ምርጫ ቦርድ በአራት ክልሎች ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫ በመጪው ሰኔ ወር ሊያካሂድ ነው

የፎቶው ባለመብት, National Election Board Of Ethiopia
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ባልተካሄደባቸው እና በሚደግምባቸው በአራት ክልሎች በመጪው ሰኔ ወር መጀመሪያ ምርጫ ሊያካሂድ ነው።
ሰኔ 6፤ 2016 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ በ29 ምርጫ ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ዘጠኝ የህዝብ ተወካዮች እና 26 የክልል ምክር ቤቶች ወንበር ነው።
ቦርዱ ይህንን የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተ ዛሬ አርብ የካቲት 22፤ 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በጊዜ ሰሌዳው ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ካለፈው ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ እስከ የካቲት 11 የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ይካሄዳል።
ቦርዱ ከአስር ቀናት በኋላ መጋቢት 2፤ 2016 ዓ.ም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለህዝብ እንደሚያሳውቅ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ሰፍሯል።
ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ከሚያዚያ 7፤ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአስር ቀናት እንደሚካሄድ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተቀምጧል።
ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከሶስት ዓመት በፊት በ2013 ዓ.ም የመራጮች ምዝገባ መደረጉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ የመራጮች ምዝገባ በድጋሜ እንደሚካሄድ ይጠቁማል።
የመራጮች ምዝገባ በተጀመረበት ቀን ለአንድ ወር ከሶስት ሳምንት የሚዘልቅ የምረጡ ቅስቀሳ እንደሚካሄድም የጊዜ ሰሌዳው ያሳይል።
በአራቱ ክልሎች የተመዘገቡ መራጮች ሰኔ 6፤ 2016 ዓ.ም ድምጽ ከሰጡ ከአስር ቀናት በኋላ ሰኔ 16 ቦርዱ የተረጋገጠውን የምርጫ ውጤት ይፋ እንደሚያደርግ የጊዜ ሰሌዳው ያመለክታል።
ይህ የድጋሜ ምርጫ የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደ ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው።
በጸጥታ እና በሌሎች ምክንያቶች ከሁለት ዓመት ከስምንት ወራት በፊት ሰኔ 16፤ 2013 ዓ.ም ከተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ውጭ የሆኑ አካባቢዎች ግን አራቱ ክልሎች ብቻ አይደሉም። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ክልሎችም ምርጫ አልተካሄደባቸውም።
ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልልም ሙሉ በሙሉ ምርጫ አልተካሄደም። ቦርዱ በተያዘው 2016 የበጀት ዓመት ምርጫ ባለተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አስታውቆ ነበር።
ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ 320 ሚሊዮን ብር በጀት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደጸደቀ ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።












