በኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ሞት ተከሶ የነበረው የቀድሞ የማላዊ ፕሬዚዳንት የእንጀራ ልጅ ነጻ ተባለ

የስደተኞቹ የጅምላ መቃብር

የፎቶው ባለመብት, Malawi Police

ባለፈው ዓመት በማላዊ በጅምላ ተቀብረው ከተገኙት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ሞት ጋር በተያያዘ በግድያ እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተከሶ የነበረው የማላዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የእንጀራ ልጅ ከወንጀሎቹ ነጻ ተባለ።

29 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ምልክት በሌለው የጅምላ መቃብር ተቀብረው የተገኙት ባለፈው ዓመት በህዳር ወር ነበር።

በስደተኞቹ ሞትም እጁ አለበት በሚል በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የቀድሞው የማላዊ ፕሬዚዳንት የእንጀራ ልጅ ታዲኪራ ማፉብዛ እና ስምንት ወንዶች ይገኙበታል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፒተር ሙታሪካ ከየትኛውም ወንጀል ጋር ንክኪ እንዳለው ፖሊስ ማስረጃ ሳያቀርብ የእንጀራ ልጃቸው በቁጥጥር ስር መዋሉ እንዳስገረማቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር።

ከአስራ ዘጠኝ ወራት የፍርድ ሂደት በኋላ ታዳኪራ ማፉብዛም ሆነ አጋር ናቸው ተብለው የተከሰሱ ሰዎች ከወንጀሉ ነጻ ተብለዋል።

“በውጤቱ ተደስተናል” ሲሉም ከውሳኔው በኋላ የማፉብዛ ጠበቃ ተናግረዋል።

“እውነት ለመናገር በደንበኛዬ ላይ የቀረበው ማስረጃ ውሃ የሚቋጥር አልነበረም “ ሲሉም አክለዋል።

ሆኖም የህዝብ አቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ባለስልጣን የሆኑት ድዚኮንዲያንቲ ማሉንዳ “ውሳኔውን ያልተጠበቀ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤት በነጻ ያሰናበተው ማፉብዛ ረቡዕ ዕለት ከፍርድ ቤቱ ሲወጣ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም ፎቶ ለመነሳት ቆሞ ነበር።

ባለፈው ዓመት ህዳር ወር ምዚምባ በተባለችው የማላዊ ግዛት ፖሊስ በጅምላ የተቀበሩ የ29 ስደተኞችን አስከሬን አግኝቷል።

የአካባቢው ወጣቶች ደኑ ውስጥ የሚያውክ ሽታ እንዳለ መጠቆማቸውን ተከትሎ ነበር አስክሬኖቹ በቁፋሮ የተገኙት።

ሁሉም አክስከሬኖች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሆነ ይታመናል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ኢትዮጵያ ከማላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ስለ ክስተቱ ምርመራ እያደረገች ነው ሲሉ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አምባሳደር መለስ፣ በክስተቱ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም መናገራቸው ይታወሳል።

የማላዊ ባለሥልጣናት ማፉብዛን ለቀናት ከፈለጉት በኋላም ግለሰቡ በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ ውስጥ እጁን መስጠቱንም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

የቀድሞው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ዲሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ በቀድሞው ፕሬዚዳንት እና ደጋፊዎቻቸው ላይ የተቃጣ “ፖለቲካዊ ሴራ” ነው ብለውታል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙና ብዝበዛ እንደሚደርስባቸው ማስታወቁ አይዘነጋም።

ድዛሌካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እንደሚደርስ ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ጽሕፈት ቤት (ዩኤንኦዲሲ) እና የማላዊ ፖሊስ ባደረጉት የጥምረት ክትትል ነው።

ማላዊ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከሚፈተኑ አገራት አንዷ ናት።

ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናት ጭምር በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ ለማቅናት ይሞክራሉ።

ጉዟቸው ግን በስቃይና በእንግልት የተሞላ ባስ ሲልም ለሞት የሚዳርግ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የማላዊ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኡላዲ ሙሳን ከስደተኞች ዝውውር ጋር በተያያዘ የአምስት ዓመት እስራት ፈርዶበታል።