረንሳይ የዲጂታል ሚንስተር ጄን-ኖዌል ባሮት አፕል ለፈረንሳይ መንግሥት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ ታዟል ብለዋል።
የፈረንሳዩ የሬዲዮ ሞገዶች ተቆጣጣሪ ድርጅት አይፎን 12 በኪስ ውስጥ ሲቀመጥ በአውሮፓ ኅብረት በአንድ ኪሎ ግራም ውስጥ መኖር ከሚኖርበት ስፔስፊክ አብሶርፕሽን ሬት 5.74 ዋትስ በላይ ነው ይላል።
ፈረንሳይ ይህን አይፎን 12 የተመለከተ የሽያጭ እግድን ያወጣችው አፕል አይፎን 15 ለገበያ ይፋ ባደረገበት ዕለት ነው።












