ጋና ወደ ድል ስትመለስ ሮናልዶ አስቆጠርኩት ያለው ጎል ለፈርናንዴዝ ተቆጥሯል

ደቡብ ኮሪያ ከጋና ያደረጉት ጨዋታ በጎሎች የተንበሸበሸ፣ የስሜት መለዋወጥ እና ካርድ ያስመዘዘ ሆኖ አልፏል።

በመጀመሪያው ጨዋታ በፖርቹጋል የተሸነፈችው ጋና በ24ኛው ደቂቃ በሞሐመድ ሳሊሱ ጎል ቀዳሚ ሆነች።

ሞሐመድ ኩዱስ ያስቆጠራት ሁለተኛ ጎል ጋናዊያን በቀላሉ አሸነፉ አስብሎ ነበር።

የደቡብ ኮሪያ ሊግ ኮከብ ጎል አስቆጣሪው ቾ ጉ-ሱንግ በተከታታይ ያስቆጠራቸው ጎሎች ጨዋታውን ቀየሩት።

ደበብ ኮሪያ 2-2 ጋና።

ጋናዎች በፍጥነት በኩዱስ ባስቆጠሩት ጎል ምላሽ ሰጡ።

ደበብ ኮሪያ 2-3 ጋና።

ደቡብ ኮሪያ አቻ ለመሆን ያደረገችውን ተደጋጋሚ ጥረት ግብ ጠባቂው አቲ ዚጊ አክሽፎታል። ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ።

ጋናዎች ሲጨፍሩ የደቡብ ኮሪያው አምበል ሰን ሁንግ-ሚን ሲያለቅስ ታይቷል።

የኮሪያው አሰልጣኝ ፓውሎ ቤንቶ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ከዳኛው ጋር በነበራቸው እሰጥ አገባ ቀይ ካርድ ተመልክተዋል።

በምድቡ ሌላኛ ጨዋታ ፖርቹጋል ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።

የጨዋታው መልክ የተቀየረው 54ኛው ደቂቃ ላይ ነው።

ቡርኖ ፈርናንዴዝ ያሻማው ኳስ ከመረብ ላይ ያርፋል። ክርስቲያኖ ሮናልዶ ኳሱን ማስቆጠሩን በመተማመን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ደስታውን ገልጿል።

ጎሏ ሮናልዶን በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለፖርቹጋል በርካታ ጎል ካስቆጠረው ኡሴቢዮ የምታስተካክለው ነበረች።

በኋላም ሮናልዶ ኳሷን አልነካትም በሚል ጎሏ በፈርናንዴዝ ስም እንድትመዘገብ ተደርጓል።

ውሳኔው ሲገለጽ አጥቂው በምጸት ፈገግ ሲል ታይቷል።

ጨዋታው መገባደጃ ላይ የተገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምትም ፈርናንዴዝ አስቆጥሯል።

ምድቡን በስድስት ነጥብ የምትመራው ፖርቹጋል ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።

ጋና በሦስት ነትብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ደቡብ ኮሪያ እና ኡራጓይ አንድ አንድ ነጥብ አላቸው።

በምድብ ሰባት ጨዋታ ካሜሮን እና ሰርቢያ 3 ለ 3 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።

ጂን-ቻርለስ ካስቴሌቶ በ29ኛው ደቂቃ ካሜሮንን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጠረ።

ስታርሂንጃ ፓቭሎቪች እና ሰርጌይ ሚሊንኮቪች-ሳቪች በተከታታይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሰርቢያ 2 ለ 1 እየመራች እረፍት ወጡ።

አሌክሳንደር ሚትሮቪች ያስቆጠራት ጎል ሦስቱን ነጥቦች ሰርቢያ ለመውሰድ የቻለች አስመስሏት ነበር።

በካሜሮን በኩል ተቀይሮ የገባው ቪንሰንት አቡበከር የጨዋታውን መልክ ቀየረው።

አቡበከር አንድ ጎል በስሙ ሲያስመዘግብ ኤሪክ ማክሲም ቹፖ-ሞቲንግ ያስቆጠራትን ኳስ ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል።

በዚህም ጨዋታው ሦስት አቻ ተጠናቋል።

ለዋንጫው ትልቅ ግምት የተሰጣት ብራዚል ከስዊዘርላንድ ጋር ያደረገችው ጨዋታ ቅዝቅዝ ያለ ነበር።

በፊፋ ሃገራት ደረጃ ቀዳሚ የሆነችው ብራዚል ያለ ኮከብ ተጫዋቸዋ ኔይማር ነበር ወደ ሜዳ የገባችው።

ብራዚል በ83ኛው ደቂቃ ጎል ለማስቆጠር ችላለች።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካይ ካሰሚሮ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል።

ጨዋታው በዚሁ ውጤት ሲጠናቀቅ ብራዚል ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።

ብራዚል በስድስት ነጥብ ምድቡን ትመራለች። ስዊዘርላንድ ሦስት ነጥብ አላት።

ካሜሮን እና ሰርቢያ በአንድ ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የኳታር የዓለም ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ መከናወን ይጀምራሉ።

ምድብ አንድ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ 12 ሰዓት ይከናወናሉ።

አዘጋጇ ኳታር ኔዘርላንድስን አል ባይት ስታዲየም ትገጥማለች።

ኻሊፋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ላይ ኢኳዶር እና ሴኔጋል ይገናኛሉ።

ኔዘርላንድስ ምድቡን በአራት ነጥብ ስትመራ ኢኳዶርም በተመሳሳይ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ሴኔጋል ሦስት ነጥብ አላት። ኳታር ያለምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛለች።

በምድብ ሁለት እንግሊዝ ከዌልስ እና ኢራን ከአሜሪካ ምሽት አራት ሰዓት ይጫወታሉ።

ምድቡን እንግሊዝ በአራት ነጥብ ትመራለች። ኢራን በሦስት ነጥብ ትከተላለች። አሜሪካ ሁለት ነጥብ ሲኖራት ዌልስ አንድ ነጥብ አላት።