ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ ኪንግደም ከስመ ጥር ዩኒቨርስቲዎች ለተመረቁ በቀላሉ ቪዛ ልትሰጥ ነው
በትምህርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በቀላሉ ለመግባት ማመልከት የሚችሉበት የቪዛ መርሃ ግብር ይፋ ተደረገ።
ዛሬ ሰኞ በሚጀመረው በዚህ አዲስ የቪዛ መርሃግብር “ከፍተኛ አቅም ያላቸው” ተመራቂዎች ወደ ሥራው ዓለም ከመቀላቀላቸው በፊት የተመቻቸላቸው መልካም አጋጣሚ ነው ሲል የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል።
መርሃ ግብሩ ከዩኬ ውጪ ከሚገኙ ስመጥር ዩኒቨርስቲዎች ባለፉት አምስት ዓመታት የተመረቁ ተማሪዎችን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ መስፈርቱን የሚያሟሉ የየትኛውም አገር ዜጎች ሥራ ማግኘት ሳይጠበቅባቸው ወደ ዩኬ ለማቅናት ማመልከት ይችላሉ።
ዕድሉ የሚቀናቸው ለመጀመሪያ እና ለሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች ሁለት ዓመት የሚያገለግል የሥራ ቪዛ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ሦስተኛ ዲግሪ ላላቸው ደግሞ የሦስት ዓመት ቪዛ ያገኛሉ።
ተጨማሪ መመዘኛዎችን የሚያሟሉ ተመራቂዎች ደግሞ ረጅም ዘመን የሚያገለግል የሥራ ቪዛ ሊያመለክቱ ይችላሉ።
ዩኬ ስመጥር የትምህርት ተቋማት የምትላቸው በታይምስ የዓለም ከፍተኛ የዩኒቨርስቲዎች ዝርዝር፣ ኳኳሬሊ ሲሞንድስ የዓለም ዩኒቨርስቲዎች ደረጃ ወይም የዓለም ዩኒቨርስቲዎች አካዳሚክ ደረጃ በተሰኙት የዩኒቨርስቲዎች ደረጃ ከሚመመደብባቸው ዝርዝርዎች ውስጥ እስከ 50ኛ ደረጃ የተካተቱትን ነው።
ከላይ በተጠቀሱት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ መዳቢዎች ከተለዩት በተጨማሪ የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርስቲ እና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜልበርንን ጨምሮ ከ17 የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ተማሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ናቸው።
ቪዛው 715 የእንግሊዝ ፓውንድ የሚከፈልበት ሲሆን ለጤና ምርመራ ተጨማሪ ክፍያ ይኖረዋል።
ዕድሉን ያገኙ ተመራቂዎች ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የመሄድ ይችላሉ። ሆኖም ቤተሰብ ለማቋቋም የሚያስችል 1 ሺህ 270 ፓውንድ ሊኖራቸው ይገባል።
በተጨማሪም ዕድሉን የሚያገኙ ሰዎች በወንጀል ውስጥ አለመሳተፋቸው ይረጋገጣል። እንግሊዝኛን አቀላጥፈው መናገርም ይጠበቅባቸዋል።
ይህ የከፍተኛ ተቋማት ዝርዝር በአፍሪካን፣ በላቲን አሜሪካ እና በደቡብ እስያ አገራት ካሉ ዩኒቨርስቲዎች አንድም እንኳን ባለማካተቱ አንዳንድ የትምህርት ባለሙያዎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል።